Wednesday, December 16, 2015


በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው
ኢሳት (ታህሳስ 6 2008)
ከሶስት ሳምንታት በፊት በምዕራብ ሸዋ ጊንጪ ላይ የተጀመረውና በመላው ኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለው ተቃውሞ ከአዲስ አበባ 60 ኪ/ሜ ጊንጪ ተባብሶ መቀጠሉን ብሉምበርግ ዘገበ። 
የብሉምበርግ ዘጋቢ ዊሊያም ዴቪድሰን ከስፍራው እንደዘገበው መንገድ ተዘግቷል፣ የመንግስት ሃይሎችን ጥቃት በማውገዝ፣ በሺ የሚቆጠሩ ፈረሰኞች ወደሆለታ ከተማ ተንቀሳቅሰዋል። 
የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን አርሶአደሮችን ያፈናቅላል፣ ህገመንገስቱን ጭምር ይጻረራል በሚል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጀመሩትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እያካተተ የቀጠለው ተቃውሞ፣ በተለይ በአዲስ አበባ አቅራቢያ እየተጠናከረ መገኘቱ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት ስቧል። 
በአዲስ አበባና በአምቦ መካከል የምትገኘውና ከአዲስ አበባ በ60 ኪሎሜትር ላይ የምትገኘው ወለንኮሚ ከተማ 4 ሰላማዊ ሰዎች ትናንት መገደላቸውን ከስፍራው የዘገበው የብሎምበርግ ዊሊያም ዴቪድሰን፣ ከተማዋ በመከላከያ ሰራዊት መያዟን ገልጿል። 
ሰው ተደብቆ እንደሚገኝና በየሰከንዱ የማያቋርጥ ተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ የገለጸው ዊሊያም ዴቪድሰን፣ ከጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት በስተቀር ሁሉም ተቋማት ላለፉት 4 ቀናት በሰልፈኞቹ ተይዘው መቆየታቸውን ጽፏል። 
የቶታል ነዳጅ ማደያ ተሳቢ መኪናን እንዲሁም የዳሸን ቢራ ፋብሪካ የጭነት መኪና በመጠቀም ወደ አምቦ የሚወስደውንና ወደ አዲስ አበባ የሚወስደውን መንገድ የዘጉት ሰልፈኞች የቀበሌ ፅ/ቤት ጠረጴዛዎችንና መደርደሪያዎችን ጭምር ለመንገድ መዝጊያነት እንደተጠቀሙ ከስፍራው ተዘግቧል። 
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል ተባብሶ የቀጠለውንና ብዙዎችን እየተገደሉበት ሁኔታ ያስቆጣቸው የሜታ ሮቢ ፈረሰኞች ዛሬ ረቡዕ ወደ ሆለታ ተንቀሳቅሰው ተቋውሟቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ለመንቀሳቀስ ሞክረው እልቂት ይከሰታል በሚል ማግባቢያ መመለሳቸው ተወስቷል። 
በኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል በተቀጣጠለው ህዝባዊ ቁጣ የመንግስት ሃይላት የአጸፋ ጥቃት የቀጠለ ሲሆን፣ ህዝባዊ እምቢተኝነትቱም ጨምሯል። እሳት እየተከታተለ ዝርዝሩን ያቀርባል።

No comments:

Post a Comment