Thursday, December 24, 2015

ከ “ናስ ማሰር – አፍ ማሰር” (ይገረም አለሙ) ይገረም አለሙ

ጊዜው ድሮ ድሮ ነው፡፡ቦታው ደግሞ ዝናር ወይንም ጀበርና ታጥቆ ብረት/ጠብ -መንጃ ትከሻ ላይ ጣል አድርጎ መሄድ አንድም ለአቅመ ወንድነት መድረስ ሁለትም በሀብት ከሌላው የተሻሉ ተደርጎ የሚታይበት አካባቢ ነው፡፡ ደረስኩ ደረስኩ ያለ ጎረምሳ በወቅቱ ተወዳጅና ተመራጭ የነበረውን ናስ ማሰር የተባለ ብረት/ጠመንጃ ይገዛና በሀገር በሰፈሩ አንቱ የተባሉና የተከበሩ ሽምግሌ ጋር በመሄድ አባት እስቲ ይህችን ብረት እዩልኛ ይላቸዋል፡፡ ርሳቸውም እያገላበጡ እያዩ ቀዝቀዝ ባለ ስሜት ጥሩ ናት ሸጋ ብረት ናት ይሉታል፡፡ ከገጽታቸውና ከአነጋገራቸው ጥሩ ስሜት አንዳልተሰማቸው የተረዳው ጎረምሳ ምነው አባት ሆሳ ነች እንዴ ወጥ አይደለችም? ሲላቸው አረም ሸጋ የሆነች ወጥ ብረት ነች ይሉታል፡፡ አሁንም አነጋራቸው ስላላማረው ታዲያ ምነው አነጋገርዎ ቀዝቀዝ ቢላቸው አዎ ልጄ ከናስ ማሰር አፍ ማሰር ነው የሚበጀው ብየ ነው አሉት ይባላል፡፡
Getachew Reda, Press and Publicity State Minister
የህይወትም ሆነ የንብረት ደህንነት የሚጠበቀው በጠመንጃ ሳይሆን እጅ በሚሰራው መልካም ድርጊት ከአንደበት በሚወጡ የታረሙ ቃላት ነው፡፡ በጠመንጃ እየተማመኑና በጡንቻ እያሰቡ የሚሰሩትና የሚናገሩት ሁሉ ጠላት ስለሚያፈራ፡ የህይወትና የንብረት ደህንነት አይኖርም፡፡ ስነ ምግባር የገራውና በራሱ እንዲፈጸምበት የማይፈልገውን በሌሎች የማይፈጽም፤ ፈሪሀ እግዚአብሄርን የተላበሰና አንደበቱ የታረመ ለህሊናው የሚገዛ ሰው ግን ወዳጅ እንጂ ጠላት ስለማይኖረው በቀንም ሆነ በለሊት በሜዳም ሆነ በጫካ ብቻውን ቢጓዝ የሚያሰጋው ነገር አይኖርም፡፡
በጠመንጃ መተማመን ሲጀመር የማሰብንና የመወሰንን ስራ ጡንቻ ስለሚረከብ የሚሰራው ሁሉ የእብሪት የሚነገረው ሁሉ ለከት የለሽ ይሆንና ወዳጅ እያነሰ ጠላት እየበዛ ይሄዳል፡፡ ይህ አድራጎት በፖለቲከኞች ሲፈጸም ደግሞ የሚያስከትለው ጦስ ከድርጊቱ ፈጻሚዎች ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን ይሆናል የሚጎዳው፡፡

ደርግን ማሸነፋቸው የፈጠረባቸው እብሪት ሀያ አራት አመት ሙሉ ሊበርድላቸው ያልቻለው የወያኔ ባለሥልጣናት የህዝብን አመኔታና ፍቅር ለማግኘት የሚያስችለውን መንገድ አያውቁትምና ዛሬም ህዝብን ማሰርና መግደሉን መሰብደብና ማፈናቀሉን ቀጥለውበታ፡፡ የንታቸው ብዛትም ይህን ሁሉ የሚያደርሱበትን ሕዝብ በለከት የለሽ አንደበታቸው ይሰድቡታል፡፡ ትግሉን የማያውቁት የባሩዱን ሽታ ያልቀመሱት አዳዲሶቹ ወያኔዎች ሳይቀሩ የጌቶቻቸውን ፈር እየተከተሉ ባልዋሉበት ተግባር ሲፎክሩ ባልተገራ አንደባተቸው ህዝብን ሲሳደቡ ሲዝቱና በህዘብ ሲያላግጡ እየሰማን ነው፡፡
ደርግን በማሸነፋቸው ሀያ አራት አመታት ሊበርድ ላልቻለ እብሪት የተዳረጉት ወያኔዎች የጠመንጃ ትምክህታቸው ህሊናቸውን ዘግቶ ማስተዋል ቢነሳቸው እንጂ በተቃራኒው ደርግ ለምንና እንዴት ሊሸነፍ በቃ ብለው ማሰብ ቢችሉና ከናስ ማሰር አፍ ማሰር ብሎ የሚመክር ሽማግሌም በአቅራቢያቸው ቢኖር ኖሮ በሀያ አራት አመታት ቆይታቸው ከጠመንጃ ትምክህት የህዝብን ፍቅር ወደ ማግኘት ሽግግር ባደረጉ ነበር፡፡
በጠመንጃ አምላኪነት የታበዩት ወያኔዎች በዘመነ ስልጣናቸው ከማናቸውም ወገን ለሚቀርቡ ማናቸውም ጥያቄዎች የሀይል ርምጃን ዘለፋ ስድብና ፍረጃን ምላሽ አድርገው ኖረዋል ፡፡ በውይይት ሊፈቱ ለሚችሉ ጥያቄዎች ተቃውሞዎችን ተከትሎ በሚያሰሙት የለሽ የለሽ የንቀት ንግግራቸው የበለጠ ህዝብን እያስቆጡ፣ ህዝቡ ቁጣውን በሰላማዊ ሰልፍ ሲገልጽ ለግድያ ያሰለጠኑትንና ሰዋዊ ባህርይውን አውልቀው የአውሬ ባህርይ ያለበሱትን ሰራዊት በማዝመት ያስደበድባሉ፣ ያስገድላሉ ያሳስራሉ፡፡ ሰሞኑን ኦሮምያ ውስጥ የተፈጸመውም ይሄው ከጠመንጃ አምላኪነት የተወለደው አረመኔያዊ ድርጊት ነው፡፡
ከአዲስ አበባ አልፎ አጎራባች የኦሮምያ ከተሞች መሬት አልበቃ ያላቸው ወያኔዎች ገደብ የለሽ የመሬት ፍላጎታቸውን ለማርካት የዋጡት ነው በሚል ከሁለት አመት በፊት የአዲስ አበባን ማስተር ፕላንን የተቃውሙ ዜጎችን በማሰር በመደብደብና በመግደል ተቃውሞውን ለማስቆም የቻለው ወያኔ ሁለት አመት አድፍጦ ከቆየ በኋላ አቶ አባይ ጸሀየ በአደባባይ ወጥተው ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ እንደርገዋለን፤ እንቅፋት ለመፍጠር የሚያስብ ካለም ልክ እናስገባዋለን በማለት ለህዝብ ያላቸውን ንቀት አሳዩ ወያኔ ያቀደውን አይደለም ያሰበውን ተግባራዊ ከማድረግ ወደ ኃላ እንደማይልም አረጋገጡ፡፡
አቶ አባይ ጸሀዬ እንዲህ በእብሪትና በድፍረት ለመናገር የበቁበትን ምክንያት መገመት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ጠመንጃ የወለደው ማንአለብኝነትና የህዝብ ንቀት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ኦህዴድን ጠፍጥፈው የሰሩት ወያኔዎች፤ መሪዎቹንም ከየምርኮ ሰፈር ሰብስበው ከምርኮኝነት ወደ ድርጅት መሪነት ያሸጋገሩዋቸው እነርሱ በመሆናቸው ለመቃወም ሞራልም አቅምም እንደሌላቸው ማወቃቸው ነው፡ ለሀያ አራት አመታትም ወያኔ በኦሮምያ ምድር ያሻውን ሲፈጽም ኦህዴድ የተሰጠውን ተልእኮ ከማስፈጸምና ሰጥ ለጥ ብሎ ከመታዘዝ ውጪ ትንፍሽ ያለው ነገር አለመኖሩም ለአባይ ጸሀዬ የእብሪት ዛቻና ድንፋታ አስተዋጽኦ አለው፡
ወያኔዎች ያልተረዱት ከባህሪያቸውም አንጻር ሊረዱት የማይችሉት ትናንት ወታደራዊ ምርኮኛ ዛሬ ደግሞ የስኳር ምርኮኛ ከሆኑትና ወዶ ገብ ሆነው ለወያኔ እጅ ከሰጡት የኦህዴድ አመራሮች ውጪ የሆኑ የኦህዴድ አመራሮች መኖራቸውን ፤እንዲሁም የኦህዴድን አመራሮች በምርኮ መያዝ ሕዝብን መያዝ አለመሆኑን ነው፡፡ይህን ደግሞ በአጭር ግዜ በመላ ኦሮምያ የተነሳው ተቃውሞ መማር ለሚችል በበቂ ያሳየ ነው፡፡
የአቶ አባይ ጸሀዬ ድንፋታ በተቃውሞ የቆመው ማስተር ፕላን ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን በማጋለጡ ምእራብ ሸዋ ላይ የተነሳው የደን መሸጥን ሰበብ ያደረገው የተማሪዎች ተቃውሞ ምክንያት ሆኖት ተዳፍኖ የቆየው ተቃውሞ ሲቀሰቀስ በኦህዴድ እና በወያኔ ሰፈር የተሰሙት ነገሮች መለያየት ምርኮኛም ቢሆን ጫናው ሲበዛበት አሻፈረኝ ሊል፤ሎሌም ቢሆን ንቀቱ ሲብስበት ሊያምጽ እንኳን ባይችል ሊያኮርፍ እንደሚችል ያሳየ ነው፡፡ ውሻ እንኳን በደል ከበዛበት ባይናከስ እንኳን ባለቤቱ ላይ ያጉረመርማል፡፡
ተቃውሞው ዳር እስከዳር ተቀጣጥሎ ኦህዴድን ከነመኖሩም የረሳው ወያኔ ገዳዮችን አሰማርቶ ተማሪዎችን በመግደል ተቃውሞውን አባባሰው፡፡ በቅርቡ የመንግሥት የህዝብ ግንኙነት ምኒስትር የሆነውና ከማን አንሼ በማለት በስድብና በዛቻ ከዋናዎቹ ወያኔዎች ጌቶቹ ጋር እየተፎካከረ ያለው ግልገሉ ወያኔ አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ሕዝቡን አጋንንት ሰይጣን ጠንቋይ እያለ በመሳደብ እሱም በአቅሙ የወያንን እብሪትና ንቀት በማሳየት በእሳት ላይ ቤኒዚን ጨመረ፡፡ ይህም ኦህዴድ ውስጥ ያሉትን ምርኮኞች፤ ወደ ገቦችና ነጻ ሰዎችን በአንድነት ከሕዝቡ እኩል አስቆጣ፡፡
ሰው የሚናገረው ያደገበትን፣ የተማረውን፣ የኖረበትን ወይም እየኖረበት ያለውን ወዘተ ነው፡፡ በመሆኑም አቶ ጌታቸው በስም ከጠራቸው ነገሮች ጋር ትውውቅ የጀመረው መቼ የትና እንዴት አንደሆነና ስለ እነርሱ እንዲህ በጥልቀት ያወቀበትን ምክንያት ባናውቅም የቅርብ ግንኙነት ያለው መሆኑንን ግን ንግግሩ አሰረድቶናል፡፡ በርግጥም ሲናገር የሚጠቀማቸውን ቃላቶች ብቻ ሳይሆን የፊቱን ገጽታ ጭምር ላስተዋለ ከጠቀሳቸው ነገሮች ጋ የቅርብ ትውውቅ እንዳለው ያስታውቃል፡፡ ባይሆንማ ኖሮ የቱንም ያህል መታበይ ልቡን ቢደፍነው፣ የቱንም ያህል ጠመንጃ አምላኪነት ማስተዋልን ነስቶ በጡንቻው አንዲያስብ ቢያደርገው፣ የቱንም ያህል ለከት የለሽነት ቢጠናወተው ህዝብን አጋንንት ሰይጣን ብሎ አይሰደብም በጠንቋይነትም አይፈረጅም ነበር፡፡
እብሪት፣ የህዝብ ንቀት፣ ለከት የለሽነት ወዘተ የወያኔ ባህርይ በመሆናቸው አቶ አባይ ጸሀዬ በዛቻና ድንፋታቸው፣ አቶ ጌታቸው ረዳ በለከት የለሽ አንደበቱ በህውኃትዘንድ ሊመሰገኑና ሊወደሱ እንጂ ሊነቀፉ፣ ሊወገዙና ሊከሰሱ እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡ነገር ግን ዘላለማዊ ምድራዊ ኃይል የለምና ጸሀይዋ መጥልቅ የጀመረች እለት ምላሴ ጠንቅ አተረፍሽ ለነፍሴ ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡
ተፈጥሮን ተመክሮ አይመልሰውምና ዋናዎቹ ወያኔዎች የተጠናወታቸው የህዝብ ንቀት እብሪትና ለከት የለሽነት(አፍ እንዳመጣ መናገር) መግደል መደብደብና ማሰር በውስጣቸው ስር ሰዶ የተዋሀዳቸውና ከዚህ ውጪ ሌላም ስለማያውቁ ይቅርብችሁ በሚል የሚሰጣቸውን ምክር መስሚያ የላቸውም፡፡ ሌሎቹ (መለስተኛና አዳዲሶቹ) እኛም እንደ ጌቶቻችን የሚሉ ካልሆኑ ሌላው ሌላው ቢቀር ከላይ የገለጽናቸው ሽማግሌ ለጎረምሳው እንደመከሩት ከናስ ማሰር አፍ ማሰር ይበጃል ልንላቸው እንወዳለን፡፡
ለኦህዴዶች ደግሞ የመጨረሻው መጨረሻ ሲመጣ ከሁለት ያጣ እንደምትሆኑ አስባችሁት ታውቃላችሁ? ወያኔዎች እስከቻሉና የእናንተ አገልጋይነት እስከቀጠለ ድረስ መላዋን ኢትዮጵያን ለመግዛት፣ ጀንበሯ ማዘቅዘቅ ስትጀምርና በአገዛዛቸው መቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ሲረዱ የሚገቡበት ምሽግ እንዳያጡ ሁለቱንም ጎን በጎን እየሰሩ ነው፡፡ የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ለመነጠል ወገባቸውን ታጥቀው የሚሰሩትና ትግራይን በሁሉም ረገድ ከሌሎች የኢትዮጵ ክፍሎች የበለጠች ለማድረግ የሚጥሩት ለዚሁ ነው፡፡
እናንተ ግን ምን አላችሁ፣ መሬት ከመቀራመትና ፎቅ ከመገንባት ውጪ ምን በጎ ነገር ሰርታችኋል፡፡ እንደውም ለወያኔ አገላጋይነት አድራችሁ እንወክለዋለን ከምትሉት ህዝብ ጋር ተቆራርጣችኋል፣ ከዚህ አልፋችሁም ደም ተቃብታችኋል፤ የመጨረሻው መጨረሻ ሲመጣ ደግሞ ወያኔ ሜዳ ላይ ጥሎአችሁ ወደ ምሽጉ ሲገባ ህዝቡ እንዳለየ አይቶ ንቆ የሚተዋችሁ ሳይሆን ለበቀል ይፈልጋችኋል ለፍረድ ያቀርባችኋል፡፡ በዛን ወቅት ወያኔ በምንም እንዴትም ሊታደጋችሁ አይችልም፣ ይልቁንም በአገልጋይነት አድራችሁ በሕዝብ ላይ የሰራችሁትን ሁሉ በማጋለጥ ራሱን ነጣ ለማድረግ ነው ዪዳዳው፡፡ ስለሆነም ወያኔ በጠመንጃ አምላኪነት የሚፈጽመውን የመንግስት ሳይሆን የወራሪ ሀይል ተግባር እናንተ የህውሀት አምላኪ ሆናችሁ ማስፈጸሙን በመቀጠል መጪውን ለመቀበል መዘጋጀት ወይንም በቃን ብላችሁ ከህዝብ የሚያስታርቃችሁን ውሳኔ መወሰን ወቅቱ ዛሬ ነው፡፡ህዝብ እንደሁ ይቅር ባይ መሀሪ ነው፡፡
በዚህ መልኩ አንደ ኦህዴድ አቋም መያዝና ራሳችሁን ነጻ ማውጣት የማይቻል ከሆነ ሁለተኛው አማራጭና ምርጫ ስንዴው ከእንክርዳዱ ራሱን መለየት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በኦህዴድ ውስጥ የጦርና የስኳር ምርኮኛ፤ ወዶ ገብ ( ለወያኔ ያደሩ) እና ነጻ ሰዎች መኖራችሁ ቢታወቅም ራሳችሁን በተግባር መግለጽ እስካልቻላችሁ ድረስ በኦህዴድ ላይ የሚቀርበው ተቃውሞና ክስ በጅምላ ሁላችሁንም ነው የሚመለከታችሁ፡፡ ስለሆነም በአንድ ቅርጫት ገብታችሁ ተንቃችሁ ህዝብን እያስናቃችሁ፤ ተባባሪ ሆናችሁ ህዝብን እያስፈጃችሁ መቀጠልና የሚመጣውን ለመቀበል መዘጋጀት አለያም በሌሎች ተጠቃሚነትና ጥፋት ተጠያቂ ላለመሆን ሚናችሁን መለየትና የህዝብ ወገን መሆናችሁን በተግባር ማሳየት ፡፡ ምርጫው የእናንተ የመወሰኛ ግዜአችሁም ዛሬ ነው፡

No comments:

Post a Comment