Wednesday, December 30, 2015

ጩኸቴን ማን ይስማኝ? እንኳን አትስማ የተባለው የሚሰማው አያዳምጠኝ።


ህወሃት ከጫካ ስትነሳ "አማራ"ን ጠላት ብላ ነበር፡ ውሎ አድሮ ሲታይጸ በአጽንዓት ሲመረመር ግን ጠላትነቷ ከአማራ አልነበረም፡ ከአማርኛ እንጂ።
በርግጥ ስትበላ የበለጠ የሚርባት፤ ስትለብስ የበለጠ የሚበርዳት፤ በልታም፤ ጠጥታም፤ አግኝታም የማትረካዋ ህወሃት በጎንደርና በወሎ ያለውን ለም መሬት ለመውሰድ እዛ አካባቢ ያሉ ገበሬዎችን፤ ታሪክ ጠገብ አባቶችን በሙሉ ጨፍጭፋለች፡ ያ ሁሉ ሆኖ ግን ጠላትነቷ ከአማራ አልነበረም ከአማርኛ እንጂ።
በቋንቋ የሚግባባ ህዝብ ችግርም ቢኖር ተነጋግሮ መፍትሄ ያገኛል፡ በደለም ቢኖር ተነጋግሬ የበደለ ይክሳል፡ ተበዳይ ይካሳል፡ በደለኛም ይቀጣል፡ ግን የጋራ ቋንቋ ከሌለ፡ እንኳን በደልን፤ ጥፋትን ተነጋግሮ ወደመፍትሄ ለመድረስ ይቅርና መውደድንና ፍቅርን እንኳ ለመግለፅ አይቻልም። አንድን ማህበረሰብ ለመበታተን፤ ለማለያየት፤ ፈጽሞ እንዳይግባባና በጋር አብሮ እንዳይመክር፤ እንዳይዘክር ለማድረግ ቋንቋን ማለያየት ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን ህወሃት ቀደም ብላ የተረዳችው ይመስላል።
በታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አማርኛ የብሄራዊ መግባቢያ ቋንቋ ነበር፡ ብዙ ህዝብ የሚናገረው፤ የሚግባባበት መገናኛ ድልድይ ነበር።
ህወሃት ግን ያደረገችው የመጀመሪያ መሰሪ ሴራ ይህን መገናኛ ድልድይ መስበር፤ አማርኛ ቋንቋን ማዳከም ነበር። ሁሉንም ማህበረሰብ በየክልሉ አጥራ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖር፤ አግዳ ተነጋግሮ የማይግባባ ትውልድ መፍጠር ነበር።
ይህ ሴራ ዘርን መሰረት ካደረገ ክልሏ ጋር በሚገባ ሰርቶላታል፡ 
የጎንደርና ወሎን ነዋሪዎችን አፈናቅላ፤ አሳዳ፤ በጅምላ ፈጅታ የህወሃትን ሰራዊት ስታሰፍር ያጠቃችው አማራን ሰለነበር የአማራን ጩኸት የሚሰማ አልነበረም፡ መግባባት የለማ፡ የተጨፈጨፈው "አማራ" እንጂ ኢትዮጵያዊ አልነበረማ፡ የጋራ ቋንቋ የለማ፤ የሚያስተሳስረን ድርና ማግ ተበጣጥሷላ፡

የጎንደርና ወሎ መሬት አልበቃ ብሎ የጋምቤላን መሬት ለመቀራመት አኝዋክን ሲትፈጅ፡ ሰሚ አልነበረም፡ የተጨፈጨፈው "አኝዋክ" ነዋ፡ ኢትዮጵያዊ አደለማ፡ የጋራ ቋንቋ የለ፤ የጋራ ሃገር የለ በጋራ የሚያስተሳስር ድር የለ፡
ጋምቤላ አልበቃ ብሎ ኦጋዴን መሬት ፍለጋ ስትሄድና "ኦጋዴኖችን" ስትፈጅ የ"ኦጋዴንን" ጩኸት የሰማ አልነበረም፤ ምክንያቱም የጋራ ቋንቋ፡ የጋራ ሃገር፡ የጋራ ድርና ማግ የለማ፡
እሱም አልበቃ በአፋር ለመስፋፋትና መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ለመዝረፍ አፋሮችን ስትጨፈጭፍ የ"አፋርን" ጩኸት የሰማ አልነበረም፤ ምክንያቱም የሚጨፈጨፉት "አፋሮች" ናቸዋ፡ የሚያስተሳስረው ድርና ማግ ተበጣጥሷላ፡ ድልድዩ ተሰብሯላ፡ "አፋሮች" እንጂ ኢትዮጵያን አይደሉማ፡
አሁን ደግሞ ተረኛና ብዙ ሃብት ለማጋበስ የሚያስችለው ኣዲስ አበባ ዙሪያ ያለ መሬት ነው ስለዚህ በዙሪያው ለዘመናት የኖሩ ገበሬዎች መባረር አለባቸው፡ መሬቱን የህወሃት ባለስልጣናት ይፈልጉታላ፤ ህንጻ ይሰሩበታላ፤ ሸጠው ገንዘብ ያከማቹበታላ፡፡ ይህንን የተቃወሙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ልክ መግባት ስላለባቸው በጅምላ እየተጨፈጨፉ ነው። ጩኸታቸው ግን አይሰማም፤ ምክንያቱም የ"ኦሮሞ" ተማሪዎች ናቸዋ፡ ኢትዮጵያውያን አይደሉማ፤ የጋራ ቋንቋ የለማ፤ የሚያስተሳስረን ሃረግ ተበጣጥሷላ፡
ግን እስከመቼ፡ ለዚህ ለህወሃት ሴራ መሳካት ደግሞ ምሁራኖች ከፍተኛውን ድርሻ መውሰድ አለባቸው ብዬ በድፍረት ለመናገር እገደዳለሁ። የስርዓት ጥላቻን ከቋንቋ ጋር አገናኝቶ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖር፡ ተቀራርቦ ተነጋግሮ ታሪካዊ ስህተቶች ቢኖሩ እንዛን ፈር ባለው መንገድ አስተናግዶ የጋራ በጋራ ተቆርቋሪነት መንከባከብ ሲቻል፡ የመጠፋፋት፡ የዘራፌዋ፡ ጉዞ ተመርጦ ስለነበር ለዚህ በቅተናል፡
አሁን በየዩኒቨርሲቲው የሚጨፈጨፉ ወጣቶች የማናቸው? የነ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ ልጆች አደለም? የነ አብዲሳ አጋ ልጆች አደለም? የነ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ልጆች አደሉም፡ ነገን ተረካቢ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አደሉም? ግን ጩኸታቸው የኢትዮጵያን ተማሪዎች ሳይሆን የ "ኦሮሞ" ልጆች ጩኸት ተደርጎ ሌላው በታዛቢነት እያዳመጠ ነው።
አይበቃም? 
ጅምሩ ጥሩ ነው ሊባል ይችል ይሆናል ግን በቂ አደለም፡ ዛሬም ወጣቶች ከመታፈን አልዳኑም፤ ዘሬም በዱር በቀል የህወሃት አጋዚ ከመጨፍጨፍ አልተረፉም፡ 
የፈረሰውን ድልድይ የምንገነባው መቼ ነው፡ የተበጣጠሰውን ድርና መማግ የሚንቀጥለው መቼ ነው?
ጊዜ የለም በአራቱም ማዕዘናት ነገን ተረካቢ ወጣቶቻችን እየረገፉ ነው።
ህወሃትና ዱር በቀል አጋዚ ሰራዊቷ ባስቸኳይ ሊገቱ ይገባል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የጋራ ቋንቋ፡ የጋራ ሃገር አለን ብለን ስናምንና የሚያስተሳስረን ድርና ማግ አሁንም ጠንካራ መሆኑን ስንገነዘብ ነው፡

ለሁላችንም ልቦና ይስጠን!!

No comments:

Post a Comment