Sunday, December 27, 2015

ኢትዮጵያ የማን ናት? (ከአንተነህ መርዕድ) ከአንተነህ መርዕድ

“ኢትዮጵያ የማን ሆና ነው ኦሮሞ የሚገነጠለው” ( ኮሎኔል ዓለሙ ቂጤሳ)
“ኦሮሞ ግንድ ነው አይገነጠልም” (ጄኔራል ጀጋማ ኬሎ)

ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት የብዙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የልብ ህመም ሆኖ የቆየው የኦሮሞ ጥያቄ ነው። ዛሬም በኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ጥያቄ ቢኖር የኦሮሞ
Map of Ethiopia
ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሆነ በጨለማ ለመግዛት የተነሱት ጣልያንም ሆነ ወያኔ ለአላማቸው ማስፈፀምያ የዚህን ታላቅ ህዝብ ጥያቄ ነበር ኢትዮጵያን ለመጉዳት የሚጠቀሙበት። ከላይ በጥቅስ ያስቀመጥኋቸውን ሃሳቦች የተናገሩት በኦሮሞ ህብረተሰብ ውስጥ ትፅዕኖ ፈጣሪና ታላቅ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ከአስራ አራት ዓመት በፊት በሞት የተለዩን ኮሎኔል ዓለሙ ቂጤሳን ንግድ ማተምያ ቤት አጠገብ ባለው መኖርያ ቤታቸው ለጦቢያ መጽሄት ቃለ መጠይቅ ልናደርግላቸው አንጋፋው ጋዜጠኛ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ ጋር ሄደን ነበር። ሜጫና ቱሉማን በመመስረትና ለኦሮሞ መብት በመታገል ኢትዮጵያዊ መፍትሄ እንዲያግኝ በመልፋት የሚታወቁት እኒህ አንጋፋ አባት አመሻሽ እድሜአቸው ላይ ሆነው ያዩት ሁሉ አላስደሰታቸውም።

አክራሪ ፅንፍ የያዙ የኦሮሞ ኤሊቶች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን መለየትን እንደመፍትሄ በግልፅ በሚሰብኩበትና ለተግባራዊነቱ በሚገፉበት፤ ወያኔም ይህንኑ አጀንዳ አስጨብጦ በሚያራግብበት ፈታኝ ወቅት ነበር የሄድንባቸው። አምቦ አካባቢ ግንደበረት ተወልዶ ከማደጉም በላይ የኦሮሞን ህብረተሰብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ጋሽ ሙሉጌታ ከኮሎኔሉ ጋር ያላቸውን መግባባትና መከባበር ስመለከት ተገርሜያለሁ። በርካታ አገራዊና የግል ጥያቄዎችን ያቀረብንላቸው ቢሆንም በቁጣ ስሜት የመለሱት ለኦሮሞ ችግር ከኢትዮጵያ መገንጠል መፍትሄ ይሆናልን? የሚለውን ጥያቄአችንን ነበር። “ኢትዮጵያ የማን ሆና ነው ኦሮሞ የሚገነጠለው?” በማለት ነበር ጥያቄአችንን በጥያቄ የመለሱት።
ኦሮሞ የኢትዮጵያ እምብርት ብቻ ሳይሆን ከሰሜን ጫፍ እስከ ትግራይ፣ በደቡብ እስከ ኬንያ፤ በምስራቅ ኦጋዴንን ነክቶ በምዕራብ ሱዳን ድረስ ሲያጣቅስ በመሃል ከአብዣኛው ኢትዮጵያውያን ተዛንቆ፣ ተዋልዶ፣ ተዋህዶ በመኖሩ እድሉ የኢትዮጵያ ባለቤት መሆን እንጅ ጊዜው እንደወለዳቸው ፖለቲከኞች ቁራሽ መሬት ይዞ መወሰን አይደለም የህዝቡ ፍላጎት። ኮሎኔል ዓለሙ ቂጤሳም የገለፁት ይህንኑ የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት ነበር። ቃለ መጠይቁን ለህትመት አብቅተን ኮሎኔል ዓለሙን ደግመን ስናገኛቸው ያየሁትና የሰማሁት ለብዙ ጊዜ አሳዝኖኛል። የጊዜው የፖለቲካ አራጋቢዎች ትልቅ የመንፈስ ስብራት ፈጥረውባቸው ነበር። “ዛሬ በሽምግልናዬ ቤት ውስጥ ተወስኜ ሞቴን በጸጋ በምጠብቅበት ሰዓት የአገር ጉዳይ ጠልቆ ያልገባቸው ወንድሞቼ በእኔና በቤተሰቤ ያሳደሩብኝ ጫና ቀላል አይደለም። ቀሪ ጊዜዬን በሃዘን እንዳልቋጨው ታገሱኝ” አሉን። እኛም ታገስናቸው።
ዛሬ ኮሎኔል ዓለሙ ቂጤሳና አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ በህይወት የሉም። ጋሽ ሙሉጌታ ሊለየን ትንሽ ሰዓታት ሲቀረው “ለዘመናት ወጣቱ ላይ የነበረኝን ወቀሳ አንስቻለሁ፤ አገሩን የሚታደግ ወጣት በማየቴ ኮርቻለሁ። በሉ ተነሱ ሰልፍ የጀግና ነው፣ ድል የእግዜብሄር ነው” ሲል ተስፋውንና ጥሪውን ገልፆ አልፏል። የኦሮሞ ህዝብና ቀሪው ኢትዮጵያዊ ባንድ ቁሞ ታላቋን ኢትዮጵያን የመገንባቱ ተስፋ እየለመለመ ነው። የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ ባለቤት ለመሆን አገራዊ አጀንዳ ይዞ እየተነሳ ነው። የኦሮሞ ፖለቲከኞች (ኤሊቶች) እንደ ኦሮሞ ህዝብ ሰፊ ልቦናና ኢትዮጵያዊ ባለቤትነትን ካላቀፉ ለጠባቡና ለጊዜአዊ የፖለቲካ ፍጆታ ራሳቸውን ወስነው መነሳት እንደማያዋጣቸው የተረዱ ይመስላል። ከአንጋፋ ፖለቲከኞች ሌንጮ ለታና ጓዶቻቸው፣ ከወጣቶቹም ጁአር ሞሃመድና ሌሎችም ሰሞኑን ያሳዩት ሁሉን አቃፊ (አኮሞዳቲቭ) አቋም ያየ፤ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የኦሮሞን ህብረተሰብ በሚመጥን ደረጃ ለመገኘት መንቀሳቀሳቸውን ወይንም መፈለጋቸውን ይገነዘባል። ያድርግልን። ከሰሞኑ የህዝብ አመፅ በኋላ የአማራውና የኦሮሞው አንድነት ጥሪ በሰፊው ተሰብኳል። አመፁን ተከትሎ የመጣ በረከት ይመስላል (ፈረንጆች ኤ ብሌሲንግ ኢን ዲስጋይዝ እንደሚሉት)። አመፁን ወደ እውነተኛ አንድነት እንዲያድግ ከተፈለገ አጀንዳው ከክልላዊነት ወጥቶ ወደ አገራዊነት መለወጥ አለበት።

ለኢትዮጵያ ህልውናና እድገት የህዝቦቿ መተባበር፤ በተለይም የኦሮሞውና የአማራው በአንድነት መቆም ወሳኝ ነው። ለዚህም ነው የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጠው ለመግዛት የሚያልሙ የውጭ ሆነ የውስጥ ጠላቶች እነዚህን ጉልህ የህዝብ ክፍሎችን የጥቃታቸው ኢላማ የሚያደርጉት። አድዋ ላይ አባቶቻችን ያንበረከኳትና በዓለም ፊት ያዋረዷት ጣልያን የሽንፈቷ ምክንያት የኢትዮጵያውያን ህብረት መሆኑን ከውድቀቷ ተምራለች። ከአርባ ዓመት በኋላ ቂም ቋጥራ ዳግም ስትመጣ፤ መጀመርያ የተሰማራችው ተባብረው የደቆሷትን አማራና ኦሮሞን በመለያየት ላይ ነው። ብዙ ክፍተት ለጊዜው ብትፈጥርም እንዳልተሳካላት ሌላውን የኦሮሞ የጀግንነት ምሳሌ የሆኑትን ኢትዮጵያዊ ታሪክእንቃኝ። የበጋው መብረቅ የሚባሉት የጀግናው የጄኔራል ጀጋማ ኬሎ አጎት ናቸው። ፊታውራሪ አባዶዮ ዋሚ ገሮ ይባላሉ። አባ ዶዮ የፈረስ ስማቸው ነው። ጣልያን አማራንና ኦሮሞን ለመከፋፈል በሰፊው ሠርቶ ስለነበር፤ ይህ ሰበካ እውነት የመሰላቸው ታላላቅ ሰዎች የፊታውራሪ አባ ዶዮ ዋሚ ገሮን ምክርና ይሁንታ ለመሻት ቤታቸው ሄዱ። “አማራ የሚበድለን ስለሆነ ከአካባቢያችን ልናስወጣ አስበናል ምን ይመክሩናል?” የሚል ሃሳብ አቀረቡላቸው። እንግዶቻቸውን አብልተው አጠጥተው፣ በነገሩም አሰላስለው ቆዩና ለእያንዳንዳቸው እፍኝ እፍኝ ሙሉ ሰርገኛ ጤፍ እንዲሰጣቸው አዘዙ። ጤፉም ለእንግዶቹ ተሰጠ። “በሉ ቀዩን ከነጩ ጤፍ ለዩልኝ” አሏቸው። ግራ የተጋቡት እንግዶች “አባ ዶዮ ይሄማ እንዴት ይቻላል?” በማለት እንደማይሆን ነገሯቸው። “ያቀረባችሁልኝ እኮ እንዲህ ያለ ጥያቄ ነው። ከአማራ ያልተጋባ፣ ያልወለደ፣ ያልተዛመደ ማን አለ? እንዝመት ካላችሁ በራሳችን፣ በቤታችን እንጀምር። ይህንን ደግሳ ያበላቻችሁ የልጆቼ እናት አማራ ናት። ልጆቼንና ልጆቿንም፣ እሷንም ጭምር ግደሉ፤ እናንተም በየቤታችሁም ሂዱና የአማራ ደም ያለበትን አጥፉ። ይህ እንዲሆን አይደል የምትጠይቁኝ” አሏቸው። በርግጥም ከአማራ ያልተዛነቀ ኦሮሞ፤ ከኦሮሞ ያልተዋለደ አማራ ጥቂት ነው። ጥፋታቸውን የተረዱት መልዕክተኞች የጣልያንን ተልዕኮ አከሸፉ። በነገራችን ላይ ዶክተር መረራ ጉዲናም አንዳንድ ፅንፈኛ የሆኑትን ፀረ አማራ የሆኑ የኦሮሞ ልሂቃንን “ማታ ቤታቸው አማራ ሚስቶቻቸውን ታቅፈው እያደሩ ቀን ስለእነዚህ ትልልቅ ህዝቦች መለያየት ይሰብካሉ” ሲሉ ከሃያ ዓመት በፊት መተቸታቸውን አስታውሳልሁ።
ታሪኩ በዚህ አያበቃም። የፊታውራሪ አባ ዶዮ ዋሚ ገሮ ወንድም የአባ ኬሎ ገሮ ልጅ ጀጋማ ኪሎ ጣልያንን ገና በአስራ አራት አመታቸው ጀምሮ ነው በጥይት እየቆሉ መውጫ መግቢያ አሳጥተው ነፃነታችንን ያጎናጸፉን። የጣልያንን ሴራ ብቻ ሳይሆን ሰላቶን ከነባንዳው አይቀጡ ቅጣት የቀጡት ጄኔራል ጀጋማ ኬሎ ከአምሳ አምስት ዓመት በኋላ የባንዳ ልጆች የሆኑ የወያኔ መሪዎች በአማራውና በኦሮሞው ልዩነት ፈጥረው ለማፋጀት ሲነሱ አጎታቸው ዘንድ ለምክር እንደሄዱ መልዕክተኞች የህወሃትን መርዝ ይዘው ኦሮሞን ከኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠል ሲያቀነቅኑ ልባቸው በሃዘን ተነክቷል። አዛውንቱ ፖለቲከኛ ቡልቻ ደመቅሳ “ለኦሮሞ መገንጠል ይበጀዋል ወይ?” ብለው ለጠየቋቸው “ኦሮሞ ግንድ ነው አይገነጠልም” ቅርንጫፍ እንጂ ግንድ አይገነጠልም ብለው እንደመለሱላቸው ሰምቻለሁ። ዛሬ ጄኔራል ጀጋማ ኬሎ የ95 ዓመት አዛውንት ናቸው። የኦሮሞ አድባር፣ የኦሮሞ ዋርካ፣ የአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ዋርካ በህይወት እያሉ ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ስንት ጊዜ ተጠቃች? ስንት ጊዜ አፈር ልሳ ተነሳች?
አብዛኞቹ የህወሃት መሪዎች ለጣልያን ያደሩ የባንዳ ልጆች መሆናቸውን ከገብረመድህን አርዓያ የበለጠ ምስክር አንሻም። Rኡቅ ሳንሄድ የህወሃት ሴራ ባለቤት የመለስ ዜናዊ አያት የጣልያኑ ደጃዝማች አስረስ በርካታ ህዝብ ያስፈጁ አገር የሸጡ ባንዳ መሆናቸውን ሁሉም ያውቀዋል። ታድያ እነመለስና ጓደኞቻቸው ከአባቶቻቸው የተማሩት አገርን መታደግ ሳይሆን ማፍረስ ነው። ጀግናው አፄ ዮሃንስ ከበርካታ የኢትዮጵያ ጀግኖች ጋር(የትግራይን ጨምሮ) አንግታቸውን የተሰውበትን መሬት ሳይቀር ለሱዳን ሲሰጡ ሃፍረት የማያውቁ ከሃዲ ወንጀለኞች ናቸው። በመሆናቸውም ነው መሃል ኢትዮጵያን አፍኖ ለመግዛት አማራና ኦሮሞን ለመለያየት የባንዳ አባቶቻቸውን ጌቶች ፖሊሲ የተከተሉት። ይህ ተንኮል ከጣልያን የበለጠ ለእነሱ ሰርቷል። ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት ከሁለቱ ህዝብ ፅንፈኛ የሆኑና ለፍርፋሪ የሚያድሩትን በማግኘታቸው ዙፋናቸው ላይ እስከአሁን ተደላድለዋል።
አማራው በየሄደበት እንደ አውሬ ታድኗል። ዐይኑ እያየ ገደል ላይ ተጥሏል። ይህንን ደግሞ ሃውዜን ላይ በትግራይ ህዝብ ሲፈፅሙት የተካኑ በመሆናቸው በፊልም እየቀረፁ “ኦሮሞው አማራውን እንዲህ አድርጎ ነው የገደለው” ብለው በአደባባይ በማሳየት እስከዛሬ የሠራላቸውን የመከፋፈል ሴራ ውጤታማ አድርጎታል። ተንኮላቸው በሁለት በኩል ስለት እንዳለው ቢላዋ ባንድ በኩል ኦሮሞውን ከአማራ ለመለያየት ሲያገለግላቸው፤ ሌላኛው ስለት ኦነግን የፖለቲካ ሞት እንዲሞትላቸው ማድረጋቸውን የዚህ ተንኮል መሃንዲስ ከሆነው መለስ ዜናዊ ጋር በቅርብ የሠሩትና አጥርተው የሚያውቁት ሊንጮ ለታ ዛሬ በአዛውንት እድሜአቸውና በሰከነ አእምሮአቸው ቢመሰክሩ ደስ ይለናል። ለትናንት የፖለቲካ ዓላማ ባይጠቅምም፤ ለዛሬውና ለነገው ትውልድ ትምህርት ይሆነዋል።
ኦሮሞው በየቦታው ሲሰደድ፣ ሲገደልና የአገሪቱን እስር ቤቶች ሲያጨናንቅ፤ አድር ባይ ልጆቹ ወያኔ የሰጣቸውን የመቶ ዓመት ታሪክ ሲቆፍሩና ተጠያቂ ሲፈልጉ፣ ዛሬ የሚፈጸመውን ዐይን ያወጣ በደልና ግፍ እነሱም ዐይተው እንዳላዩ፣ ህዝቡም እንዳያይ ብዙ የከፋ ወንጀል ሠርተዋል። ቢዘርፉ የማይጠረቁ የወያኔ መኳንንት አዲስ አበባን ጨርሰው የአካባቢውን ገበሬ ሲያፈናቅሉ “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” በሚል ጅል ተመክሮአቸው ህዝቡን አጥንቱ እስኪቀር ትንሽ ፍርፋሪ እያገኙ አስግጠውታል። ዛሬ ፅዋው ሞልቶ ሲፈስና ህዝቡ ከዳር ዳር ሲነሳ በድንገት ባነኑና የህዝብ ደጋፊ ነን ለማለት በአዳራሽ ተሰብስበው ወያኔ ላይ መፎከራቸውን ከኢሳት ሰምተናል። ልጃገረዷ አረገዘች የሚል ሃሜት ሲናፈስ “እስቲ ታገሱ፤ እህል ከሆነ ይጠፋል፣ ሽል ከሆነም ይገፋል” እንዳሉት ኦህዴዶቹ ከልባቸው ከሆነ የምናየው ነው። ጌታቸው ወያኔ ሳይቀድሙት በመቅደም አባዜ የተካነ ነውና ቀበቶአቸውን ጠበቅ ሊያደርጉ ይገባል። የስምንት ዓመት ልጅ በጥይት ከሚደፋ፣ አስከሬን ለወላጅ በሺህ ብር ከሚሸጥ፣ አገርን ቆርሶ ከሚቸበችብ አምባገነን ጋር ከመስራት የከፋ ወንጀል አለ? ርህራሄ የሌለው ህወሃት ለዚህ ድፍረታቸው በመቶ ሺዎች አሳልፈው ከሰጧቸው፣ እስር ቤት ከሚገኙ ወንድሞቻቸው ጋር ለማጎር አይሳሳም። ደርግ መኢሶንን ተጠቅሞበት ደመኛ ጠላቶቹ ከሆኑት ኢህአፓዎች ጋር በአንድ እስርቤትና በአንድ ጉድጓድ እንዳገናኛቸው ሁሉ ወያኔም ይህንኑ እንደሚያደርግ ግልፅ ነው። ኦህዴድ ሆይ! በአገሪቱ በተለይ በኦሮሞው ላይ ለተሠራው ሁሉ ወንጀል ሃላፊነቱን በግልፅ በመውሰድና ከህዝብ ጎን በመቆም ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ መፍትሄ ለማምጣት ካልታገላችሁ ይህ ሙት ስርዓት ይዟችሁ ይሞታል።
የኦሮሞ ህዝብ ልበ ሰፊ ነው። አስተዋይና አዋቂም ነው። ይህንን ትልቅነቱን ሰሞኑን በሚገባ አሳይቷል። በውስጡ ያሉትን አማሮችና ሌሎችንም እንዲተነኩስ ዘረኞች ቢሰብኩትም በልበ ሰፊነት ሰላማዊ ትግል እያደረጉ ልጆቹ ለሰላምና ለፍቅር ሲሉ ወድቀዋል። አምናም ዘንድሮም የወደቁ ጀግኖች የኢትዮጵያ ሰማዕታት ናቸው። ለጠባብ አላማ አልወደቁም። ይልቅስ ገዳዮቻቸው ወራዳ ታሪክ ፈፅመዋል። የኦሮሞ ህዝብ በትልቅነቱ ልክ አባቶቹ በደማቸው የአቆዩአትን አገር ባለቤት ሆኖ ነፃ ሊያወጣት ከወንድሞቹ ጋር ይሰለፋል እንጂ ፖለቲከኞች በሰፉለት አርቲፊሻልና ጠባብ ዓላማ ራሱን ወደ ትንሽነት አይቀይርም። ለዚያውም የትግራይን ህዝብ የካዱ የባንዳ ልጆች መጠቀምያ አይሆንም። ለኦሮሞ ህዝብ እንኳን ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካ ትጠበዋለች። “ኢትዮጵያ የማን ሁና ነው ኦሮሞ የሚገነጠለው” ያሉት ኮሎኔል ዓለሙ ቂጤሳ ዛሬ በህይወት ቢኖሩ ምንኛ ተስፋቸው በለመለመ። “ኦሮሞ ግንድ ነው አይገነጠልም” ያሉት ጀግናው ጄኔራል ጀጋማ ኬሎ እንደልብ መስማት ባዳገታቸው በዚህ የሽምግልና ወቅት አሁን በምልክትም ቢሆን የኦሮሞን ህዝብ እንቅስቃሴ መረዳታቸው አይቀርምና የመጨረሻ ዘመናቸው በሃዘን እንዳይቋጭ መትጋት ያስፈልገናል።
የእኛ ያልሆነን ሶሻሊዝም ለማፅደቅ የብዙ ኢትዮጵያውያን ደም ፈስሶ ስር ሳይሰድ ቀርቷል። የልዩነትና የጎሳ ፖለቲካም አፍላው ያለፈበትና የመሸበት አስተሳሰብ መሆኑን እንደሶሻሊዝሙ ብዙ ከፍለንበት ተምረናል። ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ካለንበት ጨለማ ለመውጣት በጋራ ካልተነሳን ተስፋ የለንም። በተለይም ከአማራውና ከኦሮሞው የወጡ ጽንፈኞች በህዝቡ ስም በመነገድ አምባገነኑና ዘረኛው የውያኔ አገዛዝ እድሜ እንዲኖርው ከማገዝ እንዲቆጠቡ በግልፅ ሊነገራቸው ይገባል። በዘውግ ፖለቲካ ተጨፍነን እያለ፣ ለከተማ መሬት ስናዝን፣ የአግሪቱ ለም መሬት ለሱዳን እየተሰጠ ነው። በጉርሻ ስንጣላ የህልውናችን መሰረቱ ራትና ምሳችን ሊሄድ ነው። መተማ ላይ የአፄ ዮሃንስን አንገት የቀላ ሰይፍ ድንበሯን አናስነካም ያሉትን ንፁሃን በመቁረጥ ላይ ነው። ሰይፉ ከሁለት አቅጣጫ ተደቅኖብናል። ከሱዳንና ከህወሃት። ሰሞኑን የሱዳኑ መሪ አልበሽር ሰራዊታቸው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲንቀሳቀስ አዝዘዋል። በኢትዮጵያ ምንግስት በኩል ደግሞ ኃይለማርያም ደሳልኝ ኢትዮጵያውያንን ሱዳንን የሚያጠቁ ሽፍቶች ሲሉ በፓርላማው ፊት ወንጅለዋል። ይህም ይህወሃት ሰራዊት ከሱዳን ጋር ተባብሮ ዜጎቹን ለመውጋት መዘጋጀቱን ያመለክታል። ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደዚህ ያለ ለህልውናዋ ጠላት የሆነ መንግሥት አጋጥሟት አያውቅም።
ይህን ጽሁፍ በማጠቃለል ላይ እያለሁ ወያኔዎች በቀለ ገርባንና ሌሎችንም እያደኑ ማሰራቸውን ሰማሁ። ይህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እጣ መሆኑን ያላወቀ ካለ አንድም የዋህ ነው፣ ያለዚያም የስርዓቱ አገልጋይ ነው። በቀለ ገርባን የመሰለ የተረጋጋ፣ ሰላም ፈላጊና ትልቅ የዓላማ ሰው አገሪቷ እንዳይኖራት ወያኔ ተግቶ መሥራት የጀመረው አሁን አይደለም። ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን፣ አሰፋ ማሩን፣ ተስፋዬ ታደሰን….ገድሏል፤ የቅንጅት መሪዎችን፣ አንዱዓለም አራጌንና ሺህ የኢትዮጵያ ተስፋዎችን አስሯል። በአራቱም ማዕዘናት ወጣትና ሽማግሌ ኢትዮጵያውያንን ገድሏል። አገርንና ህዝብን እንደጠላት ኢላማ አድርጎ ከተነሳ ስርዓት በጎ ነገር የመጠበቅ የዋህነት አብሮ የመግደልን ያህል ወንጀል ከሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ኢትዮጵያውያን ሌት ተቀን መስራት ያለብን በቀለ ገርባንና ተመስገን ደስአለኝን ከመሰሉ ጀግኖች ጎን መቆምና እነሱን የመሰሉ ሺዎችን ከመካከላችን ማፍራትና መንከባከብ መሆን አለበት። ዳር ቆሞ ሌሎችን በመተቸት የተጠመደው ልሂቃን እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ተገቢ ዋጋ እየከፈሉ ባለበት ሰዓት የጥርጣሬና ያለመተማመን ዲስኩሩን ያቁምና የትግሉ አካል ይሁን።
ኢትዮጵያ የቅን ልጆቿ ሁሉ የጋራ ናት!
በሁሉም አቅጣጫ መስዋዕት በሚከፍሉ ልጆቿም በቅርቡ ጨለማው ይገፍላታል!!
በአንድነት የተነሱ ታጋዮቿ ይታደጓታል!!
Amerid2000@gmail.com

No comments:

Post a Comment