Tuesday, December 8, 2015

የዘመናችን ሙሴ (ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ)

«ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ» ዕብ 11-24 ታዬ ብርሃኑ ከቨርጂንያ በመጽሐፍ ቅዱስ ካሉ የቅዱሳን ታሪኮች ውስጥ የሙሴን ታሪክ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ እንዳነበበው ስለማምን የሙሴን ታሪክ በዚህ ጽሁፍ ላይ መተረኩ አያስፈልገኝም። ሆኖም የዕብራውያን መልእክት ዕምነት ምን ማለት እንደሆነ የሚያስተምርበትን 11ኛው ምእራፍ ላይ ሌሎች ቅዱሳንን ጨምሮ የሙሴን ታላቅ እምነት ይጠቅሳል። ሙሴ በግብጽ ፈርዖን ቤተ መንግስት ውስጥ ጮማ እየቆረጠ፣ ጠጁን እየተጎነጨ፤ በወርቅና በገንዘብ ተከቦ መኖርን ትቶ በባርነት ከሚሰቃዩት ወገኖቹ ጋር መከራ መቀበልን እንደመረጠ ይተርካል። የንጉሱን ቁጣ ሳይፈራ በጊዜዋ ልዕለ ኃያል ሃገር የነበረችውን የግብፅን አገር ኑሮ ትቶ ከወገኖቹ ጋር የኤርትራን ባህር ተሻግሮ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመሄድ የወሰነው በእምነት ነበር። እምነት ማለት የማይታየውን እንደሚታይ አድርጎ በተስፋ መነጽር ማየት ነው። ባለፉት አራት አስርት ዓመታት የሀገራቸን ኢትዮጵያ ጉዳይ በሁሉም ዘርፍ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሆነ የዓይን ምስክር ነን። ሞት፣ ርሃብ፣ ስደት፣ ጎጠኝነትና የፍትህ እጦት የዘመናችን ታሪክ ነው። ወደድንም ጠላንም በየትኛውም ጎራ ብንቆምም፤ በፍትህ እጦት እየተገደሉ መንገድ ላይ ሬሳቸው ይጣል የነበሩት ወጣቶች፣ ተረሽነው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ የተቀበሩት 60 ሚኔስትሮች፣ አገርን የባህር በር ማሳጣት፣ ድምጻቸው እንዲከበር ሊጠይቁ አደባባይ ሲወጡ በአጋዚ አልሞ ተኳሾች የተገደሉት የእነ ህጻን ነቢዩ ታሪክ የዚህ ትውልድ ታሪክ ነው። በአማራው፣ በኦጋዴንና በአኝዋኩ ላይ የተካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻም የኛ ታሪክ ነው። ለአገር ለምድር እንደ ታቦት የሚከብዱና እድሜ ልካቸውን ቤተክርስቲያናቸውን እና አገራቸውን ያገለገሉት የኦርቶዶክስ ቤ/ክ አ
ባቶች ስደትም የዚህ ትውልድ ታሪክ ነው። ይሄ ትውልድ ይህንን ታሪክ ፈቅዶ አይደለም የሰራው። ጠብመንጃን መከታ ባረጉት በገዢው መንግስት ጫና ምክንያት ነው። ዝምም ብሎ አላየም። ይህንን ታሪክ ለመቀየር ከፕሮፌሰር አስራት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሁሉም በሚችለው ሞክሯል። አብዛኛው የመታሰር፣ ሌላውም የስደትና የሞት ጽዋ ደርሶታል። እስከ አሁን ድረስ የተከፈለው መስዋዕትነት ዘረኛውን የወያኔ መንግስት ሊገረስሰው አልቻለም። ምናልባትም የትግሉ ስልት ሁሉን አቀፍ ወይም ሁሉንም የትግል ተልዕኮ ያላካተተ ስለ ነበር ይሆናል። አሁን ግን ከምስራቁ የአሜሪካ ክፍል የኢትዮጵያውያንን የትግል ተልእኮ በአንድ ላይ አካትቶ፣ የኤርትራን ባህር አሻግሮ፤ ወደ ተስፋይቱ ምድር በመውሰድ የዚህን ትውልድ ታሪክ የሚቀይር ልባምና አስተዋይ መሪ የዘመናችን ሙሴ አግኝተናል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ በተመቻቸ ህይወት ይኖርባት ከነበረው ምድረ አሜሪካ፣ የደለበ ደሞዝ የሚያገኝበትን የፕሮፌሰርነትን ስራ ትቶ በወያኔ የአፓርታይድ መንግስት የሚሰቃዩት ወገኖቹ ነጻ ይወጡ ዘንድ መከራን መረጠ። ከሁሉም በላይ ሞትን ሳይፈራ እንደ ዓይን ብሌን የሚሳሳላቸው ቤተሰቦቹን ትቶ ምትክ የማይገኝለት ህይወቱን ለኢትዮጵያ ሀገሩ ሊሰዋ ወስኖ ወደ ትግል ሜዳ ሄደ። አስከፊ ታሪክ ያለው የዚህ ዘመን ትውልድ የሚያስደስትም ታሪክ አለው። የዘመናችን ሙሴ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የዚህ ትውልድ ታሪክ ነውና። ፕሮፌሰር ብርሃኑ እና የትግል አጋሮቹ ነጻነትን እምነት አርገው የድል ተስፋን ሰንቀው ዱር ቤቴ ብለዋል። እኛስ ምን እያደረግን ነው? ይህችን አጭር ጽሁፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ሰሞኑን የወያኔዎችን ደም ያንተከተከው የፕሮፌሰር ብርሃኑ ለአውሮፓ ፓርላማ የሰጠው የምስክርነት ቃል ነው። ሁላችን እንዳያነውና እንዳነበብነው በርቱዕ አንደበቱ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ኢትዮጵያው ውስጥ ያለውን ችግር ነቅሶ በማውጣት አቅርቦታል። በዚህ ትንታኔው ውስጥ የኔን ትኩረት የሳበውን ኃይለ ሃሳብ መጥቀስ እወዳለሁ። ፕሮፌስር ብርሃኑ ወያኔ በቤተ እምነት ውስጥ ጣልቃ እንደሚገባ አስረድቶ በኦርቶዶክስ ቤ/ክ አባቶች ላይ እስከ መሰደድ ያደረሰውን የወያኔ ጥፋት በአለም አደባባይ ይፋ አርጎታል። በተቃዋሚ የትግል ጎራ ያሉ መሪዎች ስለተሰደደችው ቤ/ክ እና አባቶች ከዚህ በፊት ሲያነሱት አለመስማቴ ሁሌም ያሳዝነኝ ነበር። የተሰደደችው ቤ/ክ ወይም ህጋዊ ሲኖዶስ ሰብዓዊ መብት፣ የህግ የበላይነት እና ፍትህ በምድረ ኢትዮጵያ እንዲከበር ከአውደ ምህረትም እሰክ ዓለም በአደባባይ ድምጻቸውን እያሰሙ የትግሉ አካል ተደርገው አለመወሰዳቸው ይገርመኝ ነበር። ሽማግሌ በሀገሪቷ ስለጠፋ እንጂ ከልጅነት እስከ ሽምግልና ቤተክርስቲያንን ያገለገሉ አባቶች በባእድ አገር ሲሰደዱ እንዴት ዝም ይባላል? ዳሩ ሽምግልና የእንጨት ሽበት የሆነበት  ዘመን ላይ ደርሰናል። እነዚህ አባቶች ስደታቸውን ባርኮ በስደት ያለውን ህዝብ ቢሰበስቡም አያሌ አብያተ ክርስቲያናትን ቢመሰርቱም በየአውሮፕላን ጣቢያ በሽምግልና እድሜአቸው ሻንጣ እየተሸከሙ ህዝባቸውን ለማገልገል ቀና ደፋ ሲሉ ማየት ያቆስላል። የዮሴፍን ስደት የባረከ አምላክ የእነርሱንም ባርኳል። ፕሮፌስር ብርሃኑ ያገኘውን በረከት ቀድሞ የቅንጅት አሁን ደግሞ ህብረ ብሔር ፓርቲ የሆኑት አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ መሪዎች አላገኙትም። ወደፊት የወያኔ መንግስት በሌሎች ቤተ እምነቶች ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ሲያወግዙ ወያኔ በኦርቶዶክስ ቤ/ክ ላይ የፈጸመውን የቀኖና መደፍጠጥ፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተሾመን መንበር ለስደት ማብቃቱን ማውገዝ ይገባቸዋል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለሌሎች ታጋዮች ተምሳሌት ሆኗል። በአንጻሩ በስደት የሚገኙትን አባቶች በተሰደዱበት የባእድ አገር እንኳን በሰላም እንዳይኖሩ ማኃበረ ቅዱሳን የተሃድሶ ታርጋ በመለጠፍ አገልግሎታቸው ላይ እንቅፋት የፈጸመው አፍራሽ ተልዕኮ ያስተዛዝባል። ራሱን የቅዱሳን ማኃበር እያለ የሚያሞካሸው ስብስብ ዳንኤል ክብረት የሚባል የጎበዝ አለቃ ከኢትዮጵያ እየላከ አባ መላኩ ጋር እያረፈ ከአቡነ ማትያስ ጋር በመላው ሰሜን አሜሪካ እየዞረ ህዝቡ ህጋዊውን ሲኖዶስ እንዳይቀበል ያረገው ሙከራ ሊሳካ አልቻለም። ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያናን ለመፈተን ከሰማይ ወደ ምድር ወንድሞችን እና አባቶችን ሊከስ የተወረወረው ዘንዶ ነው። ይሄ አውሬ አሁን በስደት ላይ በምትገኘው ቤተክርስቲያን ስኬት እንደገና ተቆጥቶ ስልቱን ቀይሮ በአዲስ መልክ የስም ማጥፋት ዘመቻውን አጠናክሯል። በፊት ከውጭ ሆኖ ነበር አሁን ግን በህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ካድሬዎቹን አስርገው በማስገባት ምእመናን ለዓመታት በስደት ያገለገሉትን አባቶች በተሃድሶ አራማጅነት እንዲጠራጠር በማድረግ ትጥቁን የማስፈታት ዘመቻ በከፍተኛ ደረጃ እያካሄደ ነው። የማህበረ ቅዱሳን ክፍተኛ አመራር የነበሩት ጠቅልለው ወደ ምድረ አሜሪካን መጥተው የጥፋት ዘመቻውን በግንባር እየመሩት ነው። በስደተኛው ሲኖዶስ ስር የሚገቡት ካህን መስል ጮሌ ካድሬዎች መስቀል ጨብጠው ቀሚሱን አንዘርፍፈው ነው የሚገቡት። በዲሲ ገብርኤል፣ በአትላንታ ቅድስት ማርያምና በቶሮንቶ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ የገቡት ካድሬዎች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። ውሎአቸው ከማህበረ ቅዱሳን ከፍተኛ አመራርና ከአባ መላኩ ጋር ነው። የአትላንታው መነኩሴ (አባ ኃይለሚካኤል) የጥፋት ስራቸው አልሳካ ስላላቸው እዚህ ቨርጂንያ መጥተው ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጋር በመሆን የቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ ብለው በአባ መላኩ ባራኪነት ከፍተው ነበር። ለአንድ ወር ያህል ሞክረው ስላልተሳካላቸው እንደ ኪዮስክ ዘግተውት ተሰናብተው ወደ መጡበት አትላንታ ማርያም ሄደው ዘው ብለው ገብተዋል። ይህ የሚያመላክተው ማኃበረ ቅዱሳን ካድሬ ካህናትን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ሆዳም የቦርድ አባላትን አቅፈው እንደሚንቀሳቀሱ ነው። የአትላንታ ማርያም የባጣህ ቆየኝ አማራጭ ስትሆን ዝም ብሎ የሚያይ የቦርድ አባል ሃላፊነት የማይሰማው ነው። ፕሮፌሰር ብርሃኑና የትግል አጋሮቹ እንደ ሙሴ የተመቻቸ ህይወታቸው ትተው፤ ስለ ፍትህ ስለ ነጻነት በእምነት እምቢ ብለው የድል ተስፋን ሰንቀው የሚመጣውን መከራ ከህዝባቸው ጋር ለመቀበል መርጠዋል። በእግዚአብሔር ድጋፍ ምኒልክ ቤተመንግስት ከተቀመጠው የዘመናችን ፈርዖን ህዝባቸውን ነጻ ለማውጣት የኤርትራን ባህር ሰንጥቀው ሰብዓዊ መብት በሚከበርባት፣ የህግ የበላይነት ወደሚኖርባትና እኩልነት ወደ ሰፈነባት ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደርሱታል። በአሁኑ ሰዓት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የመረጠውን የትግል ስልት ለመተቸት ማንም የሞራል ልእልና የለውም፤ ቢቻል ይከተለው አለዚያም እጁን በአፉ ላይ ያስቀምጥ። ፕሮፌስር ብርሃኑ ይህን ትግል ስልት የመረጠው ወዶ አይደለም። የሰላሙን ትግል ሞክሮና አይቶ ነው። በእስር ቤት ሆኖ እንኳ አሳሪዎቹ ላይ ጥላቻ እንዳይኖረን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት የመሰለ መጽሃፍ ነበር የጻፈልን። ወያኔን ደህና አርጎ ስለሚያውቃቸው፤ በሚያቁት ቋንቋ ሊያናግራቸው እነርሱን አዝሎ የሚኒልክ ቤተመንግስትን ወደ አሳያቸው አካል ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ሊገጥማቸው ሄዷል። በመጨረሻም የአርበኞች ግንቦት 7ትን ትግልን ለሚደግፉ አካላት በሙሉ ፕሮፌስር ብርሃኑ መልእክት አስተላላፏል። ወያኔን በደንብ ስለሚያውቅ፤ የወያኔ ዘመቻ በፓሊቲካ ሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በቤተ እምነትና በማህበራዊ ህይወትም ውስጥ እንደሆነ ጠቁሞናል። እምነትና ፖሊቲካን እንለይ ለምትሉ የዋሆች ወያኔ በሁሉም ዘርፍ እንደገጠመን ከፕሮፌስሩ ትንተና እንማራለን። ወያኔን እየተቃወማችሁ ከእነ አባ መላኩ ጋር አትሞዳመዱ። ቀኖና ጥሶ በጠብመንጃ ኃይል የተሰበሰበ ሲኖዶስ፤ በመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን በወያኔ ርእዮተ ዓለም የሚመራ ቅድስና የሌለውን ሲኖዶስ እንዴት መቀበል ይቻላል? የአባቶቻቸን አምላክ ስሙ እግዚአብሔር ነው እርሱም ተዋጊ ነው እርሱም ድል አድራጊ ነው! ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ የአባቶቻችን አምላክ የተመሰገነ ይሁን - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/48844#sthash.khhZxqIB.dpuf

No comments:

Post a Comment