የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ወደ ወህኒ ከተጋዙት ሙስሊሞች አንዱ የሆነው ኢስታዥ ኑሩ ቱርኪ፣ በዝዋይ ወህኒ ቤት የግድያ ሙከራ የተደረገበት ሃሙስ ሚያዚያ 6 ቀን 2008 ዓም መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።
በህገ-ወጥ የሰው ዝውውር ተወንጅሎ የ12 ዓመታት እስራት የተፈረደበት ግለሰብ የግድያውን ሙከራ ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ በአትክልት መኮትኮቻ መሳሪያ ወይንም ፋስ የኡስታዝ ኑር ቱርኪን አንገት ከመታ በኋላ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ መሬት ላይ ወድቋል። በተኛበት ሆዱ ላይ በድጋሚ ጥቃት ለመሰንዘር የሞከረ ቢሆን፣ በደመ-ነፍስ ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ በመገልበጡ እንደሳተው ለኢሳት የደረሰው ዜና ያብራራል። ኢስታዝ ኑር ቱርኪ አደጋው ከደረሰበት በኋላ ህክምና እንዳያገኝ መደረጉን፣ በኋላ ግን መትረፉ ከተረጋገጠ በኋላ እስረኛው ጉዳዩን በማወቁ ለህክምና ወደዝዋይ ሆስፒታል መወሰዱን ለመረዳት ተችሏል።
ወላጅ አልባ ህጻናት እንዲሁም ጧሪ የሌላቸው አረጋውያንን በመርዳት በበጎ አድራጎት ተግባሩ የሚጠቀሰው ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ፣ ጥቃቱ በተቀነባበረ ሁኔታ እንደተካሄደበትም ተመልክቷል።
ዘወትር ሃሙስ የዝዋይ ማረሚያ ቤት የጽዳት ቀን በመሆኑ፣ የአትክልት መቆፈሪያና መኮትኮቻ መሳሪያዎች የሚወጡበት ቀን ተጠብቆ ድርጊቱ እስረኞች መሃል ሲፈጸም ተቃውሞ ይቀሰቅሳል በሚል የግድያ ሙከራውን ያደረገው ግለሰብ በህሙማን ማገገሚያ ክፍል እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ድርጊቱ መፈጸሙ ታውቋል።
ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ በሳምንቱ ቀናት ከሚገኙበት ዘመዶቹ ሃሙስ ዕለት ሊጠይቁት የመጡትን ጎብኝቶ ሲመለስ በህሙማን ማገገሚያ አካባቢ አድፍጦ የጠበቀው ግለሰብ ድርጊቱን መፈጸሙን የኢሳት የዝዋይ እስር ቤት ምንጮች አብራርተዋል።
ድርጊቱን የፈጸመው የ12 ዓመታት እስራት የተፈረደበት ግለሰብ የአእምሮ በሽተኛ ነው በማለት የወህኒ ቤቱ ሃላፊዎች ከተጠያቂነት ለመሸሽ እየሞከሩ ቢሆን፣ የግድያ ሙከራ ያደረገው ግለሰብ የእዕምሮ ጤና ችግር የሌለበት፣ በእስር ቤት ውስጥ እስረኛውን ለመሰለል ከተመለመሉ አንዱ መሆኑ በእስረኞቹ ዘንድ እንደሚታወቅም ተመልክቷል። በዝዋይ ወህኔ ቤት የአእምሮ በሽተኛ እንደማይታሰር በመግለጽም፣ የወህኔ ቤቱ ሃላፊዎች ምክንያቱ ተቀባይነት የሌለው መሆኑም የኢሳት ምንጮች አብራርተዋል።
በኡስታዝ ኑር ቱርኪ ላይ የግድያ ሙከራው የተቀነባበረው በወህኒ ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይቅርታ እንጠይቅም በማለታቸው በግድያ ከማለቃችሁ በፊት ጠይቃችሁ ውጡ የሚል በቤተሰብና የወዳጅ ግፊት ለማስከተል እንደተቀነባበረ ተምኖበታል።
ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የታሰረው ሙባረክ፣ የደሴ ከተማ ተወላጅ ድንገት በዚሁ ወህኒ ቤት መሞቱንም የኢሳት ምንጮች ያስታውሳሉ። በትኩሳት ህመም ላይ የነበረው ሙባረክ ለምርመራ ወደ ሃኪም ቤት ሲሄድ በሰጡት መርፌ፣ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉን ተገልጿል። በእስር ቤቱ ውስጥ መርዝ ወግተው እንደገደሉት ሁኔታውን የተከታተሉት የኢሳት ምንጮች ያምናሉ።
በነፍስ ማጥፋት በዘረፋና መሰል ከባድ ወንጀል የተፈረደባቸው ግለሰቦች የወህኒ ቤት ሃላሃፊዎች እስረኛውን እንዲሰልሉ እንደመለመሏቸው ሲገለጽ ቆይቷል። በእነዚህ ግለሰቦች አማካኝነት የፖለቲካ የህሊና እስረኞችን ማጥቃት ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ እየተዘወተረ መምጣቱም ታውቋል።
የአንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዚደንት የነበረው አቶ አንዷለም አራጌ በቃሊቲ ወህኒ ቤት በዚህ ሁኔታ መደብደቡ ሲታወስ፣ የኦሮሞ ህዝቡ ኮንግሬስ /ኦህኮ/ አመራር የነበረው አቶ ኦልባና ሌሊሳም በተመሳሳይ ዘርፍ በታሰረ ግለሰብ ድብደባ ተፈጽሞበታል።
መንግስትን በሃይል ለመጣል ተንቀሳቅሳችኋል በሚል የዛሬ 5 አመት በእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ ከታሰሩት ተከሳሾች ውስጥ ኮ/ል ደምሰው አንተነህ እና ኮ/ል ዓለሙ ጌትነት በጥር ወር 2007 በወህኒ ቤቱ ሃላፊዎች በጥይት የተደበደቡ ሲሆን፣ በተለይ ኮ/ል ደምሰው አንተነህ የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ለቤተሰቦቻቸው ሊያመልጡ ሲሉ ነው የተተኮሰባቸው የሚል ምክንያት መስጠታቸው ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment