Tuesday, April 12, 2016

በጅንካ የመከላከያ ሰራዊትና ልዩ ሃይል አባላት ከፍተኛ ቅኝት እያደረጉ ነው



ሚያዚያ ፬( አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት በደቡብ ኦሞ በጅንካ ከተማና አካባቢዋ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከልዩ ሃይል አባላት ጋር በመሆን፣ በተለይ ከምሽቱ 2 ሰአት ጀምሮ በመኪኖች ላይ መትረጊስና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን ደግነው ቅኝት በማድግ ላይ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የወጣቶች ነጻ እንቅስቃሴ የተገደበ ሲሆን፣ ነዋሪዎችም ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ክትትሉ የተጀመረው በአካባቢው ከፍተኛ እውቅና ያላቸው የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማዬሁ መኮንን፣ አቶ አብረሃም ብዙነህ እና አቶ ስለሺ ጌታቸው መጋቢት 17፣ 2008 ዓም መታሰራቸውን ተከትሎና ፓርቲያቸው መሪዎቹና አባሎቹ ካልተፈቱ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡ እነ አቶ አለማየሁ መኮንንን በሽብር ወንጀል ለመክሰስ የተደረገው ሙከራ ፣ ለምስክር የተዘጋጁ ሰዎች በሃሰት አንመሰክርም በማለታቸው ላይሳካ እንደሚችል ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቶአል፡፡ ለምስክርነት በቅድሚያ የታጩት የታሳሪዎች መኖሪያ ሲፈተሸ የነበሩ ስድስት ሰዎች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አቶ መስፍን እርገጤ፣ አቶ ዓሊዬ ይታ፣ እና ወጣት ሃና ‹‹ከታሳሪዎች ቤት ክላሽንኮቭ ጠመንጃና ቦምብ በፍተሻ ሲገኝ አይተናል ›› ብላችሁ ከመሰከራችሁ ‹‹አዋሳ ወስደን ከመዝናናችሁ በተጨማሪ ለመቋቋሚያ የሚሆን ለእያንዳንዳቸው ብር 50 ሺህ፣ ይሰጣችኋል ›› ቢባሉም የሃሰት ምስክርነቱን ኃሳብ ውድቅ ማድረጋቸውን ፣ ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለማወቅ ተችሎአል፡፡ መስካሪዎች ‹‹ ከጂንካ ከተማ ህዝብ ጋር ከምንጋጭ ከነድህነታችን ከህዝብ ጋር መኖር እንፈልጋለን ›› ማለታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ መስካሪዎቹ አዋሳ ለመሄድ ፈቃደኛ ያለመሆናቸውንና የዕለት ሥራቸውን ሰርተው ማደር እንደሚፈልጉ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ሳይሆን አዋሳ በግዳጅ ብንሄድ የተለየ እንደማንመሰክርና እየደረሰብን ያለውን ጫና ለህዝብ በአደባባይ ለማሳወቅ እንገደዳለን ማለታቸው ታውቆአል፡፡ በደቡብ ኦሞ መሬት ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነውን መሬት የወሰዱት የህወሃትና ከህወሃ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን የሚያመለክት ጥናት በወጣ ማግስት እነ አቶ አለማየሁ መታሰራቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወቃል፡፡ መረጃው ከወጣ በሁዋላ የአካባቢው ነዋሪዎች በስፋት እየተነጋገሩበት ሲሆን፣ የዞኑ መስዳደርም ሆነ ክልሉ በጉዳዩ ዙሪያ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ አልሰጡም፡፡

No comments:

Post a Comment