- አመራሩ ከግለ ሒስ ባለፈ ሊመዘን ይገባል ተባለ
- ሠራተኞች በአድርባይነትና ለፖለቲካ አመራሩ ባላቸው ታማኝነት እንደሚመዘኑ ተጠቆመ
በከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ አካባቢ ያለ ወገንተኝነት፣ የቁርጠኝነት ማነስና ኪራይ ሰብሳቢነት ካልተፈታ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ፈታኝ እንደሚሆን፣ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ አስቴር ማሞ ለፓርላማው ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸማ
ቸውን ለፓርላማው ማክሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት የመልካም አስተዳደር ንቅናቄው በተለያየ ደረጃ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው መልካም አስተዳደርን የማስፈን እንቅስቃሴው ለምን እንደሚንከባለልና ከፍተኛ አመራሩ ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ ተጠያቂ የማይሆንበት ምክንያት እንዲገለጽላቸው ጠይቀዋል፡፡
ወ/ሮ አስቴር መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተጀመረው ትግል የሚንከባለልበትና በተለያየ ደረጃ የሚገኝበት ምክንያት፣ በራሱ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሆነ መነሻውም ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የከፍተኛ አመራሩ ደካማነት፣ ቁርጠኛ አለመሆን፣ ውግንና የመሳሰሉት ባህሪያት ንቅናቄውን በግለት ለማስቀጠል እንቅፋት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ የትግራይ ክልል ከ40 ሺሕ በላይ የመንግሥት ሠራተኞችን በማሸጋሸግና ንቅናቄውን በተሻለ እየመራ እንደሚገኝ፣ የአማራ ክልልም 23 ሺሕ የመንግሥት ሠራተኞችን በማሸጋሸግ የተሻለ መሆኑን፣ ደቡብ ክልልና አዲስ አበባ አስተዳደርም በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴውን የጀመረው ዘግይቶ መሆኑን፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በጎ የሚባል ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሠራተኛን በማሰናበትና በማሸጋሸግ የሚመጡ ለውጦች ቢኖሩም ይህንን ማድረጉም አስፈላጊና ተገቢ እንደሆነ ቢታመንም፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን ከሥር መሠረቱ ሊቀርፉት አይችሉም ብለዋል፡፡
‹‹አመራሩ ቁርጠኛ ሆኖ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የበላይነትን እስካልያዘ ድረስ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ጠባብነት፣ ትምክህት፣ የሃይማኖት አክራሪነት እያደናቀፉን መሄዳቸው የማይቀር ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከፍተኛ አመራሩ ለምንድነው ተጠያቂ የማይሆነው የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ ዕርምጃ መወሰዱን ነገር ግን በቂ ላይሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በፖለቲካ አመራሩ ላይ ዕርምጃ የሚወሰደው በሒስና በግለ ሒስ ሥርዓት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ይህ የመመዘኛ ሥርዓት በራሱ ችግር ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹በዕምነት ተቀብሎ በደንብ ሒስ የሚያደርግ አመራር እንዳለ ሁሉ፣ በተለመደው አግባብ በሙሉ ዕምነት ሒስና ግለ ሒስ የማያደርግ አመራር አለ፤›› ብለዋል፡፡
የፖለቲካ አመራሩን በሒስና በግለ ሒስ በመመዘን ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ እስከ ድርጅት አባል ድረስ ዕርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
‹‹ነገር ግን የሒስና ግለ ሒስ ሥርዓት መጠናከር አለበት፡፡ ድክመቱና ጥንካሬው ታይቶ ለቀጣይ ሥራዎቻችን ስኬት ሥራ ላይ መዋል አለበት፤›› ብለዋል፡፡
ወ/ሮ አስቴር ወደ መልካም አስተዳደር ንቅናቄ ሲገባ ለሁሉም አመራር እኩል ዕድል ተሰጥቶ፣ በዚህ ንቅናቄ ውስጥ በሚያመጡት ውጤት ይገምገሙ ተብሎ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ይህንን ወደ ተግባር እንቀይራለን፤›› ብለዋል፡፡
ቤስት ስኮር ካርድ (ቢኤስሲ) በሚባለው መመዘኛ የሠራተኞችን ውጤታማነት መመዘን ቢቻልም፣ የፖለቲካ አመራሩ ዘንድ ሲደርስ ግን ይህ መመዘኛ እንደማይሠራ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ለፖለቲካ አመራሩ ውጤታማነት መመዘኛ ሥርዓት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍም አመራሩ የሚመዘንበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በእስካሁኑ ሒደት የቢኤስሲ የመመዘኛ ሥርዓት በመንግሥት ተቋማት የተጋነነ ውጤት እየታየበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹የውጤት አሰጣጡ አድርባይነት የነገሠበት ነው፡፡ አንዳንዱ የሚለካው በቅርበቱ፣ በኔትወርኩ፣ በዝምድናው ወይም በጓደኝነቱ ነው፡፡ አልፎ አልፎም ለፖለቲካ አመራሩ ባለው ታማኝነት እንደሚመዘንም ገምግመናል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ችግር በሁሉም ተቋማት ውስጥ ይነስም ይብዛም መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment