Friday, April 8, 2016

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮችና ደህንነቶች በዋልድባ ቁጥጥር ሲያደርጉ መሰንበታቸው ታወቀ


መጋቢት ፴( ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የገዳሙ አባቶች እንደገለጹት መጋቢት 27 የተከበረውን የመድሃኒአለም በአል ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮችና ደህንነቶች በገዳሙ በመግባት ቁጥጥርና ክትትል ሲያደርጉ ሰንብተዋል፡፡ ሁሉም ደህንነቶች ትግርኛ ብቻ የሚናገሩ የህወሃት ደህንነቶች መሆናቸውን የሚናገሩት አባቶች፣ ከወልቃይትና ከጎንደር ወደ ገዳሙ የሄዱ ምእመናን ከቤተሚናስ መነኮሳት ጋር ምን አይነት ግንኙነት አላችሁ በማለት ሲያዋክቡዋቸው እና ሲከታሉዋቸው ሰንብተዋል፡፡ የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ያሰጋቸው የህወሃት ደህንነቶች፣ ገዳሙን በተለዬ ሁኔታ ቁጥጥር እያደረጉበት ነው፡፡
ከወልቃይት ፣ ከጠገዴ ፣ ከዳንሻ፣ ሁመራ፣ አርማጭና ቆላ ወገራ በወልቃይት መዘጋ አድርገው ወደ ገዳሙ የሚሄዱ ቤተክርስያን ሳሚዎችን፣ ዛሬማ ወንዝ ላይ በማስቆም ከፍተኛ ፍተሻ ሲያደርባቸው ሰንብቶአል፡፡
በተለይ ማይበልጣ አፋፍ ወይም ውዳሴ ማርያም በተባለው ቦታ እና ሶስት ምእራፍ ላይ ከ200 ያላነሱ ምእመናን በሃወሃት የደህንነት አባላት ፍተሻ ተደርጎባቸው ንብረታቸው በሙሉ እንደተወሰደባቸው አባቶች ለኢሳት ተናግረዋል፡፡ በዚህ አካባቢ ፍተሻ ሲያካሂዱና ዝርፊያ ሲፈጽሙ የሰነበቱት የህወሃት ታጣቂዎች 4 ወንዶችና አንድ ሴት ሲሆኑ፣ ሴቶች የአንገት ሃብላቸው ሳይቀር እየተቆረጠ ተወስዶባቸዋል፡፡
ህወሃት የአካባቢው ህዝብ ተገናኝቶ በወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ እንዳይመክር የቀየሰው ስትራቴጂ መሆኑን የሚገልጹት የአይን እማኞች፣ ገዳሙ ከዚህ ቀደም ከደረሰበት ከፍተኛ ጥቃት በተጨማሪ ከወልቃይት ጥያቄ ጋር በተያያዘም ሌላው የጥቃት ማእከል ሆኖአል፡፡
በአሁኑ ሰአት ህወሃት መላው የትግራይ ህዝብ በወልቃይት ጥያቄ ጉዳይ ከህወሃት ጎን እንዲቆም ቅስቀሳ እያደረገ ሲሆን፣ ህዝቡን ለግጭት የሚያነሳሱና አንዱን ብሄር ጠላት አድርጎ ለማሳየት የሚደረገው ጥረት ህወሃት ከደርግ ጋር በነበረው ጦርነት ወቅት ያደርግ ከነበረው ቅስቀሳ ጋር ተመሳሳይ ነው በማለት ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ፡፡

No comments:

Post a Comment