Friday, April 8, 2016

ቀፎ የሚቀማ ቀፎ ስርዓት ( ሄኖክ የሺጥላ ) Henoke Yeshetlla


ኣሁን ደሞ ከምሁራዊ ወደ ምሬታዊ ትንተና እንግባ ( እባካችሁ እየሳቃችሁ፥ በደንብ እየሳቃችሁ ምን ይታወቃል እነዚህ ሰዎች እኮ በዚህ ከቀጠሉ ሳቃችሁንም ሳታዝመዘግቡ ነው የምትጠቀሙት እና ኣስመዝግቡ ሳይሉን ይቀራል ?)። ለነገሩ እንዲህ ያለው ስርዓት ኣጠገብ መሳቅ በህገ ወጥ መንገድ ካልሆነ እንዴት ይቻላል ። በምን እንሳቅ?! የእንባ ሃገር!
መንግስታችን የሞባይል ቀፎዎች የስርቆት መበራከት እያሳሰበው እንደመጣ እና ለዚህም ሲባል በተጠቃሚዎች እጅ ላይ ያሉ ማናቸውም ኣይነት የስልክ ቀፎዎች ምዝገባ እንደሚካሄድ በተጨማሪም የሚከተለው እንደሚሆን ተናግረዋል “Once this technology is implemented, shops that sell phone apparatus and distributors that have phones in their possession that have entered the country illegally will become useless because they will not work. With regards to the phones that are already in the hands of our customers, we are discussing if they should buy new mobiles while we provide it to them or leave the ones that are already in use and focus on the new phones entering the country,” Andualem Admassie

ጋሽ ኣንዷለም ( የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዋና ስራ ኣስኪያጅ ) እንዳሉት ከሆነ ። ይህ የስልክ ማስመዝገብና ፥ በኢንተርኔት የስልክ ኣገልግሎት የመጠቀም ሂደት በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲውል ከተደረገ በኋላ ፥ ወደ ሃጋሪቷ በህገ ወጥ መንገድ ገብተው በነጋዴዎች እጅ ያሉ ስልኮች ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ይደረጋል ። ከውጭ ሃገር ያለ ቀረጥ የገቡ እና ኣሁን በተጠቃሚዎች እጅ ላይ ያሉትን ስልኮችን በተመሳሳይ ሁናቴ ከጥቅም ውጭ ለማድረግ « ለማካካሻ » ህዝቡ ከኛ ስልክ እንዲገዛ እናድርግ ወይስ ኣሁን በኣገልግሎት ላይ ያሉት ስልኮች ይመዝገቡና ለቀጣይ ቀረጥ ያልተቀረጠባቸው ስልኮች ካገልግሎት ውጭ ይሁኑ የሚለው ጉዳይ ላይ እየተወያየንባቸው ነው ። የሚል መግለጫ « በእንግሊዘኛ» ኣውጥተዋል ። 
ዛሬም ጥያቄ ኣለን

1ኛ ቀረጥ ያልተቀረጠባቸው የስልክ ቀፎዎች የተባሉት ፥ በየት በኩል ነው ከተማ የገቡት ? በቦሌ ኣየር ማረፊያ ያለ ምንም ተቃውሞ እና ፍተሻ እንደፈለጉ ሲገቡ የነበሩ ስልኮች ዛሬ በኣንድ ሌሊት በህገ ወጥ መንገድ የገቡ ስልኮች የተባሉበት ምክንያት ምንድን ነው ?
2ኛ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገራችን የገቡት የስልክ ቀፎዎች ብቻ ናቸው ወይ ? በህገ ወጥ መንገድ ወደ ጋንቤላ ገብተው ኣንድ ካሬ ሜትር መሬት ባንድ ሲጋራ ዋጋ የገዙት የመንግስታችን ኢንቨስተሮችስ እንደ ቀፎዎቹ ካገልግሎት ውጭ የሚሆኑት መቼ ነው ? ሀገራችንን የሚጎዳውስ የቱ ነው ?
3ኛ ስለ ቀፎ ከተነሳ ኣይቀር ፥ በህገ ወጥ መንገድ ከደደቢት በርሃ ቁምጣ ለብሶ ኣራት ኪሎ የገባው የሰው ቀፎስ መቼ ነው ከኣገልግሎት ውጭ የሚሆንልን ? እንደ ኣቶ ኣንዷለም ገለፃ ከሆነ ፥ በነዚህ በህገ ወጥ እና ህገኛ ስልኮች የተጠቀመው ህዝብ ለ ቴሌ ኮም የ 111% ትርፍ ማስገኘት ችሏል ። በዚህ ቀፎ ስርዓት የተመራው ህዝብ ግን «11%» ኣድገት ብቻ ነው ያሳየው ። ይህም ቁጥር መሪዎቻችን የልማት ሰንጠረጁ ላይ በግንባራቸው ወድቀው የጣፉት ( ያተሙት ) እንደሆነ ይነገራል ። ታዲያ ለህዝቡ የሚጠቅመው የስልክ ቀፎው ነው ወይስ ቀፎስ ስርኣት ?
በመጨረሻ
የስልክ ቀፎዎችን የሚሰርቁ ሌቦች እንደተበራከቱ መንግስታችን ገልጦ ፥ ይህንን ጉዳይ ለመቆጣጠር ስልኮች መመዝገብ ኣለባቸው ብሏል ። ምን ማለት ነው ባጭሩ ( በገንዘብህ ገዝተህ የምትጠቀመው ስልክ locked ( የተቆለፈ ስልክ ነው ) ማለት ነው ። ስልክህን ለሌላ ሰው ለማስተላለፍ ብትፈልግ ቴሌ ኮም ማወቅ ይኖርበታል ። ምን ኣገባው ? 
ለምሳሌ እዚህ ኣማሪካን ሃገር የኣፕል ምርት የሆኑ ኮምፒተርችም ሆኑ ስልኮችን ስትጠቀም (Find My Iphone, Mac, etc... ) የሚባል ኣፕሊኬሽን ትጠቀማለህ ። የስልክህን ቀፎ « መቼት ( መቼ የት እና እንዴት » ለማወቅ ይጠቅምሃል ። በተጨማሪ የቀፎው በባለቤቱ « የጠፋብኝ» ሪፖርት እስካላቀረበ ድረስ ባቻ ሳይሆን ቀፎው ካገልግሎት ውጭ እንዲሆንለት እስካልጠየቀ ድረስ ማንም ሰው ቀፎውን ሊጠቀምበት ይችላል ። በኮንትራት የተገኙ ( የተገዙ የስልክ ቀፎዎችን ብቻ ) ፥ ኮንትራት ኣቅራቢው የቀፎው እዳ ሙሉ ለሙሉ እስኪከፈል ድረስ የራሱ ንብረት ስለሆነ ጉዳዩን ተከታትሎ ቀፎውን ካገልግሎት ውጭ የማድረግ ህጋዊ መብት ይኖረዋል ።

የኛ መንግስት ሊያደርግ የፈለገው ግን ከዚህ እጅግ በጣምተቃራኒውን ነው ። ይህ ደሞ የቀፎ ህግ በቀፎዎች እንደወጣ ጉልህ ማሳያ ነው ። ያ ከሆነ ደሞ ፥ እንጠይቃለን እንዲህ ብለን «ቀፎውም ፥ ቀፎ መሪዎቻችንም ይመዝገቡልን!!!» ። እንደውም እንደውም ይሄ (Find Me ) ( ፈልገኝ) የተባለው ኣፕ ከቀፎዎቻችን ይልቅ መሪዎቻችን ላይ ነው ዳወን ሎድ መደረግ ያለበት ። ምክንያቱም በሳውዝ ኣፍሪካ በጎማ እሳት ስንቃጠል የት ነበሩ ? በሊቢያ ስንታረድ የት ነበሩ ? በሱኡዲ ስንዋረድ የት ነበሩ ፥ በግብፅ በርሃ ልባችን ተሰንጥቆ ሲወሰድ የት ነበሩ ? ( Find them !) ( ፈልጋቸውን) ጫንባቸው ። ኣረ እንደውም ፈልጋቸው ስታገኛቸው ኣጥፋቸው! ( ዴሊት!)
ስንደመድም ፥ ሌብነት ያሳሰበው መንግስት ችግሩን ለመፍታት ሌባ መሆንን የመረጠ ይመስላል ። ህዝቡ ከዚህ ወዲያ ለመታገስ ከፈቀደ የራሱ ምርጫ ነው ። እንደ ምርጫ 100 % ( እየሳቅን ሰዎች ! ኣማሪካን ሃገር የሃበሻ የእንግሊዘኛ እጥረት እና እሱን ተከትሎ የሚመጣ ጭንቀት ምንጭ ነው!)
መልካም ኣርብ !

No comments:

Post a Comment