Friday, April 8, 2016

ለኮ/ል አታክልቲ ገ/ሚካዔል ልጅ ማሳከሚያ ከብረታ ብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን 3 ሚሊዮን ወጪ ተደረገ ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2008)


የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለአንድ ባለስልጣን ልጅ ማሳከሚያ ሶስት ሚሊዮን ብር የህዝብ ገንዘብ ወጪ ማድረጉን ለኢሳት የደረሰው ሰነድ ያስረዳል። ኮሮፖሬሽኑ የወጣውን ገንዘብ በስሩ ያሉ ድርጅቶች በመዋጮ እንዲሸፍኑት መመሪያ ተላልፏል።
በብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሰው ሃይል አስተዳደርና ዕቅድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በኮ/ል ፅጌ አለማየሁ ስምና ፊርማ ህዳር 8 ፥ 2005 የተጻፈው ደብዳቤ ለኮ/ል አታክልቲ ገ/ሚካዔል ልጅ ማሳከሚያ የወጣው ወጪ በስሩ ያሉ ድርጅቶች በመዋጮ እንዲሸፍኑት ያዛል። ህክምናው በታይላንድ ባንኮክ መከናወኑንም ያስረዳል።
ጉዳዩ የኮ/ል አታክልቲ ልጅ ተማሪ ዮናስ አታክልቲ ታይላንድ ሄዶ የታከመበትን የህክምና ወጪ ይመለከታል በሚል ርዕስ የወጣው ደብዳቤ የሚከተለውን መልዕክት ይዟል። 
EPPc
የብረታብንረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የህወሃት ታጋዮች በነበሩት መኮንኖች የሚመራ ሲሆን፣ ዋና ዳይሬክተሩም አንጋፋ የህወሃት ታጋይ የነበሩት ብ/ጄኔራል ክንፈ ዳኘው መሆናቸው ይታወቃል።
ኮርፖሬሽኑ ከመንገዶች ባለስልጣን ለዕድሳት ብሎ የወሰደውን 88 ማሽነሪ ለትግራይ ክልል አሳልፎ መስጠቱ በአለም ባንክ ኦዲተሮች መጋለጡ በቅርቡ በሰነድ አስደግፈን መዘገባችን ይታወሳል። የማሽነሪዎች ዋጋም ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ለባለስልጣን ልጆች ማሳከሚያ በመስጠት የህዝብና የሃገር ሃብት በመመዝበር ላይ መሆኑ የብዙዎች ስጋት ሆኗል። በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ-ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀማዕምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ ለልጃቸው ማሳከሚያ በሚል ለአዲስ አበባ አብያተክርስቲያናት ባቀረቡት ጥሪ ከአንድ ደብር ከአንጦጦ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ብቻ 500ሺ ብር እንዲወጣ መወሰኑ ባስነሳው ውዝግብ ጉዳዩ መጋለጡ ይታወሳል።
ፓትሪያርኩ በወሰዱት እርምጃ የማነ ዘመንፈስቅዱስ ከሃላፊነት የተነሱ ቢሆንም፣ የተዋጣውን ገንዘብ በተመለከተ ስለተደረሰው ውሳኔ የታወቀ ነገር የለም።

No comments:

Post a Comment