Sunday, May 1, 2016

ቂሊንጦ የግፍ ዶፍ ማዝነቧን ቀጥላለች ( ዘሪሁን ገሠሠ)


አሁን የምንነጋገረው ስለ ሰብአዊነትና አውሬያዊ የጭካኔ ድርጊት ነው፡፡ ‹‹ሰው›› ስለመሆንና ‹‹ሰው›› የመሆንንም ክብር ስለመገፈፍ፡፡ እኛ ወጉ አይቀርምና ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› በምንባባልባት የፋሲካ ዋዜማ ላይ ከወደቂሊንጦ እስር ቤት ‹‹ፈጣሪ ይማርህ›› መባልንም እንኳ ስለተቀማ፤ አንድ ጀግና የህዝብ ልጅ ስለሚፈፀምበት፤ ከግፍም በላይ ግፍ ከሰቆቃም በላይ ሰቆቃ፤ …….. ሰብአዊነትን ከተላበሰ ፍጡር የማይጠበቅ የጭካኔ ተግባር ሰማሁ፡፡ ህሊናዬ፤ እረፍት አጣ፤ የጣርና የስቃይ ድምፆቹ እየደጋገሙ ከጆሮዬ የሚያቃጭሉ ይመስለኛል፤ ከጨለማው ውስጥ ተዘግቶ፤ በህመም እየተሰቃየ፤ ‹‹ የወገን ያለህ!›› እያለ ሲጣራ የሰማሁም ይመስለኛል፡፡ በግዞት ስቃይን ከሚጎነጩ እልፍ ሰላማዊ የነፃነት ታጋይ ወገኖቻችን፤ የዚህኛው ጀግና ጣር ጎልቶ አስተጋባብኝ፡፡
.
ወጣቱ የግፍና የስቃይ ሰለባ፤ከሰሜን ጎንደር የተገኘው የነፃነት ፈርጥ፤ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር ወጣት አባይ ዘውዱ ይባላል፡፡ በገዢው የኢህአዲግ አንባገነናዊ አገዛዝ በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጭቆናና ግፍ፤ የሚሸከም ህሊና ቢያጣ፤ ‹‹ለሀገሬና ለህዝቤ ነፃነት በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ!›› ብሎ፤ ፈታኙንና እልህ አስጨራሹን ጉዞ፤ በሙሉ ወኔና ጀግንነት ተቀላቀለ፡፡ ይህ ያልተዋጠለትና አስሮ የማይሰለቸው፤ አሳሪው መንግስት፤ አባይ ዘውዱን ፤ ለህዝብ ነፃነት መከበር፤ ስለሚደርስብን ግፍና ጭቆና በአደባባይ ስለሞገተ፤ ሀሳቡን በነፃነት ስለገለፀ ወደማሰቃያው ‹‹ቂሊንጦ›› አወረደው፡፡ ይህ ጀግና ሰላማዊ ታጋይ በግፍ ታስሮ ውድ መስዋትነት እየከፈለ ባለበት መራራ ወቅት፤ ሌላ መራራ እክል ገጠመው፡፡ በእስር ቤት እንዳለ ለጉበትና ጣፊያ እብጠት ተዳረገ፡፡ ‹‹ሲያመጣው አያድርስ›› ነውና ወጣቱ ሀገር ወዳድ የቲቢ በሽታ ተጠቂ መሆኑም ተረጋገጠ፡፡ እነዚህ በሽታዎች ህይወቱን ሊያሳጡት ከጫፍ ደርሰው፤ አካሉ መንምኖ ገፅታው ጠቁሮ፤ የጣር ድምፀት እያሰማ ባለበት ሁኔታ ፤ ጨካኞቹ ፍጡራን የተሟላ ህክምና እንዳያገኝ ማድረጋጨውን ከስፍራው ሄደው ያረጋገጡት የትግል አጋሮቹ ተናግረዋል፡፡ ምን አይነት ጭካኔ ነው? ምን አይነት ኢ-ሰብአዊነትስ ነው?
.
ለፃፉት ህግ እንኳ ተገዢ የማይሆኑት፤ ጨካኞች፤ በእልፍ ወገኖቻችን ላይ የሚፈፅሙት ግፍ፤ ምን ያህል አሰቃቂ እንደሆነ የወጣት አባይ ዘውዱ ወቅታዊ ሁኔታ ማሳያ ነው፡፡ ስልጣንም፤ ሀይልም፤ …… ጅረት ነው፡፡ ነገር ግን የስቃይና የመከራውን መስፈሪያ ከአፍ እስከገደፉ እየሞሉ የሚሰፍሩልን አንባገነኖች፤ ‹‹ በሰፈሩት ቁና፤ …..›› የሚለውን ሀገረኛ ብሂል የዘነጉት ይመስላሉ፡፡ በይቅርታ የማይታበስ፤ በትእግስት የማይታለፍ ግፍ እየፈፀሙብን፤ ከይቅር ባይነት ይልቅ ቂም በቀለኛነትን እያወረሱን ይገኛሉ፡፡ አዎ! ምን ግፉና መከራው ቢበዛ፤የሚከፈለው መራራ መስዋትነት ተከፍሎ ከነፃነት አደባባይ መድረሳችን እሙን ነው፡፡ ወጣት ታጋይ አባይ ዘውዱና መሰል በግፍ የሚሰቃዩ ወገኖቻችንን እየከፈሉት ያለው ውድ መስዋትነት በከንቱ እንዳይቀር ሁላችንም፤ እነሱ የተጓዙበትን የነጻነት ጥርጊያ ተከትለን በመጓዝ የሚፈለገውን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል፡፡ አባይ ዘውዱ ላይ ስለሚፈፀመው ግፍና የተሸለ ህክምና የሚያገኝበት መንገድ እንዲፈጠር፤ ድምፃችንን ከፍ አድርገን እንጮህ ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment