የኢትዮጵያ ወታደሮች ባለፈው ወር ከጋምቤላ ክልል ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን ለማስለቀቅ በድጋሚ ወደ ደቡብ ሱዳን መግባታቸው ተገለጸ።
ወታደሮች በሃገሪቱ የቦማ ግዛት ቢደርሱም የግዛቲቱ ባለስልጣናት ወታደሮቹ የቦማ ግዛትን አልፈው ለመሄድ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ፈቃድ ሳይሰጣቸው መቀረቱን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ የግዛቲቱን ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘግቧል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ተወካዮች ከሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጋር ሲያካሄዱት በነበረው ድርድር ታፈነው ከተወሰዱት ከ100 በላይ ህጻናት መካከል ከግማሽ በታች የሚሆኑት ብቻ መለቀቃቸው ይታወሳል።
ቀሪዎቹ ህጻናት ጉዳይ ዕልባት ባለማግኘንቱም የኢትዮጵያ ወታደሮች ከቀናት በፊት ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትንና እንስሳትን ለማፈላለግ በሚል በቦማ ግዛት በምትገኘው የፒቦር አስተዳደር መስፈራቸው ታውቋል።
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማት የሆኑት አምባሳደር ፍሰሃ ሻወል ወደሃገሪቱ የገቡት የኢትዮጵያ ወታደሮች ታፍነው የተወሰዱት ህጻናት የማፈላለግ ተልዕኮ እንዳላቸው ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ወታደሮቿን በድጋሚ ወደ ደቡብ ሱዳን ያሰማራችው እየተካሄደ የነበረው ድርድር በመቋረጡ ይሁን አይሁን የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ከሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጋር ማካሄድ የጀመረውን ድርድር ተከትሎ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከደቡብ ሱዳን ለቀው መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በድንበር ዙሪያ በመሆን የተለቀቁ ህጻናትን ሲቀበሉ ሰንብተዋል።
የቦማ ግዛት አስታዳደር ሃላፊ የሆኑት ባባ ሜዳን ግዛቱ በቂ ግንዛቤ ተሰጥቶት ህጻናቱን ማፈላለግና መመለስ እንደሚፈልግ ለሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ገልጿል።
በግዛቲቱ የሚገኙት የኢትዮጵያ ወታደሮችም ወደተለያዩ አካባቢዎች በመዝለቅ ፍለጋን ለመጀመር ያደረጉት እንቅስቃሴ በግዛቲቱ ፈቃድ እንዳልተሰጠው ሃላፊው አክለው አስረድተዋል።
በግዛቲቱና በደቡብ ሱዳን ፕሬዜዳንት ሳልባ -ኪር መካከል በተደረሰ ስምምነት መሰረትም የቦማ ግዛት ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን አፈላልጎ ኣንዲመልስ ውሳኔ ተደርሷል ሲሉ ሃላፊው ለወታደሮች ፈቃድ ያልተሰጠበትን ሁኔታ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን ለማስለቀቅ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሃገሪቱን ዘልቀው ከሚገቡ ይልቅ ራሱ አፈላልጎ ቢሰጥ ምርጫው እንደሆነ ሲገልጽ መቆየቱም ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ደቡብ ሱዳን በድጋሚ መግባታቸው ቢገለጽም እስካሁን ድረስ የወሰዱት ወታደራዊ እርምጃ አለመኖሩም ተነግሯል።
በጉዳዩ ዙሪያ የደቡብ ሱዳን መንግስት የሰጠው ይፋዊ ምላሽ የለም።
No comments:
Post a Comment