Wednesday, May 4, 2016

የሕዝብ ማእበልና ሱናሚ በመስቀል አደባባይ (ይገረም አለሙ)

የፊታችን ቅዳሜና እሁድ የሚውሉት ሚያዝያ 29 እና 30 ከአስር ዓመት በፊት በ1997 ዓም በተመሳሳይ ቀናት ነበር የዋሉት፡፡ እነዛ ሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ ይዘው የሚኖሩ ትእይንቶች የታዩባቸው ነበሩ፡፡ በተለይ ሚያዝያ ሰላሳ በዚህ ትውልድ ዳግም ይታያል ተብሎ ለመገመት የማይቻል ትእይንት ነው አሳይቶን ያለፈው፡፡
የምርጫ 97 ዋንኛ ተፎካካሪ የነበረው የአራት ፓርቲዎች ጥምረት ቅንጅት ከድምጽ መስጫው ግንቦት 7/97 እለት አስቀድሞ በሚውለው እሁድ የምርጫ ዘመቻ ማጠናቀቂያ ሕዝባዊ ትእይንት በመስቀል አደባባይ እንደሚያደርግና የትዕይንቱ መሪ ቃልም ለዴሞክራሲ እናዚም/እንዘምር የሚል አንደሆነ ቀደም ብሎ አስታወቀ፡፡ ይህን አንደሰማ ኢህአዴግም ለሚያዝያ 29 ቅዳሜ ፕሮግራም አንዳለው ገለጸ፡፡
የኢህአዴግ ትዕይንት ሕዝብ፤Statement from 9 Ethiopian coalition parties
የፖለቲካ ፉክክር አንድም አስቀድሞ አቅዶ በሚፈጸም ተግባር በልጦ መገኘት፣ ሁለትም የተፎካካሪዎችን እንቅስቃሴ እግር በእግር እየተከተሉ የሚሰሩትን በማየትና የሚናገሩትን በመቅለም አጸፋዊ ተግባር መከወን እንደመሆኑ የቅንጅት የምርጫ ዘመቻ ማጠቃለያ ትእይንተ ሕዝብ ፕሮግራም እንደተሰማ ወይኔ በጥድፊያ ተዘጋጅቶ ለሚያዝያ 29 በመስቀል አደባባይ ጥሪ አደረገ፡፡ በእለቱም በየቀበሌው የተለመደውን የካድሬ ስራ ሰርቶ፤ ንብ የታተመችበትን ካናቴራ አድሎ፣ ራቅ ላሉ ቀበሌዎችም የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አቅርቦ ሰዉን መስቀል አደባባይ አወጣው ወይንም አስወጣው፡፡ በዚህ ሁኔታ አደባባዩ በሕዝብ ተጥለቀለቀ፡፡ አቶ መለስም አይተውት የማያውቁትን የህዝብ ብዛት በአደባባይ ሲያዩ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደወጣ ሳይረዱ በጥይት መከላከያ መስተዋት ጀርባ ሆነው ባሰሙት ንግግር ስሜት ፈንቅሎአቸው ይህ የህዝብ ማእበል ምንም ማጭበርበር ሳያስፈልገው ምርጫውን ማሸነፍ ይችላል አሉ፡፡ በዚህም ድርጅታቸው በምርጫ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ሳይሆን አጭበርብሮ ለማለፍ የተዘጋጀ መሆኑን አጋላጡ፡፡ መሪዎች በአደባባይ የሚያደርጉት ንግግር ተጽፎ የሚሰጣቸው እንዲህ በስሜት ተገፍተው አደጋ የሚያመጣ ነገር እንዳይናገሩ ይመስለኛል፡፡ አቶ መለስ የተነፈሱትን ማናፈስ ስራቸው የሆኑት የመገናኛ ብዙኃንም በመስቀል አደባባይ የህዝብ ማእበል ታየ በማለት እያጋነኑ አቀረቡት፡፡
ይህ በመስቀል አደባባይ የታየውና ማዕበል ተብሎ የተገለጸው የህዝብ ቁጥር ኢህዴጋዊያንን ሲያስፈነድቅ( ለአንድ ቀንም ቢሆን) በአንጻሩ ለቅንጅት አመራሮች ብቻ ሳይሆን ለአባላቱና ለደጋፊዎቹም ትልቅ ጭንቀት ፈጠረ፡፡ የጭንቀቱ ምክንያትም በማግስቱ ሚያዝያ ሰላሳ ቢያንስ ተመጣጣኝ የሆነ የህዝብ ቁጠር ይገኝ ይሆን የሚለው ነበር ፡፡
የቅንጅት ትዕይንተ ሕዝብ
እሁድ ሚያዝያ ሰላሳ ጠዋት ቀይ መስቀል፣ በመስቀል አደባባይ ዝግጅት ነበረው፡፡ የቅንጅት ጥሪ ደግሞ ከሰአት በኋላ ነው፡፡ አምስት ሰአት ተኩል አካባቢ መስቀል አደባባይ ስንደርስ ቀይ መስቀሎች ጓዛቸውን እየጠቀለሉ ሲሆን አደባባዩ በሰው እየተሞላ ነበር፡፡ ሰአት ገና ነው ብለው ወደ አደባባዩ የደረሱት ቅንጅቶች ከጥሪው ቀድሞ የሰዉን መጉረፍ ሲመለከቱ መድረክ የማዘጋጀቱንና የድምጽ መሳሪያ የመዘርጋቱን ሥራ ማጣደፍ ጀመሩ፡፤ ፌዴራል ፖለሶች ደግሞ ጎን ለጎን ተያይዘው በመቆም ሰዉ ወደ መኪና መንገዱ እንዳይገባ ለማደረግ አጥር ሰሩ፡፡ ነገር ግን የሰዉ ቁጥር ሲጨምር ሲያፈገፍጉ በዚህ መልኩ እየተገፉ ሄደው መጨረሻ ክቡር ትሪቡኑ ስር በሚገኘው ምሽጋቸው ውስጥ ተጠቃለው ለመግባት ተገደዱ፡፡ መንገዱ ሙሉ በመሉ በህዝብ ተሟላ፡፡
ወደ መስቀል አደባባይ የሚያደርሱት ስድስቱም መንገዶች በህዝብ ተጨናነቁ፤ከፒያሳ አቅጣጫ የሚመጣው ከፖስታ ቤት፤ከሜክሲኮ አቅጣጫ የሚመጣው ከቡናና ሻይ፤ ከሳሪስ የሚመጣው ከአራተኛ ክፍለ ጦር፤ ከቦሌ የሚመጣው ከፍላሚንጎ፤ ከመገናኛ አቅጣጫ የሚመጣው ከባምብሲ፤ከአራት ኪሉ የሚመጣው ከታላቁ ቤተ መንግሥት ማለፍ አልቻለም፡፡ የቅንጅቶች መድረክ በሕዝብ ተውጣ እንኳን ከሩቅ ከቅርብም የማትታይ ሆነች፡፡ ከመድረክ የሚነገረውም የሚሰማው በመድረኩ ዙሪያ ላሉት ብቻ ሆነ፡፡
ማእበል ለመባል ከበቃው በኢህአዴግ ትእይንተ ሕዝብ ላይ ከተገኘው የህዝብ ብዛት ይህኛው በሁለት ምን አልባትም በሶስት እጥፍ የሚበልጥ በመሆኑ ሱናሚ ተባለ፡፡ በወቅቱ በወያኔ አደገኛ ቦዘኔ ከመባል አልፎ ህግ ወጥቶ እየታደነ ይታሰር የነበረው ወጣት አደገኛ ቦዘኔ ራሱ ወያኔ፤ ወጣቱ ስራ አጥ አንጂ ቦዘኔ አይደለም በማለት በየምርጫ ቅስቀሳ መድረኮች ሲያሰማው የነበረውን መፈክር በአደባባዩ ከማሰማት አልፎ አደገኛ ቦዘኔ ያለመሆኑን ያሳየበትን ተግባር ፈጸመ፡፡ በአደባባዩ የተተከሉ የጌጥ መብራቶች ስስ ከመሆናቸው የተነሳ በቀላላ ሊሰበሩ የሚችሉ ቢሆኑም ወጣቱ ባደረገው ጥንቃቄና መከላከል በዛ የህዝብ መጨናነቅ ውስጥ አንድም ጉዳት ሳይደርስ ቀረ፡፡ የእጅ ስልኮች ወድቀው ተገኝተው ወደ መድረክ ተላለፉ፡፡ ሰልፉ ከተበተነ በኋላ በህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ሲሳፈሩ ራሳቸው ስርአት አስከብረው አንድ ሰው ሳይከፍል አንዳይሳፈር ገንዘብ ያልያዘ ካለ ያልያዛ አንዲከፍልለት እያደረጉ ወጣቶች ኢትዮጵያዊ ጨዋነታቸውንና ህግና ሥርዓት አክባሪነታቸውን በተግባር አሳዩ፡፡ ትናንት ለእንጀራችን ዛሬ ለእምነታችን፤ ትናንት ለካናቴራ ዛሬ ለባንዲራ ወዘተ የሚሉ መፈክሮችም በየቦታው ተሰሙ፡፡ እነዚህ ኢህአዴጋዉያንን በእጅጉ ያበሳጩ እንደነበሩ ለማተዘብ ተችሏል፡፡
የቅንጅቶችም ጭንቀት ለኢህአዴግ የወጣውን ያህል ህዝብ ይወጣልን ይሆን ከሚለው ይህ ሁሉ ሕዝብ በሰላም በየቤቱ ይገባ ይሆን ወደሚል ተለወጠ፡፡ ቢያንስ በጥንቃቄና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ወደየቤቱ እንዲሄድ መልእክት ለማስተላለፍ አለመቻሉ የቅንጅቶችን ጭንቀት እንዳበረታው በመድረኩ እቅራቢያ የነበርን ታዝበናል፡፡ ነገር ግን ፕሮግራሙ አንዳለቀ ከየት መጣ ያልተባለ ዝናም ድንገት ወረደና በተነን፡፡ ከፊሉ መጠለያ ፍለጋ ሲሯሯጥ በተለይ ወጣቱ በቡድን በመሆን እያዜመ ዝናቡ ምንም ሳይመስለው ጉዞውን ቀጠለ፡፡ምሽት ላይ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተለመደውን ተቃራኒ ዜና ሰሩ፡፡ ይህ ደግሞ ህዝቡን ይበልጥ አበሳጨው፡፡
የሀያ ዘጠኙ ትእይንተ ሕዝብና የተሰራው ፕሮፓጋንዳ በሰላሳ ሕዘቡ ነቅሎ አንዲወጣ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ ከሰፈሬ አንድ በእድሜ ጠና ያሉ ሰው ትእይንተ ሕዝቡ ላይ ተገኝተው አንደነበረ ሲያጫውቱኝ፤ የቅንጅቶችን ጥሪ አስቀድሜ ብሰማም የመውጣት እቅድ አልነበረኝም፤ የቅዳሜውን ሰው ሳይ ግን አንዴት እንዲህ ይሆናል አልኩ፤ፕሮፓጋንዳቸው ደግሞ ይበልጥ አበሳጨኝና ለመውጣት ወሰንኩ፡፡ግን ከፖስታ ቤት ማለፍ አልቻልኩም፤ ባየሁት የህዝብ ብዛት ግን በጣም ነው የተደሰትኩት ነበር ያሉኝ፡፡
ዳግም ይታይ ይሆን!
ከዚህ ማእበልና ሱናሜ ከተባለ ተእይንተ ህዝብ ወያኔ በሚገባ መማሩን ተግባሩ ይመሰክራል፡፡ ተቀዋሚው ግን የተማረ አይመስለኝም፡ወያኔ ቅዳሜ ያን ያህል ሕዝብ ወጥቶ አቶ መለስንም ምስጢር አስወጥቶ በማግስቱ በሁለት እጥፍ መውጣቱ በህዝብ ልብ ውስጥ አለመኖሩን እንዲገነዘብ አስችሎታል፡፡ በህዝብ ካልተወደደና ተቀባይነት ከሌለው ደግሞ በህጋዊ አግባብ ፍላጎቱና ማሳካት፣ ወንበሩንም ማስጠበቅ አይቻለውም፡፡ ስለሆነም ህገ ወጥ ህጎችን ማውጣት፣ ማናቸውንም አንቅስቃሴዎች በጠመንጃ ጸጥ ማሰኘት፣ ፓርቲዎች ከቢሮአቸው መግለጫ ማውጣት ያለፈ እንቅስቃሴ አንዳይኖራቸው ማድረግ ወዘተ ስራው ሆነ፡፡
ወያኔ ያን መሰል የሕዝብ እንቅስቃሴ ዳግም በኢትዮጵያ እንዳይኖር ለማድረግ ያስቻለውን ስራ ቢሰራ ከታገለለት ዓላማና ከሥልጣን ወይንም ሞት መርሁ አንጻር ተገቢ ነው፡፡ ተቀዋሚዎች ግን ወያኔ ለሥልጣኔ አስጊ ብሎ የፈራው ይህ የህዝብ ተነሳሽነት አስፈላጊነቱን አምነው አንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችል ስራ ለመስራት አለመቻላቸው ነው እንቆቅልሹ፡፡
በምርጫ 97 ለታየው የህዝብ ተነሳሽነት የሚጠቀሱ እንደየሰው አስተሳሰብ የሚለያዩ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም አንዱ ምክንያት አራት ፓርቲዎች ቅንጅት ፈጥረው አንድ ሆነው መቅረባቸው እና በቅንጅት አመራር ውስጥ ከዛ በፊት ብዙም በፖለቲካው መድረክ ያልታዩ ሰዎች ብቅ ማለታቸውና የህዝቡን አመኔታ ማግኘታቸው መሆኑ ሁሉም ሰው የሚስማማበት ይመስለኛል፡፡
በአንድ ዓላማ ተሳስሮ በልዩነት ተከባብሮ ህብረት ፈጥሮ በአንድ የትግል መስመር ላይ መቆም አንዲህ ተአምራዊ የህዝብ ተነሳሽነት አንደሚፈጥር በተግባር ታይቶ እያለ ለዚህ መሳካት የየግል ፍላጎትን በመክላትና ድብቅ አጀንዳን በማስወገድ መስራት ሲገባ ፖለቲከኞቻችን ከራስ በላይ ማሰብ እየተሳናቸው ትብብር ሊፈጥሩ ቀርቶ የጀመሩትንም እያፈረሱና እየበተኑ ለወያኔ እድሜ ማራዘሚያ መድሀኒት ይሆናሉ፡፡
የፖለቲከኞቻችን ችግር ከዚህም ይዘላል፡፡አለመተባበር ብቻ ሳይሆን መቀናናትም አለ፤ አንዱ የተሻለ መስራት ከቻለና የህዝብ አመኔታና ድጋፍ ካገኘ ሌላው እሱም ሰርቶ ለመታመን ከመጣር ይልቅ ለሚሰራው እንቅፋት ይሆናል፡፡ቅንጅት ሚያዝያ 30/97 ያን ያህል ሰው አደባባይ ስለወጣለት በቅናት ያረሩ በተበለጥን ሰይጣናዊ ስሜት የተቃጠሉ ስሜታቸውን መቆጣጠር እየተሳናቸው ይህን የሚያጋልጡ ቃላት ከአፋቸው ሲያመልጡ እየሰማን ታዝበናል፡፡ ይህን ደግሞ ስም ግዜና ጋዜጦችን እየጠቀሱ ማስረጃ ማቅረብ ቢቻልም ቢያንስ ለዛሬ ጠቀሜታ የለውምና ይቅር፡፡
በአጠቃላይ ሚያዝያ 29 እና 30/97 ያየነው ትእይንት ዳግም ሊታይ መቻሉ አጠራጣሪ ነው፡፡ ይህም የሆነው ወያኔ ሕዝብን አደባባይ ቢያወጣ ወደ ተቃውሞ ተቀይሮ በራሱ ጥሪ ራሱ አንዳይወገዝ ተቃውሞ አንዳይደርስበትና በህዝቡም ዘንድ አዲስ መነሳሳት እንዳይፈጠር ስለሚሰጋ ሲሆን በተቃውሞው ጎራ ደግሞ ያንን ለማድረግ የሚያስችል እቅም ያለው ፓርቲም ሆነ ህብረት ባለመኖሩ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment