“ኲሉ ጻድቅ በጊዜ ርቱዕ” እንዲሉ የአገራችን
ሊቃውንት “በደግ ጊዜ ሁሉ ጻድቅ ነው”። በሰላም ጊዜ ሁሉ ጀግና ነው።
በደግ ዘመን ሁሉ ሃይማኖተኛ ነው። በጥጋብ ዘመን ሁሉ ቸር ነው። በደስታ
ዘመን ሁሉ ወዳጅ ነው። በጤና ዘመን ሁሉ ጓደኛ ነው። ጊዜ ሲገለበጥስ? ስለ
እምነቱ ሰው መከራ በሚቀበልበት ዘመን ሰማዕት ለመሆን የሚፈቅደው
ጥቂት ነው። በጦርነት ወቅት ጀግናው ትንሽ ነው። በረሀብ ዘመን አዛኝ ሰው
ጥቂት ነው። በሐዘን ጊዜ ወዳጅ ማግኘት ከባድ ነው። ጤና ሲርቅ እና በሽታ
ሲመጣ የሚደግፍና ቀና የሚያደርግ ማግኘት ከባድ ነው። ማዕበሉ ይዞህ
ሲነጉድ እጁን የሚያቀብልህ ከየት ታገኛለህ?
ማርክ ትዌይን እንዲህ አለ፦ “In the beginning of a change, the patriot is a scarce man, and
brave, and hated and scorned. When his cause succeeds, the timid join him, for then it costs
nothing to be a patriot” ― (Mark Twain) አፍታትቼ ስተረጉመው “በለውጥና በነውጥ ወቅት፣ አርበኛ ውድ
ነው። አርበኛ ጀግና ነው። ግን ማንም አይወደውም። ሁሉም ፊቱን የሚቋጥርበት ሰው ነው። አርበኛው ያነገበው
ዓላማ ሲሳካ ግን የጠሉት ሁሉ ይከቡታል፤ ከዚያ ወዲያማ አርበኛ መሆን ዋጋ ስለማያስከፍል ሁሉ አርበኛ
ይወዳል፤ አርበኛ ይሆናል” እንደማለት ነው።
አርበኝነት ጀግንነት ነውና አርበኞች በቀላሉ አይገኙም።
ግንባራቸውን ለጥይት፣ ደረታቸውን ለጦር፣ ጀርባቸውን ለግርፋት ያዘጋጁ
ሰዎች አርበኞች ናቸው። ነገር ግን እነርሱ በጥይት አረር ለሚመቱት፣
እነርሱ በጦር ለሚወጉትና ለሚገረፉት ሐሳባቸው ብቻ የሚያስፈራቸው
ብዙዎች ናቸው። አርበኝነት በሐሳብ ደረጃ ቢወደድም በየዘመኑ የነበሩ
አርበኞች ግን ይወደዱ ነበረ ማለት አይቻልም። አርበኛው የሚወደደው
እርሱ የቆመለትና የሞተለት ዓላም ሲሳካ ብቻ ነው። ያን ጊዜ በከንፈር
መጠጣ፣ በዘፈን ድርደራ፣ በመቃብር ሙሾ የሚያመሰግነው አያጣም።
በቁሙ የገፋው ሲሞት ያነሣዋል።
አጼ ቴዎድሮስ እጅግ የተደነቀ ንጉሥ ነው። (ነገሥታት አጼ
ዮሐንስ፣ ምኒልክ ወይም ኃ/ሥላሴ አንቱ ናቸው። ለምን ቴዎድሮስን ብቻ
“አንተ” እንደምንል አላውቅም። ምናልባት ሞገደኛ ስለሆነ ይሆን ወይስ “የኮሶ ሻጭ ልጅ” የሚለውን ተቀብለነው?
ለነገሩ እንኳንስ ቴዎድሮስን እግዜርንም አንተ ስለምንለው በፍቅር ትርጉሙ ወስጄዋለሁ።)
“መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፣
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ” እንበለው እንጂ መጀመሪያውኑ ብቻውን እንዲሞት
ፈርደንበት ነበር። እንግሊዞቹን መርተን መቅደላ ተራራ ግርጌ ያደረስናቸው እኛው ነን። አገር ምድሩን ገዝተን (ዝ
ይጠብቃል) ሰው እንዳይከተለው ያደረግን እኛው ነን። ሲሞት በዘፈን ያሞገስነውም እኛው ነን። “ወንድ ማን እንደ
በላይ” እንበል እንጂ በላይ ዘለቀ መሐል ከተማ ሲሰቀል ማንም አልታደገውም።
“ተሰቀለ ሲሉኝ ዝናሩ ነው ብዬ፣
ተሰቀለ ሲሉኝ ጠመንጃው ነው ብዬ፣
ለካስ በላይ ኖሯል ትልቁ ሰውዬ” ብለን አለቀስን። አበቃ። አምስት ዓመት በዱር በገደሉ የተንከራተቱ
አርበኞች አገራቸውን ነጻ አወጡ። እሰየው። ባንዶቹም ይጸየፉት የነበረውን አርበኝነት አሞገሱ።
“ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፤
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ብለን አዜምን። አርበኞቹ ከነጻነት ማዕዱ ተገለሉ፣ የአብዮት ሰማይ
እስኪደፋባቸው ድረስ ባንዳዎቹ ተሞገሱ። ድሮስ አርበኝነትን ማን ይጠላል፤ አርበኛን እንጂ። አርበኝነትን
እያሞገስን፣ አርበኛውን እያገለልን፣ ለነጻነት የደማውን ትተን ስለ ነጻነት እንዘምራለን።
አርበኝነት የሚጠይቀው ውድ ዋጋ ሕይወትን መገበር ከሆነ ከጥንት እስከዛሬ ይህንን የፈጸሙ አሉ።
ይብዛም ይነስም በአምስት ዓመቱ የጠላት ወረራ ወቅት የተዋደቁት ብቻ በጅምላ ስም “አርበኞች” ይባሉ እንጂ
አርበኝነትና አርበኞች እንደየዘመኑና በየዘመኑ አሉ። የኢትዮጵያ ድንበር የታጠረው በአርበኛ አጥንት ነው። አገሪቱ
“ዳሩ እሳት መሐሉ ገነት” ሆና ከኖረች እሳቱ በበላቸው ሰዎች ደምና አጥንት እንጂ በሌላ በምን ይሆናል።
ከአርበኝነት ሁሉ ዳሩ እሳት በተባለው የጦርነት አውድማ የሚውሉትን እንጂ መሐሉ ገነት በተባለው
ሥፍራ የሚኖሩትን የየዘመናችንን አርበኞች ማስተዋል ችለን ይሆን? የሚከፍሉትን ዋጋስ ማን ይረዳላቸው?
የአርበኛ ኑሮና ሕይወት ምኑ ይማርካል? ሕይወትን ለአደጋ ማጋለጥ፣ ከራስ አልፎ የራስ ወገንን ኑሮ ማናጋት።
አምስት ዓመት በዱር በገል ከመዋጋት ከጣሊያኑ ጋር ወግኖ መኖር አለ አይደል? ዛሬስ ቢሆን ብረት ያነገበውን
ተቃውሞ በማዕከላዊ እስር ቤት ከመንገላታት ገዳዩን ጻድቅ፣ ሌባውን ለጋስ፣ ቀጣፊ ውሸታሙን እውነተኛ አድርጎ
በመናገር መኖር ይቻል የለ?
አርበኝነት ደስ ይላል። የአርበኛ ዕጣ ፈንታ ግን ያስፈራል። ባንዳነት ያሳፍራል ባንዳ መሆን እና የባንዳ
ኑሮ ግን ያስጎመጃል። ባንዳው ራሱ ቢጠየቅ
ባንዳነትን ያወግዛል። ባንዳ ለምን እንደሆነ
ቢጠየቅን ግን ምክንያት አያጣለትም። “ንጉሡ
ራቁታቸውን ናቸው” ከማለት ይልቅ “የንጉሡ
ልብስ ያምራል” የሚለው ቢጠየቅ ውሸታምነትን
ይኮንናል። ለመዋሸቱ ለራሱ ውሸት ግን
ምክንያት አያጣለትም።
ታዲያ አርበኞችን ማን ይወዳል?
መከራን ማን ይናፍቃል። በአርበኝነት ጀምረው
በባንድነት የሚጨርሱ ሰዎችን ታሪክ ልብ ብለን
ካስተዋልን ምክንያቱን እንረዳዋለን። ስለ መብት
መከበር ይጮኹ የነበሩ ተገልብጠው ለመብት
መከበር የሚጮኹትን የሚያስሩ ሲሆኑ
አይተናል። ስለ ነጻነት በመጻፍ ጀምረው አሁን
ነጻነትን የሚገፍፉትን ሰዎች የሚያሞካሹ ሰዎች
እናውቃለን። እነዚህም ቢሆኑ ግን አርበኝነትን
አይጠሉም አርበኛ ግን አይወዱም። በአርበኛው
ውስጥ የራሳቸውን ባንዳነት ያያሉና።
ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኛ መሆን ወይም ከመንግሥት ተቃራኒ የሆነ ፖለቲካ የሚያራምድ ሰው መሆን
አርበኝነት ይጠይቃል። መዘዙን እያየነው ነውና። ጋዜጠኛም ሆነ ፖለቲከኛ ባትሆን ነጻ ሰው መሆንም አርበኝነት
ነው። ኅሊናን ዳኛ አድርጎ መኖር፤ ክፋትን መጥላት፣ ከመልካም ጋር መተባበር፣ ለደሃው ማዘን፣ አገርን መውደድ፣
ያልሰሩበትን ገንዘብ አለመፈለግ፣ ዘረኝነትን መጠየፍ አርበኝነት ነው። ባንዳነት በየዘመኑ አለ ካልን በዚህ ዘመን
ያለው ባንድነት ከሚሞተው ሰው ይልቅ ለገዳዩ ማዘን፣ የአገዳደሉን ትክክለኛነት ለማሳመን ደፋ ቀና ማለት ነው።
ገዳይማ ከሞተው ሰው ሕይወት ይልቅ ለመግደል ስለጠፋው ጥይት መቆርቆሩ የታወቀ ነው።
በዚህ ዘመን ከአስኮ እስከ አሶሳ፣ ከደብረ ዘይት እስከ ሐሮማያ ድምጻቸውን የሚያሰሙ ልጆች
አርበኝነት ያስገርመኛል። አንዲት ወረቀት በጻፉ እጃቸው በካቴና የሚታሰሩት ጦማርያን እና ጋዜጠኞች
የሚከፍሉት ዋጋ ልቤን ይገዛዋል። ብረት ካነገበው ደፋር ነኝ ባይ ይልቅ በፈገግታ አንገታቸውን ደፍተው በየፍርድ
ቤቱ የሚቆሙት ሰዎች ጀግንነት ያስደንቀኛል። ሁለት ጸጉር አብቅሎ ገራፊዎችን ከሚያሰማራው ሽማግሌ ይልቅ
ግርፋቱን ለሚታገሱት ወጣቶች ክብር አለኝ። በብዙ ወንጀል ከተበላሸ አረጋዊነት ይልቅ በንጽሕና የተጌጠ
ወጣትነት ይማርከኛል። "ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቈጠራል፥ ከንፈሩንም የሚቈልፍ 'ባለ አእምሮ ነው'
ይባላል።" (መጽሐፈ ምሳሌ 17፥28) እንዲል እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ ከሚሆኑ “አዋቂዎች” ይልቅ
“ጆሮ ያለው ይስማ” እያሉ በበረሃ የሚጮሁ ሰዎች ያስደንቁኛል።
ይቆየን - ያቆየን
ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ ለሚታተመው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት የተጻፈና በዚያም ላይ ለሕትመት የበቃ
ነው።http://www.ethioreference.com/amharic/arbegnenet.pdf
No comments:
Post a Comment