Friday, May 27, 2016

ኢህአዴግ “ህዝቡን በመልካም አስተዳደር ማወያየታችን አመጽ እንዳይፈጠር አድርጓል” አለ


ግንቦት ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 25ኛ ዓመት የስልጣን ዘመኑን በማክበር ላይ ያለው ኢህአዴግ፣ ከፍተኛ አመራሮቹን ይዞ ግምገማ በማድረግ ላይ ነው። በግምገማው ኢህአዴግ ባለፉት 25 አመታት የተጓዘባቸው መንገዶች እና ያጋጠሙት ችግሮች በነባር አመራሮቹ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላ የኢህአዴግን የርእዮት አለም አቅጣጫ በማብራራት ግንባር ቀደም ሆነው የወጡት በሁዋላም ከጤና ጋር በተያያዘ የመድረክ እንቅስቃሴያቸውን የቀነሱት አቶ በረከት ስምኦን በግምገማው መሪ ተዋናይ ሆነው ወጥተዋል።
በግንባሩ ሊ/መንበር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በተመራው በዚህ ግምገማ አቶ በረከት ያቀረቡት ሪፖርት አወንታዊና አሉታዊ አስተያየቶችን አስተናግዷል። አቶ በረከት “ ኢህአዴግ ህዝቡን በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ማወያየታችንና መድረክ መፍጠራችን ብሶቱን እንዲተነፍስ እና ወደ ተራዘመ አመጽ እንዳያመራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎአል” ብለዋል።
የህዝብ ብሶት ማክሸፊያ ተደርጎ የቀረበውን የመልካም አስተዳደር ተግባቦት ስትራቴጂ የነደፉት አቶ በረከት ስምኦን በኢህአዴግ የምክር ቤት አባላት ውዳሴ ተችሮአቸዋል።
አቶ በረከት ባቀረቡት ግምገማ “ በከፍተኛ ደረጃ ያልተሰበሩ፣ ለወደፊቱ ብቅ ሊሉ የሚችሉና ጠንካራ ክንድ የሚሹ ችግሮች አሉ” ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ መስተዳደር ያለው የመሬት ችግር፣ የቦታና የንብረት አስተዳደር እንዲሁም የህወሃት ነባር አባላት የሃብት ክምችት ማእከል ሆነው መገኘታቸው” የሚሉትን ጠቅሰዋል።
አቶ በረከት ነቀፋቸውን በመቀጠል፣ “በኢህአዴግ ውስጥ ፖለቲካዊ ነጻነት አልተረጋገጠም፣ አሁንም በራሳቸው የሚወስኑ ሚኒስትሮች እና የክልል መስተዳድሮች አልተፈጠሩም”፣ ያሉ ሲሆን፣ በወረዳ ደረጃ በተደረገው የህዝብ የማወያየት እንቅስቃሴ 350 አይነት የኢህአዴግ አመራሮች የፈጠሩዋቸው ችግሮች መነገራቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያክል ጸረ- ዲሞክራሲን መሸከም የማይችል ጫንቃ እንደፈጠረ የሚያሳይና የኢህአዴግን አስቻይ ጸረ-ዲሞክራትነት የሚያረጋገጥ ነው ብለዋል።
“ህዝቡ ግማሹ ትከሻው ቢረገጥም፣ ግማሹን የሚችልበትን ስርዓት ገንብተናል “ ያሉት አቶ በረከት፣ የዚህ አይነቱን ስርዓት አደጋም አስቀምጠዋል። “ ይህ ሃምሳ ሃምሳ የሆነ፣ ሃምሳ የበደል ሃምሳ የካሳ ስርዓት አንድ ፕርሰንት ጨምሮ ወደ በደል ካመራ፣ ስርዓቱን ገደል ይከተዋል” ያሉት አቶ በረከት፣ ነገር ግን ይላሉ “ ህዝቡን በማስተንፈስ ስትራቴጂ ቀጥለን በአንድ ፐርሰንት ልዩነት በደሉን የሚችልበትን ትከሻ ከፈጠርንለት በስልጣን ላይ የመቀጠላችን እድላችን መቶ ፐርሰንት የተሻለ ነው።” ሲሉ ያረጋግጣሉ።
“ከመልካም አስተዳደር ውይይት” በተጨማሪ ህዝባዊ አመጾች እንዲራዘሙ ያደረጉ ምክንያቶችም ተዘርዝረው ቀርበዋል። አንደኛው ምክንያት የኢሳት ታፍኖ ለወራት መቆየት ሲሆን፣ ኢሳትን ያለ የሌለ ሃይላችንን በመጠቀም በጊዜው ታፍኖ እንዲቆይ ባናደርግ ኖሮ በተለይ የኦሮምያ አመጽን ተከትሎ አደጋው ስርዓቱን እስከማጥፋት በተለይም ታማኝ አመራሮችን በማጥፋት ትግሉ ወደ መሃል አገር እንዲስፋፋ የማድረግ እድሉ ከፍተኛ ነበር ተብሎአል።
ሰማያዊ ፓርቲ መከፋፋሉና አመራሩ እርስ በርስ መተማመን እንዳይኖረው መደረጉ እንዲሁም አርበኞች ግንቦት7 ተጠናክሮ ወደ መሃል ሀገር መግባት አለመቻሉ ግንባሩን ከአደጋ መታደጉም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።
አቶ በረከትን በድፍረት መንቀፍ የቻሉት የህወሃት ነባር የአመራር አባል የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ ብቻ ነው። አቶ ስብሃት ለአቶ በረከት ግምገማ በሰጡት አስተያየት “ አንተ የምታቀርበው ሪፖርት ሁሌም ሞት ጠሪ ነው፤ ችግርህ ምንድነው? አንተ ከአመራርነት ለመውጣት የቀረህ ጊዜ አጭር ስለሆነ ነው?” ካሉ በሁዋላ፣ በአንተ ሪፖርት ኢህአዴግን ደርግ ሆኖብኝ ነው ያገኘሁት፤ እኛ ነጻ አውጭዎች እንጅ ጨቋኞች አይደለንም” ብለዋል።
በአቶ ስብሃት የሰላ ትችት የተበሳጩት አቶ በረከት “ አንተን ደስ እንዲልህ ፣ መብራቱ ሲቆም የሚቆም የባቡር ሃዲድ ተሰራ ብዬ ሪፖርት አላቀርብም። ኢህአዴግ ደርግ ሆነ ላልከው አንተ ብለኸዋል። ብትችል የእኔን ሰነዶች እያነበብክ ተቃውሞ ከምታደራጅ፣ ከእኔ የተሻለ ሰነድ መጻፍ ብትችልና ብታቀርብ ጥሩ ነበር። እኔም ከዚህ የስልጣን ዘመን በሁዋላ ብትለምነኝም አታገኘኝም ያውም አንተ ከቆየህ” በማለት ዱላ ቀረሽ ምልልስ አድርገዋል።
ሰብሳቢው አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ፣ “የበረከት የመልካም አስተዳደር ውይይት እቅድና ውጤት ራሳችንን እንድናይ መስታውት ሆኖናል” በማለት አሞግሰው፣ ህዝቡ ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር እንዳያብር አድርጎታል ብለዋል።

No comments:

Post a Comment