አዲስ አድማስ ግንቦት 20 ቀን 2008 ዓ.ም
ባለፉት 25 ዓመታት በዲሞክራሲ ግንባታ፣በሰብአዊ መብት አያያዝና በፍትህ ሥርዓት----የተመዘገቡ ስኬቶችናውድቀቶች እንዴት ይገመገማሉ? ግንቦት 20 ለኢትዮጵያውያን ምን ፈየደላቸው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ
ካሳዬ፤አንጋፋውን የህግ ባለሙያ አቶ አብዱ አሊ ኢጂራን አነጋግራቸዋለች፡፡
እርስዎ ግንቦት 20ን እንዴት ይገልጹታል ?
ግንቦት 20 ትልቅ ቀን ነው፡፡ ትልቅ የሆነው ግን ለውጥ ስለመጣ ሳይሆን ደርግን የመሰለ አፋኝ፣ ጨቋኝ፣ ወንበዴና ወሮበላ መንግስት ስለወደቀ ነው፡፡ ያ ትልቅ ድል ነው፡፡ 17 ዓመት በፈጀ ትግል የተገኘ ድል፡፡ ትግሉ 17 ዓመት የፈጀው በደርግ ግዙፍነት ብቻ ሳይሆን ህዝቡን አሰባስቦ ትግሉን የሚመራ በመጥፋቱ ጭምር ነው፡፡ ከዚህ በላይ ግን የለውም፡፡ ከዚህ በላይም አይደለም፡፡
የግንቦት 20 ትልቁ ፋይዳ፣ደርግን መገላገሉ እንጂ አዲስ ነገር ማምጣቱ አይደለም፡፡ ደርግን ከማስወገድ በላይ ሰፍቶ የሄደ ለውጥ አላሳየንም፡፡
ህዝቡ የደርግን መውደቅ የፈለገው በምትኩ ወይም በደርግ መቃብር ላይ የተሻለ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ነፃነትና ፍትህን አገኛለሁ ብሎ ነው፡፡ ሆኖም በእያንዳንዱ ጉዳዮች ላይ የሚፈለገውን ያህል መራመድ አልተቻለም፡፡
የተሻለ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ፣ ከጎረቤቶቿ ጋር በሰላም የምትኖር አገር መመስረት ነበር ግቡ፡፡ ይህ ሁሉ ተሟልቷል ወይ? ካልሽኝ አንፃራዊ መሟላት አለ፡፡ ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት ያው ነው፡፡
ጦርነቱ ቢያቆምም፣ ጦርነት የሌለበት ሰላምም የሌለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ጉዳያችን ወይም ፋይላችን አሁንም አልተዘጋም፡፡
ህአዴግ ከአምባገነኑ የደርግ ሥርዓት በእጅጉ የተሻለ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይሰማል፡፡ እርስዎ ንጽጽሩን እንዴት ያዩታል?
ኢህአዴግ ሁልጊዜም ራሱን የሚያወዳድረው ከደርግ ጋር ነው፡፡ ይህ በጣም አሳዛኝና አስተዛዛቢ ነገር ነው፡፡ እንዴት አንድ መንግስት፣ 17 ዓመት ሙሉ ከታገለው መንግስት ጋር ራሱን አወዳድሮ፣ እኔ እሻላለሁ ብሎ ይናገራል? እንዴት አንድ መንግስት፣ ራሱን ከኤርትራ መንግስት ጋር አወዳድሮ የተሻልኩ ነኝ ይላል? በእርግጥ ደርግ በመውደቁ ምክንያት ሰላም አለ፡፡ የመን ወይም ሶሪያና ኢራቅ ውስጥ ያለው ችግር እኛ ጋ የለም፡፡
ይህ ግን ደርግ በመውደቁ ምክንያት እንጂ ኢህአዴግ በመምጣቱ ምክንያት የጨመረው ነገር ኖሮ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደውም ደርግ ራሱ ተፈቅዶለት ቢኖር ኖሮ፣አሁን አለም ሁሉ ተቀይሮና ተለዋውጦ ባለበት ሁኔታ፣ ይህን ያህል መራመድ ያቅተዋል ብዬ አላስብም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይህን በመናገሬ ሊበሳጩ፣ ሊናደዱና ሊያብዱ ይችላሉ፤እውነቱ ግን ይሄ ነው፡፡
መንግስት፤ባለፉት 25 ዓመታት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ የሰብአዊ መብት አከባበር፣ የፍትህ ሥርዓት--- ወዘተ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ይናገራል፡፡
ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ከመሻሻል ይልቅ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡ እኒህ የሚቃረኑ አስተያየቶች እንዴት ይታረቃሉ?
ዲሞክራሲ ማለት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ነው፡፡ የሀሳብ ልዩነት በየትም ቦታ ይኖራል፡፡ ይህንን የሀሳብ ልዩነት ማስተናገድ የሚችል ነገር አለን ወይ ነው? ጉዳዩ፡፡ በሀሳብ መለያየት ኢትዮጵያ ውስጥ ሞት ነው፡፡ አንድ ሀሳብ ብቻ ነው የሚራመደው፡፡ የተለያዩ ሃሳቦች የሚፋተጉበት፣ የተለያዩ ሀሳቦች ገበያ ወጥተው በሀሳብ ያሸነፈው የማስተዳደር አቅም የሚያገኝበት ሥርዓት ተገንብቷል ወይ ነው? ጥያቄው፡፡
ዲሞክራሲ ቢባል፣ ምርጫ ቢባል፣ ሀሳብን ከመግለፅ ነፃነት በኋላ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫ የሀሳብ ነፃነትን ጉዝጓዝ ካላደረገ፣ ሰው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ ሊኖረው አይችልም፡፡ ሰዎች ሀሳባቸውን አውጥተው በፓርቲ ተቧድነው፣ በድርጅት ተጣምረው ካልመጡ በስተቀር ሰው አማራጭ አይኖረውም፡፡ ምርጫ ማለት ደግሞ አማራጮች የበዙበት፣ ከአማራጮች መካከል የተሻለው የሚመረጥበት ማለት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም ንግግር (ሀሳብን በነፃነት መግለፅ) ቅድመ ሁኔታው ነው፡፡ ምርጫውንም ምኑንም ጎዶሎ የሚያደርገው የመናገር ችግራችን ነው፡፡ ሀሳብን መግለፅ አለመቻል ችግራችን ነው፡፡ የሀሳብ የሸመታ ገበያው የለንም፡፡
በሚዲያው በኩል የመጣሽ እንደሆነ፣ በ1984 ዓ.ም ግንቦት ላይ የኢህአዴግን ቴፕ የጎረሱት የመንግስት መገናኛ ብዙኃን፣ ዛሬም እሱኑ ጎርሰው ቃላቶቹን ብቻ ቀያይረው ያነበንባሉ፡፡ ሚዲያው አካባቢ ይህንን የመሰለ የተዋረደ ነገር አለ፡፡ ኢህአዴግ በፕሬስ ነፃነት ላይ ከዚህ ያነሰ ጉዳይ ሊያደርግ አይችልም፡፡ መቼም አነበባችሁ፣ፃፋችሁ ብሎ ሊገድል አይችልም፡፡ ነገር ግን ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ ሲገባው አላደረገም፡፡
በፍትህ ነፃነት ላይ ባነሳሽው ጥያቄ፤በቅርቡ ያየሁትን አንድ ጉዳይ ላነሳልሽ እፈልጋለሁ፡፡ በአንድ የግል ጋዜጣ ላይ፤“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት ሥራዬን መስራት አልቻልኩም አለ” የሚል ዘገባ ወጥቶ አይቼአለሁ፡፡
ይኼ አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ አንድ የመንግስት አካል ፍ/ቤቶች ጣልቃ ገቡብኝ ብሎ ሲናገር፤ፍ/ቤት እኮ እንደ ኳስ ጨዋታ ዳኛ ጥፋት ባየ ቁጥር ፊሽካ የሚነፋ አይደለም፡፡ አቤቱታ ሲቀርብለት የሚያይ መ/ቤት ነው፡፡ እና አቤቱታ ለምን ተቀብለው አስተናገዱ፣ ዳኝነት ለምን ሰሙ እየተባለ በመንግስት ደረጃ ለዚያውም አዲስ አበባ መስተዳደርን በሚያህልና ለሌሎች የክልል መስተዳድሮች አርአያ ሆኖ ህግ ሲያወጣ፣ ህጉን ወስደው በሚያወጡበት አገር ላይ፣ የዳኝነት ስልጣን የፍ/ቤቶች ብቻ ነው የሚል ህገ መንግስት ባለበት አገር ላይ፣ ጣልቃ ገቡብን እያሉ መናገር በጣም አሳፋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ያሉትን ችግሮች በቀላሉ ለማሳየት የሚያስችል ነው፡፡
የሰብአዊ መብት አከባበር ላይም ተመሳሳይ ችግሮች ይታዩበታል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባይቀበሉትም የኢህአዴግ መንግስት፤ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞን በአደባባይ የመግለጽ መብት፣ የደርግ መገርሰስን ተከትሎ መረጋገጡን በመጥቀስ፤ከግንቦት 20 ፍሬዎች አንዱ መሆኑን ይናገራል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው ?
ቅድም እንዳልኩሽ ደርግን ከማነፃፀሪያነት ማውጣት አለብን፡፡ በደርግ ዘመን ተቃውሞን በአደባባይ ወጥቶ መግለፅ በጭራሽ የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡
በንጉሱ ዘመን በግልፅ የተፃፈና “ማስፈቀድ ያስፈልጋል; የሚል ህግ አለ፡፡ የአሁኑ ደግሞ ማስፈቀድ አይደለም፤ማሳወቅ ነው ብሎ አሻሽሎታል፡፡ ይህ አይነቱ ወግ ቢኖረውም ከመከልከል ያልተናነሰ ህግ ያለው ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ አደባባይ ወጥቶ ሃሳብን የመግለፅ ጉዳይ የተዘጋ ነገር ሆኗል፡፡
እንኳንስ አደባባይ ወጥቶ ሃሳብን የመግለፅና ተቃውሞን የማሰማት ጉዳይ ይቅርና ኮንሰርት ለማዘጋጀት እንኳን መከራ እየታየ ነው፡፡
ለዚህ እንኳን ፍቃድ መጠየቅና መከልከል የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይህ ተቃውሞን ማሰማት፣ አደባባይ ወጥቶ ሀሳብን በነፃነት መግለፅ የምትይው ጉዳይ የተዘጋ ምዕራፍ ሆኗል፡፡
መንግስት የህዝብን ተቃውሞ መስማት ይገባዋል፡፡ ይህ ደግሞ ህዝቡ መብቱ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን መንግስት ራሱ፤“የህዝቡን ብሶትና ተቃውሞ መስማት ይጠቅመኛል” ብሎ መሆን ነው ያለበት፡፡
ለካስ ከእኔ የጎደለ ነገር አለ፡፡ ለካ እኔ የማላውቀው ጉዳይ አለ፤የሚል ጨዋነት የተሞላበት መንግስት መኖር አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ለችግሮች መላ ለመምታትና ምን ማድረግ ይሻላል ለሚለው ጉዳይ ምላሽ ለማግኘት ይረዳዋል፡፡
ማድመጥና የሰውን ምሬት የማስተጋባት ነገር ካለ፣መፍትሄው በራሱ ይመጣል፡፡ በንጉሰ ነገስቱ ዘመን፣ በሰላማዊ ትግል ጥሩ ሁኔታው ቢቀጥል ኖሮ፣ አሁን ያለውን ነገር የሚያሰፋ የተሻለ ነገር ይመጣ ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡ ደርግ ግን ደርግ ነው፡፡ ደርግን ማወዳደሪያና መለኪያ ማድረግ በጭራሽ አይቻልም፡፡
የአገሪቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል?
እኛ አገር ተቃዋሚ ፓርቲ አለ ወይ? መከራ ነው! ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የህዝብን ፍላጎትና የልብ ትርታ የሚያስተጋቡ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ነፃ ምርጫ ይደረግ ቢባል እንኳን በዚያ ውስጥ ገብቶ፣ አማራጭ ሆኖ የሚሰለፍ ተቃዋሚ የሌለ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የራሳቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ጥፋት ቢኖርበትም የሌላ ወገንም ጥፋት አለበት፡፡
ሰላማዊ ትግልም እኮ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የሙሉ ጊዜ ሥራሽ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ የሚሆን ጊዜ ወስደው፣ ቦታ ሰጥተው፣ የሙሉ ሰዓት ሥራ አድርገው የሚይዙበት ሁኔታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=18252:%E2%80%9C%E1%8C%8D%E1%8A%95%E1%89%A6%E1%89%B5-20%E1%8D%A4%E1%8B%B0%E1%88%AD%E1%8C%8D%E1%8A%95-%E1%8A%A8%E1%88%9B%E1%88%B5%E1%8B%88%E1%8C%88%E1%8B%B5-%E1%8B%A8%E1%8B%98%E1%88%88%E1%88%88-%E1%8D%8B%E1%8B%AD%E1%8B%B3-%E1%8A%A0%E1%88%8B%E1%88%98%E1%8C%A3%E1%88%9D%E2%80%9D
No comments:
Post a Comment