Friday, May 20, 2016

የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ በተካሄደው የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በትንሹ 12 ሰዎች ተገደሉ ኢሳት ዜና (ግንቦት 11 ፥ 2008)


በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ህገወጥ ናቸው የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ በተካሄደው የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በትንሹ 12 ሰዎች ተገደሉ።
የከተማው አስተዳደር በቦሌ አውሮፕላን አየር ማረፊያ ጣቢያ አቅራቢያ በተለምዶ ወረገኑ አካባቢ የተገነቡ በርካታ መኖሪያ ቤቶች በህገወጥ መንገድ የተያዙ ናቸው በማለት የማፍረስ እርምጃን እየወሰደ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ለኢሳት አስረድተዋል።
እነዚሁ የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ ፖሊስ አፍራሽ ግብረ ሃይልን በማቋቋም ከማክሰኞ ጀምሮ እርምጃን እየወሰደ ቢሆንም መኖሪያ ቤታቸው የሚፈርስባቸው ነዋሪዎች ድርጊቱን በመቃወም ተቃውሞን አቅርበዋል።
የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የሃይል እርምጃ በትንሹ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የአይን እማኞች ከሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የገለጹ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ከ10 ሊበልጥ እንደሚችልም ነዋሪዎች አስረድተዋል።
የከተማዋ አስተዳደር በተለያዩ አካባቢዎች ከግንቦት 1988-1997 ዓም ድረስ ለተገነቡ ህገወጥ መኖሪያ ቤቶች ህጋዊ ይዞታን እንደሚሰጥ በማስታወቅ ከዚህ ጊዜ ውጭ የተገነቡ ግንባታዎች እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስታውቀዋል።
ሰሞኑን የመኖሪያ ቤታቸው ህገወጥ ነው ተብሎ እንዲፈርስ የተወሰነባቸው ነዋሪዎች የቤታቸው ግንባታ ህጋዊ
ይሆናል በተባለው ስር የሚካተት እንደሆነ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ይሁንና የከተማው አስተዳደር ለበርካታ አመታት ይኖሩ የነበሩት ነዋሪዎች ይዞታቸው ህገወጥ ነው በማለት የማፍረስ እርምጃን እንደሚወስድ አሳስቧል።
ማክሰኞ መወሰድ በጀመረው በዚሁ የጸጥታ ሃይሎች እርምጃ በትንሹ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ቢገልጹም ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።
በአካባቢው ውጥረት ሰፍኖ እንደሚገኝ የሚናገሩት ነዋሪዎች አሁንም ድረስ ቁጥሩ በርካታ የሆነ የጸጥታ ሃይል እና አፍራሽ ግብረ ሃይል ሰፍሮ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በከተማው አስተዳደር እንዲፈርሱ የተወሰነባቸው የመኖሪያ አካባቢዎች ለባለሃብቶች ሊሰጡ ይችላሉ የሚል ግምት እንዳላቸውም ነዋሪዎቹ በመግለጽ ላይ ሲሆኑ ወደ ሁለት ሺ የሚጠጉ ቤቶች በእርምጃው መፍረሳቸውም ተነግሯል።

No comments:

Post a Comment