ድሮ – ድሮ “ሀገር ማለት መሬት ነው” ይባል ነበር። ቀጠለና “ሀገር ማለት ሰው ነው” የሚለው መጣ። ባለፈው ሳምንት “ሀገር ማለት ትዝታ ነው” የሚል ፅሁፍ በወጣ በማግስቱ “ሀገር ማለት አስተሳሰብ ነው” የሚል ሌላ ፅሁፍ በማህበራዊ ድረገፅ ላይ ተለጥፎ አነበብኩኝ። ነገሩ ገርሞኝ ሌሎች ፅሁፎችን ሳፈላልግ፤ “ሀገር ማለት እናት ናት”፣ “ሀገር ማለት ሕገ-መንግስት ነው”፣ እና አንዳንድ ጭራሽ ግራ የሚያጋቡ ፅሁፎችን አነበብኩኝ። ከዚያ በቀረቡት ፅሁፎች ላይ ከመወሰን ይልቅ ለጥያቄው ትክክለኛና ምሉእ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ መፅሃፍትን አገላበጥኩ። በመጨረሻም፣ በጣም አስገራሚ እውነት ላይ ደረስኩኝ፣ “ሀገር ማለት ነፃነት ነው!” ይህ ፅሁፍ፣ “ሀገር ማለት ምንድነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ዙሪያ ምሉእ የሆነ ፅንሰ-ሃሳብ ያስቀምጣል የሚል እምነት አለኝ።
ወደ ዝርዝር ትንታኔ ለመግባት በቅድሚያ “ሀገር” የሚለውን ቃል ፍቺ እንመልከት። በኣማርኛ “ሀገር/ሃገር/አገር” የሚለው ቃል “በውስጡ ህዝቦች የሚኖሩበት፣ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ያለውና በአንድ መንግስት አስተዳደር ስር የሚገኝ ግዛት” ማለት ነው። በዚህ መሰረት፣ ቃሉ ሦስት መሰረታዊ ነገሮችን የሚያመለክት ሲሆን፣ እነሱም፡- ሰው፣ መሬት እና መንግስት ናቸው። ስለዚህ፣ ሀገር በእነዚህ ሦስት ምሶሶዎች ላይ እንደተገነባ ቤት ነው። ከሰው፥ መሬት፥ ወይም መንግስት አንዱ በሌለበት ሁኔታ የሀገር ህልውና ሊኖር አይችልም። ይህ፣ “ሀገር ማለት ነፃነት ነው!” የሚለው ፅንሰ-ሃሰብ’ም በእነዚህ ሦስት ምሶሶዎች ላይ ማዕከል ያደረገ ነው። ምክንያቱም፣ ሦስቱንም በጋራ አጣምሮ ማየት እስካልተቻለ ድረስ ሃሳቡ ምሉእ ሊሆን አይችልም። እነዚህን በዝርዝር ወደ ማየቱ ከማለፋችን በፊት ግን “ነፃነት ምንድነው?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይኖርብናል።
በአጭሩ፣ “ነፃነት” ማለት ያለ ምንም ውጫዊ ኃይል ወይም አስገዳጅ ሁኔታ (necessity) ነፃ ሆኖ ማሰብ (free thinking) ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ (physical motion) ማድረግ መቻል ነው። ፅንሰ-ሃሳቡን ይበልጥ ለመረዳት እንዲያመቸን “ነፃነት” የሚለውን ቃል ፍቺ በዝርዝር እንመልከት። በእንግሊዘኛ “freedom” የሚለው ቃል ሲተነተን፤ “ነፃ-መሆን፥ ነፃ-መውጣት፣ ነፃ-ሰው፥ ነፃ-የወጣ ሰው፣ ነፃ አሳቢ፣ እንደወደዱት፥ እንደፈለጉትና እንደመረጡት ማድረግ፤ …ነፃ የመንቀሳቀሻ-ቦታ፥ ሙሉ-የመንቀሳቀሻ ቦታ፥ ለመንቀሳቀስ ምቹ የሆነ ቦታ፥ ነፃ መሬት፥ ነፃ-ይዞታ፤ …ከጥገኝነት ነፃ መሆን፥ ራስ-ገዝ፥ የራስ-አመራር፥ ራስን-በራስ ማስተዳደር፣ ጣልቃ-አለመግባት፣ ነፃ-ማውጣት፣…ወዘተ የሚሉትን ፅንሰ-ሃሳቦች ያካትታል። በዚህ መሰረት፣ ነፃነት ከሦስት የተለያዩ አቅጣጫዎች የሚታይ ሲሆን፣ እነሱም፡- የሰው ነፃነት፣ የቦታ/መሬት ነፃነት እና የአስተዳደር ነፃነት ናቸው።
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ “ሀገር” እና “ነፃነት” በሦስት ተመሳሳይ ምሶሶዎች ላይ ማዕከል ያደረጉ ናቸው። “ሀገር ማለት ነፃነት ነው” የሚለው ሃሳብ መነሻ እዚህ ጋር ነው። አንድ ሀገር እንደ ሀገር ለመመስረት ሰው፣ መሬትና መንግስት ሊኖሩ የግድ ነው። ሀገር የሚመሰረትበት መሰረታዊ ምክንያት የዜጎችን በነፃነት የማሰብ፣ ከቦታ-ቦታ የመንቀሳቀስ እና ራስን-በራስ የማስተዳደር መብት ለማረጋገጥ ነው። ከሰው፣ ቦታ እና አስተዳደር አንፃር ከተጠቀሱት መሰረታዊ መብቶች ውስጥ አንዱን አንኳን ማረጋገጥ የተሳነው ማንኛውም ሀገር እንደ ሀገር ህልውናው ያከትማል። ስለዚህ፣ የሀገር ህልውና የተመሰረተው፥ የሚረጋገጠው፤ በሰው፣ ቦታና አስተዳደር ነፃነት ላይ ነው። ስለዚህ፣ የሀገር መነሻ እና መድረሻ ነፃነት ነው። በመሆኑም፣ “ሀገር ማለት ነፃነት ነው!” ለዚህ ደግሞ ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉት።
1ኛ፡- “ሀገር ማለት ሰው ሳይሆን ነፃነት ነው!”
የሰው ልጅ ከሌሎች እንስሳት በተለየ ነባራዊ እውነታን በመገንዘብ፣ የነገሮችን ምንነት እና የምልክቶችን ትርጉም ይረዳል፣ በሃሳቦች መካከል ያለውን ምክንያታዊ ተያያዥነት ይገነዘባል፣ ሃሳቦችን ይፈጥራል፥ ያዳብራል፥ ይለውጣል። በዚህም፣ ሰው በአዕምሮው በማሰብና በመምረጥ ብቻ፣ በራሱ ግንዛቤና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የተለያዩ ተግባራትን መጀመር ወይም መግታት፤ መቀጠል ወይም ማቋረጥ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ችሎታ አለው። በመሆኑም፣ ይህ በምክንያታዊ ግንዛቤ (understanding) ላይ የተመሰረተና በነፃ ፍላጎትና ምርጫ (will) መንቀሳቀስ መቻል የሰው ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። በአጠቃላይ፣ የሰው ልጅ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ለነፃነትና ስለ ነፃነት የሚደረጉ ናቸው። ምክንያቱም፣ እንደ ሊዮ ቶልስቶይ (Leo Tolestoy) አገላለፅ፣ የሰው ልጅ ጥረት፣ ለሕይወት ያለው ስሜት በሙሉ ተፈጥሯዊ ባህሪው የሆነውን ነፃነትን በማሳደግ ላይ የተመሰረተ ነው። …ምክንያቱም፣ ሀብት እና ድህነት፤ መፈለግ እና አለመፈለግ፤ ሃይል እና ተገዢነት፤ ጤና እና በሽታ፤ ባህል እና አላዋቂነት፤ ሥራ እና ምቾት፤ ጥጋብ እና ረሃብ፤ መልካም እና መጥፎ፣ መብትና ግዴታ፣ ….ሁሉም አንፃራዊ የነፃነት ማነስ እና መብዛት ውጤቶች ናቸው።
ድምዳሜ፡- ነፃነት የሰው ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ነገር ግን፣ ሰው ሀገር እንዲሆን በነፃነት የመንቀሳቀስ እና ራስን-በራስ የማስተዳደር መብት ሊኖረው ይገባል። ስለዚህ፣ ሀገር ማለት ሰው ሳይሆን ነፃነት ነው!”
2ኛ፡- ሀገር ማለት መሬት ሳይሆን ነፃነት ነው
ከሌሎች እንስሳት በተለየ፣ የሰው ልጅ እንቅስቃሴ በአካላዊ አፈጣጠሩ ብቻ የተገደበ አይደለም። በመሆኑም፣ ከመሬት በተጨማሪ፣ ሰው እንደ ወፍ በሰማይ ይበራል፣ እንደ ዓሣ በባህር ይቀዝፋል። ስለዚህ፣ ሀገር ከመሬት በተጨማሪ፣ በአየርና በባህር ውስጥ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም፣ “ቦታ” (space) የሚለው መሬት (land) ከሚለው በተሻለ ሃሳቡን ይገልፃል። በዚህ ረገድ፣ ዳንኤል ክብረት “ሀገር ማለት ትዝታ ነው” የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ ለማብራራት ሁለት ቦታዎችን በማሳያነት ተጠቅሞ ነበር። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ባድመ (ባድሜ) ላይ የተከፈለውን መስዋዕትነት በማስታዎስ፣ “ሀገር ማለት ሰው ብቻ ሳይሆን መሬት’ም ጭምር ነው”፣ እንዲሁም በደቡባዊ የምድር ዋልታ የሚገኘውን የአንታርክቲካ (Antarctica) በመጥቀስ፣ “ሰው ከሌለበት መሬት ብቻውን ሀገር አይሆንም” በማለት አስረድቷል። በእርግጥ፣ በድንጋይ ክምር የተሞላችው ባድመ (ባድማ፡-ጠፍ፥ ወና፥ ባዶ ቦታ) እና በበረዶ ክምር የተሞላው አንታርክቲካ ሁለቱም ቋሚ ሰፋሪ፥ ነዋሪ የሌላቸው ባዶ ቦታዎች ናቸው። ሆኖም ግን፣ ለባድመ (ባድሜ) በሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጲያ ዜጎች ሲዋደቁላት፣ ለአንታርክቲካ ሲሆን ግን አንድ’ም ሰው አይደናቀፍም።
በባድመ እና በአንታርክቲካ መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ምንድነው? በሁለቱ ቦታዎች መካከል ያለው ልዩነት፣ ባድመ “ሉኣላዊ” መሬት ሲሆን አንታርክቲካ ግን ሉኣላዊ አለመሆኑ ነው። “ሉኣላዊነት” (Sovereignity) ምሉእ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት ማለት ነው። በዚህ መሰረት፣ “ሉኣላዊ” (Sovereign) ማለት ደግሞ “ነፃ የሆነ መሬት፣ ነፃ የሆነ፥ ምሉእ ስልጣን ያለው ሀገር፥ መንግስት” እንደማለት ነው።ስለዚህ፣ ባድመ ሲወረር የሀገር ሉኣላዊነት የተወረረው። አንታርክቲካ ቢወረር ግን ሉኣላዊ መሬት ስላልሆነ የሚጣስ ነፃነት የለም። በአጠቃላይ፣ አንድ ቦታ (መሬት) ሀገር እንዲሆን በቅድሚያ ሉኣላዊ መሆን አለበት። ሉኣላዊ የሆነ ቦታ ነፃ የሆነ ቦታ ነው። ለአንድ ቦታ ሀገራዊ ፋይዳ የሚኖረው ሉኣላዊ ሲሆን ብቻ ነው።
ድምዳሜ፡- አንድ ቦታ (መሬት) ሀገር እንዲሆን በቅድሚያ ሉኣላዊ መሆን ያለበት ሲሆን ሉኣላዊነት ደግሞ በራሱ ነፃነት ነው። ከሉኣላዊነት በተጨማሪ፣ የሀገር ህልውና የሚረጋገጠው በነፃነት የማሰብና የሥልጣን የበላይነት ሲረጋገጥ ነው። ስለዚህ፣ ሀገር ማለት መሬት ሳይሆን ነፃነት ነው!”
3ኛ፡- “ሀገር ማለት መንግስት ሳይሆን ነፃነት ነው!”
ማንኛውም ዓይነት ተግባር በእራሱ ወይም በአላማው፣ በሁሉም የእንቅስቃሴው ተሳታፊዎች ነፃ-ፍላጎት እና ምርጫ ላይ ተፅዕኖ እስካልፈጠረ ድረስ እንደ ትክክለኛ ተግባር ወይም “መብት” ተደርጎ ይወሰዳል። በተመሳሳይ፣ የተግባራዊ እንቅስቃሴያችን አግባብነት የሚመዘነውም በእኛ እና በሌሎች ሰዎች “ነፃነት” ላይ ከሚኖረው ተፅዕኖ አንፃር ነው። አንድ ሰው አውቆና ፈቅዶ በሚያደርገው አካላዊና ሃሳባዊ እንቅስቃሴ የሚኖረው ነፃነት የሌሎች ሰዎችን ነፃነት እንዳይፃረር ከሚያደርግ ግዴታ ጋር የተጣመረ ነው። ስለዚህ፣ ነፃነት የማድረግ እና ያለማድረግ ምርጫ ሲሆን፣ የሚደረጉ እና የማይደረጉ ተግባራት የሚለዩበትና በአንድነት እንዲፀኑ የሚደረግበት ስረኣት፣ “ሕግ” (law) ያስፈልጋል። ሕግ በሌለበት አንድ ሰው መብትና ግዴታውን መወጣት ቢችል እንኳን ሌሎች ሰዎች እንደ እሱ መብታቸውንና ግዴታቸውን እንዲወጡ ማድረግ/ማስገደድ አይችልም። በመሆኑም፣ ሕግ ለሰዎች መብትን ለማስከበርና ግዴታን ለማስገደድ የሚዘረጋ ሥርዓት ነው።
ሰው ከሰው፣ ሰው ከማህብረሰብ፣ ማህብረሰብ ከማህብረሰብ፣ ማህብረሰብ ከሀገር፣ ሀገር ከሀገር በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ሕጋዊ ሥርዓትን እንዲከተሉ፣ መብትን የመጠበቅ እና ግዴታን የማስገደድ “ስልጣን” የተሰጠው አካል መንግስት ይባላል። የመንግስት ሥልጣን/ኃይል (power) በግልፅ ወይም በውስጥ-ታዋቂነት፣ ለአንድ የተመረጠ “መሪ” የሚተላለፍ የሕዝብ ፈቃድ ሲሆን አንድን ተግባር ለመፈፀም ወይም ለውጥን ለማምጣት የሚያስችል አቅም እና ብቃት ያካተተ ነው። በመሆኑም፣ የመንግስት ሥልጣን የዜጎችን ነፃነት እና የሀገርን ሉኣላዊነት ለማስከበር ከህዝብ የተሰጠ ፍቃድና አቅም ነው።
ድምዳሜ፡- ማንኛውም መንግስት የማስተዳደር ሥልጣኑን በህዝብ ፍቃድና ይሁኝታ መግኘት አለበት። ነገር ግን፣ የመንግስት ሥልጣኑን ተጠቅሞ የዜጎችን በነፃነት የማሰብና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት የሚገድብ ከሆነ ህልውናው ያከትማል። ስለዚህ፣ ሀገር ማለት መንግስት ሳይሆን ነፃነት ነው!
****
ማጣቀሻዎች
1. የኣማርኛ መዝገበ ቃላት፥ የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፥ የካቲት 1993 ዓ.ም
2. Roget M. Peter (1911), Roget’s Thesaurus፡ Thesaurus of English and Words and Phrases, 1911 Edition, Patrick Cassidy
3.John Locke፣ An Essay Concerning Human Understanding
4. Leo Tolestoy, War and Peace
5. Immanuel Kant, the Science of Right
6. Thomas Hobbes, Leviathan
No comments:
Post a Comment