Sunday, April 3, 2016

*የኢህአዴግ አምባገነናዊ ሥርዓት በሕዝቦቻችን ሕይወት፣ መብትና ክብር ላይ እያደረሰ ያለው ወንጀል በመልካም አስተዳደር እጦት ላይ ብቻ ተሳብቦና ተድበስብሶ ሊታለፍ አይችልም!!* (ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ)


በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከዳር እስከ ዳር እየተስፋፉ ያሉት የሕዝብ ምሬቶችና ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መንስኤ
ፀረ ዴሞክራሲው የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ የፈጠረው ብልሹ አስተዳደር መሆኑን ምልአተ-ሕዝቡ ከመራር የሕይወት ልምዱ
እና ተሞክሮዎቹ የተገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ የሕዝቡን ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከፋሽስታዊ ጭካኔ ባልተናነሰ ሁኔታ
የመጨፍለቅ እርምጃ እየወሰደ ያለው የኢህአዴግ መንግሥት፣ የሀገራችንን ችግሮች በመልካም አስተዳደር እጦት ላይ ብቻ
በማሳበብ የሽንገላ መግለጫዎችን እየሰጠ መሆኑን መድረክ በትዝብት እየተከታተለው ይገኛል፡፡

መልካም አስተዳደር አሳጡ የሚላቸውንም ባለስልጣናቱን ከአንዱ ሥልጣን ወደ ሌላ እያሸጋሸጉዋቸው እያየን ነው፡፡ ከዚያም
አልፎ "በተፈጠረው ጉዳትም የፌደራል መንግሥቱ ያዘነ ሲሆን ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ይቅርታ ይጠይቃል" በማለት ሲቀናጡ
ይታያሉ፡፡ በሕዝቡ ላይ ይህን ወንጀል የፈጸመውን ተኩሶ ገዳይ ኃይልም ሆነ አስተዳደራዊ በደል እየፈጸመ ያለውን ሙሰኛ
ለሕግ አቅርቦ ሳያስቀጣ "በይቅርታ" እና "አጥፍተናል" በሚሉ ቃላት የመሸንገል አላማቸው የምዕራቡን ለጋሽ ሀገሮች ቀልብ
ከመሳብ የተወጠነ ከመሆን አያልፍም፡፡ በምዕራቡ አለም አንድ መንግሥት "አጥፍቻለሁ ይቅርታ" እስካለ ድረስ የትልቅነትና
የቅንነት መገለጫ ተደርጎ ስለሚወሰድ የኢህአዴግም ብልሀት ይህንን ክብር ከምዕራቡ ለጋሽ ሀገራት ለመጎናጸፍ በመወጠን
የያዘው ስልት ከመሆን አያልፍም፡፡

ኢህአዴግ መሠረቱ ሕዝባዊ ውክልና የሌለው አምባገንን መንግሥት በመሆኑ የሕዝቡን ምሬትና የተቃውሞ እንቅስቃሴን ከዚህ
በላይ እንደተገለጸው በአገዛዙ በሰፈነው ብልሹ አስተዳደር ላይ ብቻ ለማሳበብ ይሞክራል፡፡ በሌላ አንጻር ደግሞ የሕዝቡን
ሕገመንግሥታዊ፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመጣስና በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በሰላማዊ አግባብ በዚሁ ብልሹ አስተዳደሩ
ላይ ተቃውሞአቸውን የገለጹትን ዜጎች በገፍ እያፈሰ ማሰሩንና ማሰቃየቱን እያባባሰው ይገኛል፡፡ በሀገሪቱ ለሚካሄደው
ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተግባር እየሰጠ ያለው ምላሽም በተቃውሞ እንቅስቃሴው ተሳትፎአል ብሎ የጠረጠራቸውን ዜጎች
ሁሉ ከየመኖሪያ ቤታቸውና ከየሥራ ቦታቸው እያፈሰ ከማሰርና ከማሰቃየት አልፎ፣ እንደደርግ መንግሥት ዘመን እየገደሉ
በየቦታው አስከሬን መጣል ድረስ የደረሰ ሆኖአል፡፡

እንደማስረጃም፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቀርበው መግለጫ ከሰጡ ወዲህ ብቻ በሰላማዊ አግባብ ተቃውሞ ባሰሙትና
በዚህ ተግባርም በተጠረጠሩት ዜጎች ላይ ከተፈጸሙት አፈሳዎችና እስራቶች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ለመድረክ ጽ/ቤት
የደረሰውን መረጃ ለአብነት ያህል ከዚህ በታች እንጠቅሳለን፡፡

1ኛ፡- ከምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሂርናና ዳሮ ላቡ ወረዳዎች-------- 1000
2ኛ፡-ከምዕራብ ወለጋ ዞን ዳሌ ሰዲ ወረዳ ----------------------- 28
3ኛ፡- >> >> ሀዋ ጋላን ወረዳ --------------------- 26
4ኛ፡- >> >> መናሲቡ ወረዳ ---------------------- 39
5ኛ፡- ከሆሮጉዱሩ ዞን ከጃርቴ ወረዳ ------------------------------ 21
6ኛ፡- ከምዕራብ ሸዋ ዞን ከኢልፈታ ወረዳ ------------------------ 41
7ኛ፡- >> >> ከጨሊያ ወረዳ ------------------------- 20
8ኛ፡- >> >> አዳአበረጋ ወረዳ -------------------- 20
9ኛ፡- ከምዕራብ አርሲ ዞን 13 ወረዳዎች --------------------- 1200
10ኛ፡- ከቦረና ዞን ቀርጫ ወረዳ --------------------------------- 150
11ኛ፡- ከቡራዩ ወረዳ --------------------------------------------- 2
12ኛ፡- ከነቀምቴ ከተማና አከባቢው ------------------------------ 80
በድምሩ------------- *2627* *ዜጎች *ከኦሮሚያ
ክልል ብቻ ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው በጠባብ ክፍሎች ውስጥ በመታጎር ስቃይ እየደረሰባቸው ለመሆኑ ለመድረክ ሪፖርት
ተደርጎለታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች ከየሥራ ቦታዎችና ከየመኖሪያ ቤታቸው በገፍ ታፍሰው አብዘኛዎቹም
ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው በማያውቁዋቸው አከባቢዎች ተወስደው የተሳሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሚገኙበትን ሁኔታ ለማወቅ
አስቸጋሪ ሆኖአል፡፡ ከዚህም ሌላ በርካታ ዜጎች "ትፈለጋላችሁ" በሚል መሠረተብስ የማሸበሪያ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት ከቤት
ንብረታቸው ተለይተው ለአሳዛኝ ስዴት ተዳርገው የምርት ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ ተደርገዋል፡፡ አገዛዙ በብልሹ
አስተዳደሩ ላይ በሰላማዊ አግባብ ተቃውሞ በማሰማታቸው የታሰሩትንና በተለያዩ እስር ቤቶች ታጉረው የሚገኙትን
የኦፌኮ/መድረክ የአመራር አባላት፣ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም በአገዛዙ ላይ ምሬታቸውንና ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ
የተንቀሳቀሱ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ዜጎችን ከእስር በመፍታት ረገድ አንዳችም ተጨባጭ እርምጃ ሳይወስድና በአገዛዙ
በግፍ ለተገደሉ ዜጎችም ኃላፊነት ወስዶ ተጠያቂዎችን ለሕግ ሳያቀርብ፣ አሁንም ተቃውሞ አሰምታችኋል ባላቸው ዜጎች ላይ
ሕገ ወጥ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ የሕግ የበላይነት የሌለበት ሥርዓተ መንግሥት መሆኑን ግልጽ ያደርገዋል፡፡

አምባገነኑ የኢህአዴግ ሥርዓት ሕዝባችንን አፍኖ ለመግዛት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች መካከል፣ የመድረክ አባላትንና የበታች
አመራር አካላትን ሕገ ወጥ በሆነ አግባብ ደጋግሞ እያሰረና እየደበደበ ዋስ አስጠርቶ በመፍታት እንደዚሁም የተለያዩ
መንግሥታዊ አገልግሎቶችንና ሰብአዊ ዕርዳታዎችን እንዳያገኙ በመከልከል ስነልቦናዊ ጫና መፍጠርና ለተለያዩ ችግሮች መዳረግ
አንዱ ስልት ነው፡፡ በዚህ ስልቱም በዕለት ከዕለት የኑሮ ውጣውረድ ተጠምዶ ያለውንም ዜጋ ሁሉ በፖለቲካ አቋሙና
በሚያነሳቸው ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎች ምክንያት በደል እያደረሰ ይገኛል፡፡ የዚህ አይነት ጥቃቶች እየደረሱባቸው ካሉት
አከባቢዎች መካከል በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የከፋ ሸካ ዞን፣ የጋሞ ጎፋ ዞን፣ የሰገን አከባቢ ሕዝቦች
ዞን ውስጥ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማሕበረ ዴሞክራሲ-ደቡብ ሕብረት አንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከዚህም ሌላ በካፋ ዞን በቦንጋ ከተማ የነበረው የኢማዴ-ደህአፓ ቅ/ጽ/ቤት በአሁኑ ወቅት በዞኑ ፖሊሶችና የመንግሥት
ባለሥልጣናት እንዲዘጋ ተደርጎ ይገኛል፡፡ እንደዚሁም ለልማት እየተባለ በመንግሥትና የሙስና አጋሮቹ በሚካሄደው የመሬት
ነጠቃ ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎች ላይ እስራትና ግዲያ ጭምር ከተፈጸመባቸው መካከል የቤንች ማጂ ዞን፣ የደቡብ ኦሞና
የጋምቤላ ሕዝቦች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንደዚሁም የኮንሶ ወረዳ ሕዝብ ላነሳው ሰላማዊ ሕገመንግሥታዊ ጥያቄ የኃይል እርምጃ
ምላሽ መሰጠቱም የሚታወስ ነው፡፡ በተጨማሪም በድርቅ ምክንያት ምርት ጠፍቶ ለረሃብ ጥቃት ተዳረገ የተባለለት ሕዝብ
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆኑ እየታወቀም የኢህአዴግ የንግድ ተቋማት ሀብት የሆነውን የማዳበሪያ ዕዳ ካልከፈላችሁ በማለት
ሕዝቡን በእስራትና ንብረቱን በመውረስ ማወክብ በመላው ሀገሪቱ ተስፋፍቶ የሚገኝ ሲሆን ለአብነት ያሕልም በሀዲያ ዞን
የሌሞ፣ አንሌሞ፣ ሶሮ፣ ጎምቦራ፣ ዱናና በባድዋቾ ወረዳዎች በሚኖሩ የኢትዮጵያ ማሕበረ ዴሞክራሲ- ደቡብ ሕብረት አንድነት
ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የከፋ ወከባ እየፈጸመባቸው ይገኛል፡፡

እንደዚሁም የመድረክ አባል የሆነውን የአረና ትግራይ የአመራር አባላትን አስረው ማስፈራራታቸው፣ ማዋከባቸውና የፓርቲውንም
ድርጅታዊ ሥራ ለማደናቀፍና በሰበብ አስባቡ ሕልውናውን ለመፈታተን በምርጫ ቦርድ አማካይነት በቅርቡ እየተፈጸሙ ያሉት
ድርጊቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከዚህም ሌላ የመድረክ አባል የሆነው የሲዳማ አርነት ንቅንቄ አመራር አባላት የሆኑት፡-
1ኛ፡- አቶ ደሳለኝ መሳ፣ 2ኛ፡- አቶ ተሾመ ደበበ፣ 3ኛ፡- አቶ ደዋሳ ዳሳ፣ 4ኛ፡- አቶ ሹራ ቻቻራ 5ኛ፡- አቶ ግሼ
አማዶ ከየሥራ ቦታቸው ተይዘው ሕዝባዊ የተቃው እንቅስቃሴ ያነሳሳሉ በሚል መሠረተብስ ስጋት በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ
ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላዩም፣ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በአንድ በኩል እስከ አሁን በፈጸማቸው ወንጀሎች የተጸጸተና ያዘነ ለመምሰል አስመሳይ
መግለጫዎችን እየሰጠ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብልሹ አስተዳደሩን የተቃወሙትን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንም ሆነ ሌሎች ዜጎችን
በገፍ እያሰረ ማንገላታቱን በተግባር እያባባሰው ይገኛል፡፡

ስለሆነም እነዚህ ከተግባሩ ጋር የሚቃረኑ መግለጫዎቹ ሕዝቡን ግራ በማጋባት ውዥንብር ውስጥ ከመክተትና ችግሩንም
ከማወሳሰብ ውጭ ለሀገራችን ወቅታዊና ዘላቂ ችግሮች መፍትሔ ሊሆኑ ስለማይችሉ፣ በማስመሰያ መግለጫዎች ሕዝቡን ለመሸንገል
የሚያደርገውን ፋይዳብስ ሙከራ አቁሞ፡-

1ኛ፡- ኢህአዴግ በአደባባይ ባመነበት ብልሹ አስተዳደሩ ላይ በሰላማዊ አግባብ ተቃውሞአቸውን በማሰማታቸው ምክንያት በገፍ
ያሰራቸውን አባሎቻችንንና ደጋፊዎቻችንን እንደዚሁም ሌሎች ሰላማዊ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈታቸው እንጠይቃለን፡፡

2ኛ፡- በሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተሳተፉትን ዜጎች በግፍ የገደሉት ወንጀለኞች በገለልተኛ አጣሪ አካል ተጣርቶ
ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡

3ኛ፡- በብልሹ አስተዳደራቸው ምክንያት በሕዝቡና በንብረቱ ላይ ለደረሰው ጉዳት የኢህአዴግ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ
ለተጎጂዎቹና ለቤተሰባቻቸው ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል እንጠይቃለን፡፡

4ኛ፡- የሕዝቦቻችን ሕገመንግሥታዊ፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረውና መልካም አስተዳደር ሰፍኖ፣ ሀገራችን ወደ
ሁለንተናዊ የልማት ጎዳና እንዲታመራ ለማብቃት፣ ኢህአዴግ ከመድረክና ሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የፖለቲካ
ምህዳሩን ነፃ፣ ፍትሐዊና ታአማኒ ለማድረግ በአስቸኳይ እንዲደራደር በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም፣ ኢህአዴግ ፋይዳቢስ ባዶ የቃላት ሽንገላዎችን አቁሞ ከላይ የተጠቀሱትን ተጨባጭ የሆኑ የእርምት እርምጃዎች
በመውሰድ የሕዝባችንን መብቶች እንዲያከብርና ሀገራችንን ከገባችበት የፖለቲካ አዘቅት ለማውጣት፣ ወደ ድርድር መድረክ
እንዲመጣ መላው ሕዝባችንና ሰላም ወዳዱ የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ሁሉ የየበኩላቸውን ጫናዎች በኢህአዴግ ላይ እንዲያሳርፉ
ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ድል ለሕዝባዊ ትግላችን!!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ
መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment