Wednesday, April 6, 2016

የወተት ማብራሪያ - ስለ ጦር ሠራዊት ብዛት Tadesse Biru Kersmo


“ጦር ሠራዊት ለለውጥ” በተሰኘው የወተት መልዕክት ላይ ያለ አግባብ “የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት” እየተባለ ስለሚጠራው ጦር የሠራዊት ብዛት የሰጠሁት ቁጥር አንሷል የሚሉ በርካታ አስተያየቶች ደርሰውኛል። ይህን የገመትኩት ስለነበር አልገረመኝም።
በቁጥር ጉዳይ ለመናገር ብዙም ፍላጎት ባይኖረኝም (1) ዝም ብዬ ቁጥር ያልጠራሁ መሆኔን ለማሳየት፤ (2) ህወሓት በቁጥሮች ምን ያህል እንደሚያጭብሩንና እኛም ሳንጠራጠር እየተቀበልናቸው ስለመሆኑ አንድ ተጨማሪ ማስረጃ ስለሚሆነኝ፤ እና (3) የህወሓት ጄኔራሎች አንድ የዘረፋ በር ለማሳየት ስል ይህችን አጭር ማብራሪያ አቀርባለሁ።
አሁን ያለውን ጦር በአራት እዞች (ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ምዕራብ እና ደቡብ ምስራቅ)፣ በአየር ኃይል፣ በአጋዚ ኮማንዶና ልዩ ኃይሎች ጠ/መምሪያ እና በሌሎች መምሪያዎች የተዋቀረ ነው። አራቱ እዞች 18 ክፍለ ጦሮች አሏቸው፤ ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ እግረኛ ክፍለ ጦሮች ሲሆኑ 6ቱ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሮች ናቸው።
ከፍተኛውን ቁጥር ወስደን ብናሰላው የሚከተለውን እናገኛለን። 
የ12ቱ እግረኛ ክፍለ ጦሮች የሰው ብዛት (12 X 6,000) 72,000፤ የ 6ቱ ሜካናይዝድ ክፍለጦሮች (6 X 3,500) 21, 000፤ አግአዚ ኮማንዶና ልዩ ኃይሎች 10,000፤ አየር ኃይል 3, 500 (በቀጥታ ከአየር ኃይል ውጊያ ጋር የተገናኙ መኮንኖች ብዛት 1,200 ነው)፤ በዋና መሥሪያ ቤትና ልዩ ልዩ መምሪያዎች ውስጥ ድጋፍ ሰጪዎች 15, 000፤ በየማሰልጠኛዎች ያሉ አሰልጣኖችና ድጋፍ ሰጪዎች 10,000 እና የውጊያ ምህንድስና ክፍለ ጦር አባላት 2000 ናቸው። የእነዚህ ሁሉ ጠቅላላ ድምር 133,500 ነው። ጠንቃቃ ለመሆን ብዬ ነው በቀደመው ጽሁፌ 140,000 ያልኩት።

ይህ ስሌት በቅርቡ ከሁርሶና ከብር ሸለቆ የወጡትን አዳዲስ ምልምል ወታደሮችን ያካትታል። “ሰላም አስከባሪዎች” ከየክፍለጦሩ ተውጣጥተው ነው የሚላኩት፤ ወደ “እናት” ክፍላቸው ይመለሳሉ፤ ስለዚህ ይህ ስሌት እነሱንም ታሳቢ ያደረገ ነው።
ከዚህ አጭር ማስታወሻ የምንረዳቸው ሁለት ሀቆች አሉ። (1) የኢኮኖሚ እድገትን ጨምሮ የህወሓት የውሸት ቁጥሮች አዕምሮዓችን ውስጥ እየተቀመጡ መሆኑን፤ (2) የህወሓት አንዱ ጉልበት የሌለ ኃይል ያለው የሚያስመስል መሆኑ፤ እና (3) ከ100,000 ሺህ ያላነሰ የሌለ ሠራዊት ደመወዝ ወጪ እየተደረገ ጄኔራሎች ኪስ የሚገባ መሆኑን ነው (ሚኒስትሩ 200,000 ሠራዊት እንዳለ ለፓርላማ ሪፓርት ማቅረቡ ልብ ይሏል!)።

No comments:

Post a Comment