አቃቤ ህግ በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮነን መዝገብ 6 ምስክሮችን አሰማ
• ‹‹አቃቤ ህግ አዛዥ ናዛዥ ሆኗል›› ጠበቃው
• ‹‹አርበኛው ግንባር የሚገኘው ሻዕቢያ ነው›› ምስክር
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የፌደራል አቃቤ ህግ ዛሬ ጳግሜ 3/2007 ዓ.ም በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ ስር የሚገኙ 6ኛ ተከሳሽ ወርቅዬ ምስጋናው፣ 7ኛ ተከሳሽ አማረ መስፍን፣ 9ኛ ተከሳሽ ቢሆነኝ አለነ እና 12ኛ ተከሳሽ አትርሳው አስቻለው ላይ 6 ምስክሮችን አሰምቷል፡፡ አቃቤ ህግ በዛሬው ዕለት 13 ምስክሮችን ያቀረበ ቢሆንም ሁሉንም ሳያስመሰክር ቀርቷል፡፡ ሌሎች 7 ምስክሮች እንዳሉት ቢገልፅም ‹‹ገና ከጎንደር የሚመጡ ስለሆነና ምን እንደሚሉ ስለማናውቅ ማቅረብ አልቻልንም›› በሚል ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ 13ቱንም ምስክሮች ማን ላይ ምስክርነት እንደሚሰጡ ባለመመደቡ ጠበቃዎቹ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ አቃቤ ህግ 13ቱ ምስክሮች መካከል ማን ላይ መመስከር እንዳለባቸው የመደባቸው 6ቱ ብቻ በመሆናቸው ሌሎቹን ከሰዓት እንዲያስመሰክር በጠበቃዎቹ ቢጠየቅም ሳያስመሰክር ቀርቷል፡፡
በችሎቱ መርማሪዎቹ የተገኙ በመሆኑ ተከሳሾቹ በመቆም ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡ ከተከሳሾቹ መካከል 15ኛ ተከሳሽ አቶ አግባው ሰጠኝ ‹‹ማዕከላዊ ውስጥ ማንነታችን ሲያዋርዱና ሲገርፉን የነበሩት መርማሪዎች በዚህ ችሎት መገኘት የለባቸውም›› ሲል ተቃውሟል፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቃዎችም መርማሪዎቹ በችሎት መገኘታቸው ደንበኞቻቸውንና ምስክሮች ላይ የስነ ልቦና ጫና እንደሚፈጥሩ በመግለፅ ከችሎቱ እንዲወጡ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ቅሬታውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
በ12ኛ ተከሳሽ አቶ አትርሳው አስቻለው ላይ የመሰከረው 1ኛ ምስክር ተከሳሹ ለየትኛው ቡድን እንደመለመለው ሲጠየቅ ‹‹ለአርበኛው ግንባር፣ ለአርበኛው ግንባር ግንቦት ሰባት፣ ለግንቦት ሰባት፣ አርበኛው ግንባር ለግንቦት ሰባት›› ሲል የተለያዩ ስሞችን ተናግሯል፡፡ በተመሳሳይ 2ኛ ምስክር ተከሳሹ ለየትኛው ቡድን እንደመለመለው ሲጠየቅ ‹‹ለኤርትራ መንግስት›› ብሏል፡፡ ወደ ኤርትራ እንዲሄድ የተጠየቀበትን ምክንያትም ምን እንደነበር ሲጠየቅ ‹‹ኤርትራ ውስጥ የተሻሻለና ዴሞክራሲያዊ መንግስት አለ ተብለን ነው፡፡ ተመልሰን ይህን መንግስት እንድጥል ነው፡፡›› ሲል መስክሯል፡፡ ሁለቱም ምስክሮች ተመለመልንበት ያሉትን ቀን፣ ጊዜና፣ ተደዋወልንባቸው ያሏቸውን ስልኮችና ሌሎች ዝርዝር ጥያቄዎች ‹‹አናስታውሳቸውም›› ብለው አልፈዋቸዋል፡፡
በተመሳሳይ 12ኛ ተከሳሽ ጎንደር 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ያለ ምንም ተፅዕኖ ቃሉን ሲሰጥ አይቻለሁ ያለው ሶስተኛ ምስክር ተከሳሹን በአካል እንዲያሳይ ሲጠየቅ 7ኛ እና 10ኛ ተከሳሽን ‹‹ከሁለቱ አንዱ›› ብሎ በአማራጭነት አሳይቷል፡፡ መርማሪዎች ምስክርነት ላይ የነበሩትን ምስክሮችን ቃል በማየት በቀጣይነት ለሚመሰክሩት ከችሎቱ እየወጡ መረጃ እየሰጡና እየመከሩ ነው በሚል ተከሳሾቹና ጠበቃዎቻቸው ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቱ ሲወጡ ሲገቡ የነበሩትን መርማሪዎች ላይ ምንም ሳይል አልፏል፡፡ መርማሪዎች ለምስክሮች መረጃ እያቀበሉና እየመከሩ ነው የሚል ስጋት ያደረባቸው ተከሳሾች 3ኛ ምስክር 12ኛ ተከሳሽን ሳያውቀው በመቅረቱ መርማሪዎች ለሚቀጥለው ምስክር በምልክት ይነግሩታል በሚል 12ኛ ተከሳሽ ቦታውን ቀይሮ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ 4ኛ ምስክር ወደ ችሎት ገብቶ 12ኛ ተከሳሽን እንዲያሳይ ሲጠየቅም 12ኛ ተከሳሽን ቦታ ቀይሮ የተቀመጠውን 10ኛ ተከሳሽን በ12ኛ ተከሳሽ ስም በመጥራት ‹‹እሱን ነው የማውቀው›› በሚል ጠቁሟል፡፡
5ኛ ምስክር 9ኛ ተከሳሽ አቶ ቢሆነኝ አለነ ለኮንስትራክሽን የስራ ልምድ እንዲፅፍለት ሲጠይቃቸው ኤርትራው ውስጥ የተሻለ እንድል እንዳለ በመግለፅ ወደ ኤርትራ ለመላክ እንደመለመለው መስክሯል፡፡ ኤርትራ ውስጥ አለ የተባለው መልካም አጋጣሚ ምን እንደሆነ የተጠየቀው ምስክር ‹‹ብዙ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ስላለ ትጠቀማለህ ተብዬ ነው፡፡›› ብሏል፡፡ በመስቀለኛ ጥያቄ አርበኛው ግንባርን ለመቀላቀል ከአቃቤ ህግ በቀረበለት ጥያቄም ያመነው ምስክሩ፤ አርበኛው ግንባር የት እንደሚገኝ ሲጠየቅ ‹‹ሻዕቢያ›› ብሏል፡፡ ቀጥሎም ‹‹ሻዕቢያና አርበኛው ግንባር አንድ ናቸው›› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
በ2005 ዓ.ም በማያውቀው ወንጀል ታስሮ እንደነበር የገለፀው 6ኛ ምስክር ይህንን በደሉን ለ6ኛ ተከሳሽ ወርቅዬ ምስጋናው እንዲሁም ለ7ኛ ተከሳሽ አማረ መስፍን አማክሯቸው ሁለቱ ተከሳሾች ኤርትራ ከሚገኝ ሰው ጋር በስልክ እንዳገኙት ገልፆአል፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቃ ምስክሩ በእስር ላይ በደረሰባቸው ችግር ምክንያት በግዳጅ ለምስክርነት ቀርበው እንደሆነ ጥያቄ ቢያቀርቡም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአቃቤ ህግና በጠበቃዎች መካከል በነበረው ክርክር ለአቃቤ ህግ በተደጋጋሚ የበየኑ ሲሆን የተከሳሾቹ ጠበቃዎች ለአቃቤ ህግ የተለየ መብት ተሰጥቶታል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
አቃቤ ህግ ካሰማቸው በተጨማሪ ከሰዓት ይመሰክራሉ ተብለው የነበሩትን ምስክሮች ማን በማን ላይ እንደሚመሰክር እንዲገልፅ 16ቱን ተከሳሾች ወክለው የቀረቡት 4 ጠበቆች ጥያቄ ቢያቀርቡም አቃቤ ህግ ‹‹አንዱ መቅረብ ይችላል፡፡ ከሌሎቹ ጋር ግን ገና አልተነጋገርንም!›› በሚል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ሆኖም አንዱም እንዲመሰክር ሲጠየቅም ከሌሎቹ ጋርም ተነጋግረው ነገ እንዲያቀርብ እንዲፈቀድለት በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱ ፈቅዶለታል፡፡ ከተከሳሾቹ ጠበቃ መካከል አንዱም ‹‹አቃቤ ህግ የተለየ መብት ተሰጥቶታል፡፡ አዛዥ ናዛዥ ሆኗል፡፡ ከፈለገ ዛሬ ያቅርብ፡፡ ደንበኞቻችን በእስር ቤት እየተጉላሉ ነው›› ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ቀሪዎቹ ጠበቆችም አቃቤ ህግ አሉኝ የሚላቸው ምስክሮች አሰምቶ ደንበኞቻቸው የተፋጠነ ፍርድ እንዲያገኙ ጠይቀዋል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ የጠበቃዎችን አቤቱታ ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ አቃቤ ህግ ነገ ጳግሜ 4/2007 ዓ.ም በቀሩት ተከሳሾች ላይ 14ት ምስክሮችን ያሰማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
No comments:
Post a Comment