Thursday, September 17, 2015

አቶ ሞላ ለምን ደነበረ? (ታሪኩ አባዳማ)


ጄነራል ከማል ገልቹ ከበርካታ ወታደሮች ጋር ድንበር ጥሶ ወደ ኤርትራ ገባ ሲባል ሰማን። በዚህ የተነሳ የወያኔ ሰራዊት ለይቶለት የተናደ መስሎን በማግስቱ አንዳች የፖሊቲካ ለውጥ ለማየት የጓጓን ልንኖር እንችላለን – ጄት እና ስልታዊ የውትድርና ተዋጊ ሄሊኮፕተር ይዘው ወያኔን የከዱ መኮንኖች ዜና ሲሰማ አሁንም የድል ቀን ተቃረበ ብለን በቅንነት ደስታ የወረረን አንጠፋም።
Mola Asgedom running
በተቃራኒው ደግሞ አቶ ሞላ አስገዶም የደሚህት መሪ እጁን ለወያኔ ሰጠ ሲባል ትግሉ ተኮላሸ ብለን የደነገጥንም አንጠፋም …
በመሰረቱ ከነኝህ መልካም ሆነ ክፉ አጋጣሚዎች ልንማር የሚገባን ነገር ቢኖር የነፃነት ድል ባንድ ወይንም በሁለት ያልተጠበቁ ድንገተኛ ያቋም ለውጦች የሚጨበጥ ወይንም የሚዳከም ጉዳይ አለመሆኑን ብቻ ነው። እያንዳንዱ አጋጣሚ ግን ለትግሉ የይዘት ሳይሆን የአይነት ለውጥ በማከል ያጠናክረዋል። የህዝባዊ ትግል ድል አዝጋሚ ግን የማይቀር መሆኑን ጭምር አብሮ መቀበል ያሻል።

አቶ ሞላ አስገዶም ወያኔን በትጥቅ ትግል ለማስወገድ በደሚህት ጥላ ስር ተደራጅቶ ለአስራ ምናምን ዓመታት በመሪነት ሲሰራ (ሰታገል ማለት ይቻላል) ከቆየ በሁወላ አቋሙን ድንገት በመቀየር ወደ አገር ቤት (ለሰላማዊ ኑሮ ይሁን ትግል ገና አልታወቀም) በጥድፊያ መሸሹን ሰሞኑን በተሰራጩ ዘገባዎች ተነግሮናል። ድንገት በጥድፊያ መሆኑ ብዙዎችን አስደምሟል እንጂ።
አንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ ድርጅቱን መምራት እንደተሳነው ወይንም እንደማይፈልግ ገልፆ ራሱን ማግለል አንድ ነገር ነው ፤ ሙሉ ለሙሉ ከድቶ ከድርጅቱ በተፃራሪ መቆም እና ድርጅቱን ለማፍረስ ማሴር ግን ተራ ክህደት ይመስለኛል። ማለት የትግል ስልት ልትቀይር ትችላለህ – አንድ አላማ አንግበህ ስታበቃ ካለው የፖቲካ ምህዳር አንፃር ድል መቀዳጀት የሚቻለው በዚህ ወይንም በዚያ የትግል ስልት ነው ብልህ መወሰን ያለ ነው። አላማዬ ብለህ ያነግብከውን ግን እርግፍ አድረገህ መተው ብቻ ሳይሆን ልታፈርሰው ጭምር ስትነሳ በማንነትህ ላይ ጥያቄ ያመጣል።
ይህን የአቶ ሞላን የአቋም ለውጥ አስመልክቶ ወያኔ ባሰራጨው ወሬ መገንዘብ እንደተቻለው ሰውየው በሚስጥር ይሰልል እንደነበረ እና አሁን እንዲወጣ የተወሰነውም በተቀናጀ መልኩ እንደሆነ ነው። የአቶ ሞላ አወጣጥ የተቀናጀ የታሰበበት እና የወያኔ ተሳትፎ ያለበት ቢሆን ኖሮ በቅድሚያ ለወያኔ ጠቀሜታ ያለው አቶ ሞላ በመሆኑ ያለ አንዳች ኮሽታ እንዲያመልጥ ማድረግ በቻሉ ነበር። አላማው ሰራዊቱን ጭምር አሰልፎ እንዲያመልጥ ከሆነ ደግሞ እንደ መንጋ በተሽከርካሪ ተግተልትሎ ፣ አብዛኛው ተዋጊ ምን እየተደረገ እንደሆነ በማያውቅበት ሁኔታ ተተራምሶ ተገዳድሎ ሊሆን አይችልም ነበር።
አቶ ሞላ ለወያኔ ስለላ መረጃ ሰጪ እና የቆየ ታማኝ ሰው ከሆነ እስካሁን ያደረገው ሳይሆን ከዚህ በሁዋላ የሚሰጣቸው መረጃ የላቀ ዋጋ እንደሚኖረው ማንም መገመት ይችላል – እና ሸሽተህ ውጣ ሳይሆን እዚያው ቆይተህ ስራህን አቀላጥፍ ባሉት ነበር። ሞላም ሆነ ወያኔ የሻብያን ስለላ አውታር ሰብረው ይህን ማድረግ የሚችሉበት አመቺ ሁኔታ አለመኖሩን ግን ያውቁ ይመሰለኛል። ሞላ ሸሽቶ መሄዱ ከነፃነት ትግሉ አንፃር ከታየ ግን ትልቅ ብስራት ነው።
አቶ ሞላ በግሉ ምናልባትም ከጥቂት የሚስጢር ጓደኞቹ ጋር ዛሬ የደረሰበት ውሳኔ በርግጥም ትግሉን ከውስጥ የጠላት ቡርቦራ አድኗል። ማለትም በአዲሱ የስራ ድርሻ አመራር ላይ እንዲህ በዋዠቀ አቋሙ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ ሊደርስ የነበረው ጉዳት በቀላሉ የማይጠገን ይሆን ነበር። በልቡ ከቋጠረው ተንኮል አንፃር ሲታይ አሁን የወሰደው እርምጃ አበው ‘ባቄላ አለቀ ቢሉ … የሚሉት አይነት ነው።
የጥድፊያ ክህደቱ የወያኔ እጅ የሌለበት መሆኑን የሚያመለክቱ ነገሮች ብዙ ናቸው። አስቀድሞ ታስቦበት ቢሆን ኖሮ የወያኔ ቲቪ እና ፕሮፓጋንዳ አውታሮች ሁመራ ላይ ተክለው ይጠብቁ ነበር – ወያኔ ራሱ ድንገት በሆነው ነገር መደነባበሩን እና ጉዳዩን ለራሱ ማመን ተስኖት እንደነበር ሁኔታውን ለተከታተለው ግልፅ ነው። ሞላ ነብሱን አድኖ ሱዳን ተጠልሏል ፣ ብሎም ኢትዮጵያ ደርሷል ሲባል ወሬውን ለማጣራት እና ለመዘገብ ከቦታው ለመድረስ ሲኳትን መታየቱ ለዚህ ማረጋገጫ ነው።
ደሚህትን በሚመለከት የሰማነው ፣ ስለ ድርጅቱም አንብበን የተረዳነው እንደሚያሳየው አላማ ያለው ፖለቲካዊ ድርጅት መሆኑን ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የድርጅቱ መሪ ወይንም የተወሰኑ ሰዎች ደንብ እና አሰራር ከሚፈቅደው ውጪ ድርጅቱን የሚጎዳ እርምጃ ቢወስዱ ይጠየቃሉ – ድርጅቱ ህልውናውን ለማረጋገጥ ተገቢ እርምት ያደርጋል። አቶ ሞላ ከተናገረው እንደተረዳሁት ግን ድርጀቱ ማለት እሱ – እሱ ማለትም ድርጅቱ ነበሩ። እሱ በሌለበት ደሚህት እንደሌለ ፣ እንደማይኖርም ገልፁዋል። ይህ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲል የተናገረው ነገር የሰውየውን ውስጣዊ ተፈጥሮ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ወያኔ ያስቀመጠው ህገ መንግስት በነጋሪት ጋዜጣ ጭምር ታውጆ የምናውቀው ቢሆንም መለስ ዜናዊ በነበረ ዘመን ህግ ማለት መለስ ፣ መለስ ማለት ህግ ነበር – ዛሬ ጉዳዩ ትንሽ ተለውጦ ህግ ማለት ህወሀት – ህወሀት ማለት ህግ ሆኗል።
እንደ ሞላ አነጋገር ከሆነ ደግሞ ‘ሞላ ማለት ደሚህት – እናም ሞላ በሌለበት ደሚህት የለም’!
አስራ ሁለት ዓመት ያንድ ለነፃነት ትግል የተሰለፈ ታጣቂ ሀይል መሪ ሆኖ የቆመ ሰው የቁርጥ ቀን ሲመጣ ባንድ ጀንበር ደንብሮ ፣ ከስሩ የተሰለፉትን ሳይቀር አደናግሮ እና አዋክቦ መሸሽ ምን አመጣው? ብለን በጥሞና መነጋገር ይገባል። ምን አግኝቶት ተፈታ? ብሎ መጠየቅ ጥሩ ነው።
እንደ ውነቱ ከሆነ ይህ ሰው በብዙ መልኩ የድርጅቱ ባለውለታ ነው። ምክንያቱም ባንድ በኩል አቶ ሞላ ድርጅቱ ለረጅም አመታት በህልውና እንዲቆይ ላደረገው ተሳትፎ ምስጋና ልንነፍገው አይገባም። በሌላ በኩል ደግሞ ይህን አይነት አስተሳሰብ ይዞ አሁን አዲስ በተፈጠረው ጥምረት ውስጥ ቢቆይ ኖሮ ድርጅቱ እጅግ የተወሳሰበ ችግር ላይ ይወድቅ እንደ ነበር አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል።
ኖሮም ጠቅሟል ሸሽቶም ጠቅሟል ባይ ነኝ። የቆየውም የሸሸውም በትክክለኛ ጊዜ ነው።
ለነፃነት ትግል ለተሰለፉ ሀይሎች ቁምነገሩ ሞላ መሸሹ ሳይሆን ምን አስገድዶት ይህን አቋም ወሰደ የሚለው ሊሆን ይገባል። የሆነ ምክንያት አለ ; ያ ምክንያት መጠናት ፣ መብራራት ይገበዋል። ትግሉ በዚህ አጋጣሚ ትምህርት መቅሰም አለበት። ትምህርት ደግሞ መላ ምት ሳይሆን ተጨባጭ ነገሮችን በመተንተን ሊሆን ይገበዋል። ይህን በሚመለከት ሰፊ የስራ ድርሻ የሚጠብቀው አንድም ከድርጅቱ ሌላው በቅርቡ ከተፈጠረው ጥምረት ይሆናል። ድርጅቱም ሆነ ጥምረት የፈጠሩት ሀይሎች የሚያካሂዱትን ጥናት እና ፍተሻ ለኛ መግለፅ ግን አይጠበቅባቸውም። የነፃነት ትግል የሚያካሂድ ሀይል ራሱን ለማጠናከር የሚወስዳቸውን ርምጃዎች ለሁሉም መግለፅ ግዴታ የለበትም።
ደሚህት የፖለቲካ ድርጅት ነው ስንል በመዋቅር እና በሀላፊነት ተዋረድ ብሎም በደንብና ህግ የሚገዛ መሪው የሚወስዳቸው ማናቸውም እርምጃዎች በዚህ ማእቀፍ ውስጥ የሚከናወን ይሆናል። የድርጅቱ አቋም ሲቀየር በተዋቀረው ድርጅታዊ አሰራር ውይይቶች ይካሄዳሉ ፣ የውሳኔ ሀሳብ ይቀርባል ይወሰናል ብዬ ገምታለሁ። ይህ ካልሆነ ግን መሪው ባሻው ጊዜ እስከ ተራ አባላት ድረስ ወርዶ አቋም ማስቀየር ፣ ድርጅቱን ጥሎ መሸሽ ፣ ማፍረስ ፣ አቋሙን መለወጥ የሚችልበት አካሄድ ከታየ የፖለቲካ ድርጅት አሰራር ሳይሆን የግል ሰብ ወይንም በሚስጥር ሴራ የተቆራኙ ጥቂት ግለሰቦች የሚዘውሩት ነው ያሰኛል። የአቶ ገብሩ አስራትን መፅሀፍ አንብባችሁ ከሆነ መለስ ዜናዊ እንዴት የህወሀትን ደንብ እና አሰራር ጥሶ የራሱን ፈለጭ ቆራጭ አገዛዝ እንደገነባ እናያለን። ‘ደንብ ጥሰሀል’ እያሉ አካሄዱን ለመግታት ሙከራ ያደረጉ የህወሀት ሀላፊዎች በሙሉ እንዴት እንደተወገዱም ያስረዳል። አንድ ድርጅት በግለሰብ ቁጥጥር ውስጥ ሲወድቅ የሚሆነው ይኸው ነው።
አቶ ሞላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ‘ለህዝባችን ስንል ሜዳ ብንወጣም አዋጪ (profitable) ስላልሆነ ገምግመን ውሳኔ አደረግን’ ይላል። ‘ኢትዮጵያ ፎቅ እና መንገድ እየተሰራ መሆኑን ስንከታተል ቆይተናል…’ ሲል ያክልበታል – በረሀ የተሰደደው ፎቅ እና መንገድ እጥረት መኖሩን በማስተዋሉ ተቆጭቶ እንደ ሆነ ሁሉ!! ‘… ገምግመን ውሳኔ አደረግን’ (እኛ ሲል የደሚህትን አመራር መሆኑ ነው።) የደሚህት አመራር ግን በዚህ እንደማይስማማ ፈጥኖ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።
አቶ ሞላ ራሱ በግል ውሳኔ የወሰደውን የክህደት እርምጃ ከሌሎች ጋር ለማነካካት አስቧል። ደሚህት ማለት እኔ ነኝ የሚል ሰው ምን አይነት ውይይት ከማን ጋር ሊያደርግስ ይችላል?
ዲምሀት በፕሮግራሙ አንፃር ሲታይ ከሌሎች ተቀዋሚ ድርጅቶች ጋር በቅርብ ለመስራት የሚያግደው እንዳችም ምክንያት እንደሌለ ያመለክታል። ይልቁንም ኢትዮጵያዊ ታሪኩን እና ክብሩን በፀና መሰረት ላይ ለማረጋገጥ ሲል ብረት እንዳነሳም ፕሮግራሙ ያረጋግጣል። በዚህ ፕሮግራም ጥላ ስር ተደራጅቶ እንኳን መሪው ተራ አባሉ ሳይቀር ለኢትዮጵያዊ አንድነት መሰለፍ ግዴታ አለባቸው።
ሞላ የዚያ አንድነትን የሚሻ ድርጅት መሪ እንደነበረ ሁሉ በሰነዱ ላይ የተቀመጠው የወንዳማማችነት ትብብር ፍለጋ ጉዳይ የሱም አላማ ነበር ማለት ነው። ታዲያ በሂደት የተፈጠረው ጥምረት ፍሬ ሲያፈራ እና ኢትዮጵያዊ ከሆኑ ፖለቲካ ሀይሎች ጋር መሰለፍ ቀኑ ግድ ሲል ለምን ደነበረ? የሞላ ክህደት የተከሰተው ድርጅቱ በፕሮግራሙ አስቀምጦ እመራበታለሁ ያለው ጉዳይ እውን ሲሆን ነው። የራሱን ድርጅት ፕሮግራም አላነበበውም ወይንስ አንብቦት አልገባውም?
ስለ ትግሉ አዋጪ መሆን አለመሆን ሲናገር አንዳንድ ብሔረሰቦችን በስም እየጠራ ‘አባላቸው ከአስር እንደማይበልጥ ለምንም የማይሆኑ ናቸው’ ብሎ ለድርጅቶቹ ያለውን ንቀት ይገልፃል – እዚህ ላይ ጉዳዩ ስለ ብሔረስብ ተዋፅኦ ብዛት ነው ወይንስ የትግሉን አቅጣጫ ብሔራዊ ቅርፅ ለማስያዝ የተደረገ ነው? ሞላ የሚያሰላስለው እና የሚያሰላው ከየትኛው ብሔረሰብ ስንት የሰው መዋጮ ተገኘ በሚለው ላይ ነበር። በቃ – መለስ ዜናዊ የተከለው የዘረኝነት አባዜ ዳግም ነፃ ሊያወጣን በነበረው ሰውዬ ህሊና ውስጥ ሰርፆ ተተክሏል። ከየትኛው ብሔረሰብ ነህ የሚለው መታወቂያ ሞላ ስልጣን ሲይዝም ይጠብቀን ነበር ማለት ነው። አቶ ሞላ ጉዳዩን ከኮታ አንፃር እንጂ ከሰፊው ኢትዮጵያዊነት ስዕል አንፃር አልተቀበለውም።
እንደመሰለኝ የተፈጠረው ጥምረት ግን ለዚህ ለሞላ አቋም ቦታ የሚሰጥ ሆኖ አልተገኘም – ለሞላ አልተመቸውም። የብሔረሰብ ኮታ ለፖለቲካ ስልጣን መሰላል መሆኑ ይቁም ነው ጥያቄው – ሀሎ አቶ ሞላ ይሰማዎታል!!
ትግሉ አዋጪ ያልሆነው ከሱ ብሄረሰብ ሌላ ያለው ቁጥር አናሳ ሆኖ በመገኘቱ ነው ለማለት የሚፈልግ ይመስላል። ህዝቡ ደግሞ በጎጥ ውክልና ተገጣጥሞ የሚመጣ የነፃነት ትግል ባፍንጫችን ይውጣ ብሎ እየወተወተ መሆኑን አቶ ሞላ የሰማም የሚያውቅም አልመሰለኝም። እሱን የሚከነክነው ጉዳይ ከየትኛው ዘር ምን ያህል ሰው መጣ – ነገ ደግሞ ከየትኛው ዘር ምን ያህል ሞተ በሚል ስሌት ስልጣን እንዴት እንቀራመት የሚል ሌላ ዕዳ ሊያስታቅፈን ነው። ስንት ሰው ከዚህ ዘር ፣ ከዛኛው ዘር። የነ ተፈራ ዋልዋ የብአዴን ሰራዊት ሲያኮርፍ የስልጣን አያያዝ ቀመር – ‘እነሱ ቆንጥር ለቆንጥር ሲዋጉ…’
ሌላው ማንሳት የምፈልገው ስለ ዶክተር ብርሀኑ ነጋ የተናገረው ‘የነጋዴ’ ሆኖ አገኘሁት ጉዳይ እዚህ ግባ የማይሉት ዝባዝንኬ መሆኑን ነው። አቶ ሞላ ስለ ብርሀኑ ነጋ አስተዳደግ ፣ ትምህርት ፣ ህይወት እና ፖለቲካ ታሪክ ምንም ነገር እንደማያውቅ ተገነዘብኩ። አንድ የተሟላ ኑሮ የሚመራ ግለሰብ ‘አዋጪም አትራፊም’ የሆነ መደበኛ ስራውን እና ቤተሰቡን ጥሎ በረሀ የሚገባው እንደ አቶ ሞላ ‘ቪላ ፣ ምግብ ፣ መኪና’ ፍለጋ አልነበረም – ብርሀኑ እንደ ሰብአዊ ፍጡር የሚያስብ ነፃ በሆነ ህብረተሰብ በህግ የበላይነት ጥላ ስር ለመኖር ካለው ራዕይ የተነሳ በረሀን የመረጠ ሰው ነው።
ደግሞም ሞላ በጋዜጣዊ መግለጫው አንዳችም ስለ መርህ እና የህብረተሰብ ፖሊተካዊ ፋይዳ ያነሳው ነገር የለም። ለዚህ መልሱ ምን እንደሆነ እሱ ራሱ መጨረሻ ላይ የተናገረው ይመስለኛል “… እኔ የገበሬ ልጅ ነኝ ፣ አልተማርኩም” ሲል። የገበሬ ልጅ መሆን ፣ አለመማርም ሰብአዊነትን ዝቅ አያደርግም። ‘ትልቅነት ከትልቅ ከመወለድ’ (ጃንሆይ) ወይም ፊደል ከመቁጠርም አይመጣም።
ከሰብአዊ ፍጡርነት ባሻገር ግን ነገሮችን በተለያየ መልክ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ትምህርት እጅግ ጠቃሚ ነገር መሆኑን መካድ አይቻልም። አቶ ሞላ ሲመፃደቅ ‘ምግብ ሞልቷል፣ ቤት ሀያ አምስት ሺህ ብር ይከፈልልኝ ነበር ፣ መኪና ሞልቷል….’ በማለት። እውነቱ ደግሞ እሱ ትናንት በታጋይነት ስም አስመራ ዛሬም በከሀዲነት ውለታ አዲስ አበባ “… ቤት ፣ መኪና ፣ ምግብ” የሚነፍገው እንደማይኖር ያረጋገጠ ይመሰለኛል – ‘ከመንግስት ጋር ተደራድሬ…’ ያለው ድርድሩ ‘ምግብ ፣ ቤት እና መኪና’ ይሰጠሀል ካልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። አቶ ሞላ ደሚህት የሚባል ሰላማዊ ተቀዋሚ ድርጅት እንድመሰርት ፍቀዱልኝ ሊልም ይችላል – ድርድሩ ውስጥ – መሸጋሸግ እንዲህ ነው –
በተቃራኒው እነ ብርሀኑ ነጋ አቶ ሞላ ህይወቱን ሙሉ አይቶት የማያውቀው አይነት ቤት ፣ መኪና እና ምግብ ጥለው ወደ መራራው ትግል ወርደዋል። ነፃነትን የምንሻ ከጎናቸው መሰለፍ ብቻ ነው።
እነ ዶር ብርሀኑ ነጋ የወያኔን ዘረኛ ፖሊቲካ በሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሂደት መለወጥ ይቻላል በሚል እምነት ቅንጅትን አደራጅተው በኮረኮንች ጎዳና ረጅም ተጉዘው ፣ ሞክረውት የማያዘልቅ ጉዞ መሆኑን የተገነዘቡት መራራ ዋጋ ከከፈሉ በሁዋላ ነው ፤ ዛሬ ወደ ብቸኛው የአመፅ አማራጭ ተገፍተው የገቡት ሰላማዊ አማራጮች ዝግ መሆናቸውን በስሜታዊነት ሳይሆን በተጨባጭ ውነቶች አረጋግጠዋል።
አቶ ሞላ በተደጋጋሚ ጉሮሮውን እየሞረደ የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሳዳምጥ ስለ ግለሰቡ የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት ችያለሁ። ለምን አቋሙን እንደቀየረ ሲናገር ‘የልማት ግስጋሴ እና ሙስና… እየተወገደ መሆኑን በመገንዘቡ’ እንደሆነ ይናገራል። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የኤርትራ መንግስት በሀያ አምስት ሺህ (ዶላር ብር ናቅፋ ግልፅ አይደለም ጠቃሚም አይደለም) ቤት ያኖረው እንደነበረ – መኝታ ምግብ መኪና በሸ በሽ እንደነበር ጠቁሟል። እውነተኛነቱ ይደነቃል – እሱ ባይነግረንም ስለ ቅምጥል ኑሮው በድብቅ ተቀርፀው የተቀመጡ ባርካታ ስዕላዊ ሰነዶች እንዳሉ ሰምቻለሁ። ሙስና በታጋዮች ስም ሲፈፅም የነበረ ሰው መጠያየቂያ ቀን እየተቃረበ ሲመጣ ጥሎ ይሸሻል – ከሸሸበት አዲስ አበባ ደግሞ ሌላ የቅምጥል ኑሮ ይጠብቀው እንደሁ ወደፊት የምንሰማው ይሆናል።
በሌሎች ድርጅቶች ሰርጎ መግባት ፣ የይስሙላ ግንባር ወይንም አንድነት ፈጠርኩ ብሎ ከውስጥ መቦርቦር ፣ ተቆርቋሪ መስሎ መሰናክሎች መፍጠር… ባጭሩ ለግል ጥቅም እና ፍላጎት እርካታ ሲሉ በሌሎች ጉልበት እና ጊዜ የተገነባን ተቋም ለማፈራረስ መስራት ፖለቲካዊ ብኩንነት ነው

No comments:

Post a Comment