የ6 አመት ፍርደኛ ነኝ፡፡ ከኤች አይ ቪ በሽታ ጋር እኖራለሁ፡፡ የአንጀት ካንሰርም አለብኝ፡፡ ልጆቼን ያለ አባት ነው ያሳደኳቸው፡፡ በእኔ እስር ምክንያት አሁን እነሱም እየተጎዱ ነው፡፡ አሁን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ አራት አመት ሊሞላኝ ነው፡፡ በህዳር 2007 ዓ.ም በአማክሮ እንድፈታ ማረሚያ ቤቱ ወስኖ ነበር፡፡ ሆኖም ባላወኩት ጉዳይ እንደገና አመክሮዬን ከልክለውኛል፡፡
ቦሌ አየር ማረፊያ ‹‹23›› የሚሉት ስራ አለ፡፡ መንገደኛን ጠብቆ በመኪና አሳፍሮ መንገድ ላይ ይዘርፉና ጥለዋቸው ይሄዳሉ፡፡ አንዲት ልጅ በዚህ ወንጀል ተከሳ ታስራ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር ከመገናኘታችን በፊት ከአንድ አመት በላይ ሌላ ቦታ ታስራ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር ደግሞ አራት ወር ነው የታሰረችው፡፡ በማላውቀው ወንጀል ይች ልጅ እንድትመሰክርብኝ ተደረገ፡፡
ልጅቱ ወረዳ ዘጠኝ የሚባለው እስር ቤት ውስጥ ታስራ በነበረበት ወቅት በእግዚቪት የተያዘባት ልብስ ብቻ ነው፡፡ ፖሊሶቹም ከዚህ ውጭ ያዝን አላሉም፡፡ እኔም ብጠይቅ ሌላ ነገር ተይዞባታል የሚል አላገኘሁም፡፡ እኔን ግን የሰረኩትን ገንዘብ እስር ቤት ውስጥ ሰጥቻታለሁ ብላ መሰከረችብኝ፡፡ እንግዲህ ገንዘብ ወደ እስር ቤት ሲገባ ተመዝግቦ ነው፡፡ ሳታስመዘግብ አትገባም፡፡ ደግሞ ሰጠኋት የምትለው ገንዘብ እስር ቤት ውስጥ ሊገባ የሚችል አይደለም፡፡ እሷ ለእኔ ሰጠኋት ያለችው ወደ በኢትዮጵያ ብር ሲመነዘር 40 ሺህ ብር ያህል ነው፡፡ የዱባይ ገንዘብ ነው ሰጠኋት ያለችው፡፡ ስሙን እንኳ በደንብ አታውቀውም፡፡ ሪያድ ነው ያለችው፡፡ ሪያድ የከተማ ስም ነው እንጅ የገንዘብ ስም አይደልም፡፡ የዱባይ ገንዘብ ደግሞ ስሙ ከዚህ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ ወደ እስር ቤት ሊገባም አይችልም፡፡ እኔ እጅ ላይ ምንም ገንዘብ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ምንም አይነት ማስረጃ አላቀረቡብኝም፡፡ ባለወኩት ምክንያት ሊያጠቁኝ ፈልገው ነው፡፡ ምን እንደሆነ ግን እኔም ሊገባኝ አልቻለም፡፡
ይች ልጅ ይህን ያህል ገንዘብ እስር ቤት ውስጥ ሰጥቻታለሁ ብላ ስለመሰከረችብኝ አመክሮዬን ተከልክያለሁ፡፡ የሚያሳዝነው የሰረኩትን ገንዘብ ለእሷ ሰጠኋት ያለችው ልጅ በእኔ ላይ ከመሰከረች በኋላ ከእስር ተለቃለች፡፡ እኔን ለምን እንዲህ እንደሚያጠቁኝ አላወኩም፡፡ የኤች አይ ቪ በሽተኛ መሆኔን ያውቃሉ፡፡ ሌሎች ችግሮቼንም እንዲሁ፡፡ ይህ በደል እየደረሰብኝ ለማንም አቤት ማለት አልቻልኩም፡፡ የሚሰማ የለም፡፡ ወደ አለቆቻቸው ሄጄ አቤቱታ ማቅረብ አልቻልኩም፡፡
ልጅቱ ገንዘብ ሰርቄ ሰጥቻታለሁ ብላ ለማረሚያ ቤቱ ሰዎች ብትመሰክርብኝም አመክሮዬን ከለከሉኝ እንጅ በፍርድ ቤት ክስ አልተመሰረተብኝም፡፡ እኔም ለፍርድ ቤትም ለሌላም አካል አቤቱታ ማቅረብ የምችልበት አጋጣሚ አላገኘሁም፡፡ ከጠበቃ ጋር እንዳልገናኝ ተደርጌያለሁ፡፡ ለ3 ወር ከ9 ቀን በአጃቢ ነበር ቤተሰብን የማገኘው፡፡ ቤተሰቦቼ እንዳይደነግጡ ብዬ ‹‹እዚህኮ ሁሉንም እንዲህ ነው የሚያደርጉት፡፡ እኔን ብቻ አይደለም›› እላቸው ነበር፡፡ ሽንት ቤት ስሄድም ሳይቀር ይከታተሉኛል፡፡ አደራ ይህን መረጃ ስታወጣ ስሜን እንዳትጠቅስ፡፡ እነሱስ ማንን እንዲህ እንደበደሉ ያውቁታል፡፡ ቤተሰቦቼ እንዳይረበሹብኝ ስለፈለኩ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment