መስከረም ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ማዬት የተሳናቸው ተማሪዎች መስከረም 11 ቀን 2008 ዓም ፣ ከመብት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በማንሳታቸው በፖሊሶች ክፉና የተደበደቡ ሲሆን፣ የተማሪዎችን ተወካዮች ጨምሮ 17 ማዬት የተሳናቸው ተማሪዎች ተይዘው ታስረዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ተማሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት ፣ ተማሪዎች የማደሪያ ክፍል በአንድ ግቢ ውስጥ ለሚገኘው ኮሌጅ በመሰጠቱ ፣ ተማሪዎች እንዲመለስላቸው ሲጠይቁ፣ የፌደራል ፖሊስ በፍጥነት ገብቶ አይነሰውራን ተማሪዎችን ደብድቧል። ተማሪዎቹ የመኝታ ክፍሉ እንዲመለስላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቢቆዩም መለስ በማጣታቸው የትምህርት ማቆም አድማ አድርገዋል። ፖሊሶች፣ ተማሪዎቹ ከመኝታ ክፍላቸው እንዲወጡ ትእዛዝ ቢሰጡም፣ ተማሪዎቹ ግን ፈቃደኛ አልሆነም። ፖሊሶች ወደ ክፍል እየገቡ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ተማሪዎች ላይ ከባድ ድብደባ የፈጸሙ ሲሆን፣ ብዙዎቹ እጆቻቸውና እግሮቻቸው በድብደባ ብዛት ተጎድቷል። አንድ ተማሪ " ሩጠን ለማምለጥ በማንችልበት ሁኔታ ፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ወስዶብናል" ብሎአል። የታሰሩት 17 አይነስውራን ተማሪዎች እንስካሁን አልተፈቱም። ትምህርትም አልተጀመረም። የፌደራል ፖሊስ እስካሁን የሰጠው ይፋዊ መግለጫ የለም።
No comments:
Post a Comment