Friday, September 18, 2015

ህወሃት ኢህአዴግ በመዳከሙ የቀድሞ አባሎቹን ለማሰባሰብ ሙከራ እያደረገ ነው ተባለ

መስከረም ፯ (ሳባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቀድሞው የህወሃት መስራችና በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ አባል የሆኑት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ፣ ህወሃት ኢህአዴግ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሞ የሚገኝበት ወቅት በመሆኑ፣ ከድርጅቱ የለቀቁ የቀድሞ አባሎቹን በማነጋገር ወደ ድርጅታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየጣረ መሆኑን ገልጸዋል። ህወሃት/ኢህአዴግ በራሱ የውስጥ ችግር መዳከሙን የሚገልጹት ዶ/ር አረጋዊ ፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት እርሳቸውም ወደ አገር ቤት እንዲገቡ በተደጋጋሚ እንዳናገሩዋቸው ይሁን እንጅ እርሳቸው የሚታገሉለት አላማ ጥሪውን እንዳይቀበሉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል። ዶ/ር አረጋዊ "በቅርቡ የትህዴን ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሞላ አስጎደም ወደ ህወሃት መመለሳቸው ወይም ሌሎች የቀድሞው ታጋዮች ወደ ድርጅቱ መመለሳቸው ለህወሃት ኢህዴግ ትንሽ ስትንፋስ ይሰጠው ካልሆነ ችግሩን አይቀርፍለትም " ሲሉ ያክላሉ። በእርሳቸውና አቶ ሞላ አስገዶም ይመሩት በነበረው ትህዴን መካከል የቆዬ ግንኙነት አለ ወይ ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር አረጋዊ፣ ኮሎኔል ፍሰሃ ድርጅቱን ይመሩ በነበረበት ወቅት ግንኙነት እንደነበራቸው ይሁን እንጅ አቶ ሞላ አመራሩን ከያዙት በሁዋላ ግንኙነቱን ማቋረጣቸውንና አቶ ሞላ በተደጋጋሚ ሊቀርቡዋቸው ቢሞክሩም ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ገልጸዋል። ዶ/ር አረጋዊ ፣ አቶ ሞላም ሆኑ ሌሎች የህወሃት/ኢህአዴግ አባላት ወደ ድርጅቱ ተመልሰው መግባታቸው የትግራይ ህዝብ ሊወቀስ እንደማይገባው፣ የትግራይን ህዝብ በደፈናው ከህወሃት ጋር ደምሮ ለማዬት የሚደረገው ሙከራ ፣ እንደህወሃት/ኢህአዴግ ዘረኛ መሆንና በትግራይ ውስጥ ያለውን ብሶት ላለማዬት ከመፈለግ የሚመጣ ነው ብለዋል። ዲሞክራሲያዊ መሰረት ያለው ስርዓት ለመገንባት እንታገላለን የሚሉ ሃይሎች የኢህአዴግን አገዛዝ ለማስወገድ መተባባር ይኖርባቸዋል ሲሉም ዶ/ር አረጋዊ ተናግረዋል። ሙሉውን ቃለምልልስ እንደደረሰ እናቀርበዋለን።

No comments:

Post a Comment