ባመንክበት ጽና
የጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም ምክር
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከታዘብኩዋቸው ነገሮች አንዱ- የኢትዮጵያ ህዝብ ከሃዲዎችን ወይም የፖለቲካ አጥር ዘላዮችን የሚጸየፍ መሆኑን ነው። ለህዝብ ነጻነት እታገላለሁ ብለህ ከተነሳህ በሁዋላ፣ ከደከመህ፣ ትግሉን ትተህ አርፈህ ተቀመጥ እንጅ በምንም ሁኔታ ነጻነትን ከሚያፍነው ጋር አትተባበር ወይም አትቀላቀል። ከአፋኞች ጎራ ወጥተህ ወደ ነጻነነት ሃይሎች ጎራ እንኳን ብትገባ ህዝብ በፍጥነት ይቀበለኛል ብለህ አትመን፤ ከአፋኞች ጋር እስከመጨረሻው መፋታትህን ለማሳዬት ብዙ መስዋትነት መክፈል ግድ ይልሃል። ከነጻነት ጎራ ወጥተህ ወደ አፋኞች ጎራ ከገባህ ግን እንደሞትክ ቁጠረው። አጥር ዘላዮችን ራሳቸው አፋኞች እንኳ አምነው ከልብ አይቀበሏቸውም፣ በሚዋዥቀው ባህሪያቸው ነገ እነሱንም ጥለዋቸው እንደሚሄዱ ይሰጋሉና። ባለህበት ጽና! ከደከመህ እረፍት ውሰድ ወይም በቃኝ ብለህ ቤትህ ተቀመጥ። ሃውልት የቆመላቸው ለጽኑዎቹ ለእነአቡነ ጴጥሮስ መሆኑን አትርሳ። ከሃዲዎችማ እንኳንስ ሃውልት፣ ሞተውም ስማቸው " የክህደት ምሳሌ" ሆኖ እየተነሳ ሰላም አያገኙም፤ በህይወት ያሉ ዘመዶቻቸውም "የባንዳ ዘር" እየተባሉ መሳቀቃቸው አይቀርም። በህይወት ሲኖሩ ከመጠላት፣ ሲሞቱ ደግሞ የክህደት ምሳሌ ከመሆን የበለጠ የሞት ሞት የለምና በአለህበት ጽና፣ ጽኝ!
No comments:
Post a Comment