ቹቸቤ ነኝ እንዴት ከረማችሁ? በዐል እንዴት ነበር? ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አሉ የአገራችን ሰዎች። ዘንድሮ ከጉድም ጉደኛ ሰው ከወደ ሰሜን አቧራውን አጬሰውና የኔንም ቀልብ ሳበው። ኢካድፎች ይህንን ከሰማያዊ ፓርቲ ተዘረፈ የሚባለውን በልኩ ያልተሰፋ ሱፍ ግጥም አድርጎ ‘እኛ እኮ አንቻልም’ የሚለውን ሰውዬ አሳይታችሁን እኔንም ለሳቅና ለቅሶ ጋበችሁኝ። ሳቅሁኝ በሞላ ለጋሰራሽ ድራማ። አለቅስኩኝ ኢትዮጵያችን ሰው አጥታ ሞላ የስንትና ስንት ሺህ የነጻነት አርበኞች መሪ ነበር የሚለውን ሳስብ። ቢሆንም አቶ ተሰማ እሸቴ አንዳንድ አርበኛ የሚለውን ስም የማይመጥኑትን ለመግለጽ “እዩት ተመልከቱት የአምላክን ደግነት …. እንዴት ያስደስታል አርበኛ ሲጫወት” ብለው የተቀኙትን አስታውሼ እውነትም አር-በኛ ተጫወተብን አልኩኝ …. ሞልዬ ጎምላላዬን አይቼና ለመስማት ሞክሬ።
ሳቄን አገባድጄ ወደ ሀዘን ሰፈር ጭልጥ ስል ጠላታችሁ ስቅቅ ይበል ተሳቅቄ ልሞት…. አሄሄ የለም የለም ሞላማ ወዶ የገባበት መሳቀቄማ ለፕሮፌሰሩ ነው እንጂ። አሁን ብርሃኑ ሊቀመንበር ሞላ ምክትል ሆነው ምኑ ከምን ይያዝላቸው ነበር ብዬ ነው መሳቀቄ። ቢሆንም ያቺ ለየት የምትለው የፕሮፌሰሩን ተረብ ቅልቅል ሳቃቸውን አሰብ አረኩና እኔም ፈገግ አልኩ። ሞላ ሃሳቡ ጎድሎቦት በተደጋጋሚ “ቅድም እንዳልኳችሁ” ዲሞክራሲ ምናምን እያለ ነገሩን ሲያተረማምሰው ታሰበኝና ከተረት ማህደራችን አንዱን መዝዤ “ሳይደግስ አይጣላም” አልኩኝ።
ንግግሩን ብቻ ሳይሆን ነገረስራውን ሁሉ ተመልክቼ ግለሰቡ በመምታታትና በግራ መጋባት የታወከች ነብሱን ብብቱ ስር አድርጎ መንጎዱን ሳስብ ከመኖርህ መሄድህ በጀን አልኩኝ። ግን ምንም እንኳን እሱ በኩራት እንደ ባንዳዎቹ ‘ወገን በመምሰል ስሰልል አመት አለፈኝ’ ቢልም ድንገተኛ አኪያሄዱና አረፍተነገር ማመንዠጉ ቀለም ጠገቦቹ ምሁራን “ዱር ቤቴ” ማለታቸው እንዳሸበረው ያረጋግጣል። አሁን እነዚህ በርገር በሊታ የአሜሪካ ቅምጥሎች ቂጣ በሊታ ሊሆኑ እዚያ ድረስ ይመጣሉ ብሎ ማን አሰበ?
ጉሮሮውን ሲጠራርግ የምራቅ ድርቅ እንጥሉን እንጨት ያደረገበት ይመሰላል። እናም ደረቁን አፉን በደረቅ እጁ ሲጠራርግ ከእንቅስቃሴው በስተጀርባ ምነው በቀረብኝ የሚል ድምፅ ይሰማችሁ ይሆን? ሰውየው እህ እህ ሲል የጣር ድምፅ የሚያሰማ ነበር የሚመስለው። ደግነቱ በቀኝ እጁ የግራ ጆሮውን ለማከክ በሚያደርገው ጥረት ፊቱን ለሰከንድ የሚደብቅባት ብልጠቱ ሳልወድ ታስቀኝ ነበር።
ይህንን ጉድ አብራኝ ያየች “ኡ ኡ ኡ ሳይቸግር ጤፍ ብድር” አለች ነገሩ ሁሉ እንዳልተያያዘለት ተገንዝባ። ይበልጥ ያሳቀችኝ ግን “እኔ እምለው ቹቸቤ የወያኔ ምላስ አንድ ብቻ ነበር? እሱም ከመለስ ጋር ተቀበረ ማለት ነው?” ያለቺው ነበር። የሽሙጥ ችሎታሽ እንደ ልማታዊ መንግስታችን ትንበያ በሁለት አሃዝ አድጓል ብዬ ትከሻዋን መታ መታ አደረኩት። እውነትዋን እኮ ነው። ነብሱን ይማረው አልል ነገር እነ ገብርዔል “ለሱ ጥብቅና ማን አቆመህ?” ይሉኛል እንጂ እውነት ባለመቀስ ምላስ ነበር አቶ መለስ። አይን ያወጣች ውሸትም በሱ ምላስ ስትነገር ለመሞኝት ሆነ ብለው የተመቻቹትን ወይንም ተፈጥሮ ብልህነትን ለነፈገቻቸው ውብ ነበረች። “የመለስ ጭንቅላት ለማንም ይተርፋል” ያለቺው ኤክስ ቀዳማይ እኮ እውነቷን ነው። ካየቻቸው ሁሉ እሱ አንደኛ ነው። መቼስ ከማታውቀው ጋር አታወዳድር። እና የወያኔ ቀላማጆች ሁሉም ሁለት ግራ እግሮች ናቸው መነሻና መድረሻቸው መሄጃና መምጫቸው አይለይም። አሁን ደግሞ ሞላ ደረጃውን ከፍ አደረገው።
ሞልዬ ጎምላላዬም አፍንጫው እስክታልቅ ድረስ ጠርጎ ሊጨርሳት እያለ ‘እዚህም እኛው ነን እዚያም እኛው ነን’ አለ። አረፍተነገሩን በምናምንና በቅድም እንደነገርኳችሁ እያረዘማት ከኤርትራ አንስቶ ግንቦት ሰባት ላይ ያላትማትና በ ኤርትራ ጀነራሎች ኪስ አሾልኮ የኢትዮጵያ የቅዠት ዲሞክራሲ ላይ ያነጥራታል።
ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ በጅምላ ባይኖርም በችርቻሮ ግን ይገኛል ብሎ አፉን ሁለቴ ከጠረገ በሁዋላ ደግሞ ወደ ሌላ ውሉ የጠፋበት ታሪክ ይሄዳል። ሙስና ከኤርትራ ተሰዳ ኢትዮጵያ ገብታለች ቢሆንም መንግስት በልማት ስም ይጠግናታል ብሎ ሳያበቃ እዚያ ማዶ የጎጥ ድርጅቶች አሉ እኛ ትግራይን እንበል እንጂ አላማችን ኢትዮጵያን ጠቅልሎ ለመያዝ ነው ይላል። “ጅል ይህንንማ የትግራይ ነፃ አውጪ ጨርሶት የለም ደሚት ወይ ድማሚት ለምን ያስፈልጋል” ብላ ወዳጄ ሳቋን ስታቀልጠው ዛሬ ኮሚክ የወጣትን ሰው አጅብና አብሬ እስቃለሁ። እሱ አፈራረስኩት ካለበት ከወዲያ ማዶ ግን ትግሉን ይበልጥ እናፋፍማለን የሚሉት እንዳሉ ናቸው። ቢሆንም ቢሆንም መጠንቀቅ አይከፋም እንላለን።
ፕሮፌሰር መስፍን “ወያኔነት ከእውቀት መጣላት ማለት ነው” እንዳሉት ሞላም ወደ ደናቁርቱ ነው መጭ ያለው። ስለዚህም ነው የአኬልዳማ ደራሲና የመድረክ መሪው በረከት እንኳን ‘ለጦረኛው’ የሰላም አርማ የሆነውን ሰማያዊ ቀለም ከማልበስ ባሻገር መተወኑን ማስተማር አልተሳካለትም። ይህን መቀላበድ የፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ አለው ብሎ የበተነው ክፍል በብቃት ማነስ የተለከፈ ነውና የእውቀት ጸበል ረጨት ረጨት ቢደረግበት ደግ ነው። ምናለ በድምፅ ብቻ በራድዮ በሱ ስም የሆነ የቢቸግር ተዋናይ ቢናገርለት ኖሮ። አንዳንዴ ለሕዝባችን ክብር ሲባል የሚመጥን ውሸት ማሰናዳት ያስፈልጋል።
አቶ ሞላ አስገዶም ምላሱ እንደ ሰካራም እግር ከሃሳቡ እየተላጋች የራሱን ሀሳብ ስትጠልፍበትና ምላሱ ወደ ጉሮሮው ሲመለስበት ተንገዳግዶ እንደሚቆም ሰካራም ህ ህ እምህ ይልና ኮቱን እያስተካከለ አንገቱን ነቅነቅ ሲያደርግ ምላሱ ወደቦታዋ ትመለሳለች። ያኔ “አሄ ሄ የሰከርኩ መሰላችሁ?” እንደሚል ቀምቅሚ ምላሱ “ቅድም እንዳልኳችሁ” ትልና ቅድም ባልተናገረችው ርዕስ ላይ ዘው ትላለች። ያኔ ነብሱ መለስ ይላል መሰል የወሸት ፈገግታ ያሳይና ይወራጫል። ከዚያ በአዲስ መስመር የፃፉለትን ማስታወሻ አየት አድርጎ ቃላቱን ሲያዝረከርክ ያበቃል።
በነሲብ እየሰሩ በገፍ እየተበደሩ ወደ ገደል የሚያንደረድሩንን እናሸንፍ ዘንድ እውቀትም ጉልበትም አለን ትንሽ ብልህነት ከጨመርንባት ማሸነፋችን እውነት ነው።
በአዲሱ አመት በአንድ ደካማ ሰው የተተወነ ከርካሳ ድራማ አየን እንኳንም የሆነው ሁሉ ሆነ እንል ዘንድ ግን ወደድን:: እንዲያው እግዜሩ ራርቶላቸው ሞላን ነቀለላቸው እንጂ አብሯቸው የሚቆይ ቢሆን ኑሮ በእንዲህ ውሉ በጠፋ ፍሬከርስኪ መንዘባዘቡ ብቻ አሰልችቶ መሪዎቻችንና ታጋዮቹን በብስጭት አይገድላቸውም ነበር ትላላችሁ?
ደህና ያክርመና!
No comments:
Post a Comment