የተናገሩት ከሚጠፋ… ባለፈዉ መጣጥፌ “ቃል የእምነት ዕዳ ነዉ” ብዬ ጀምሬ “ቃላችን አይለወጥ” ብዬ ነበር የተለየኋችሁ። አለምክንያት አልነበረም እንዲህ ያልኳችሁ፤ በአንድ በኩለ ቃል መከበርም መከፈልም ያለበት ዕዳ ስለሆነ በሌላ በኩል ደግሞ ቀትር ላይ የገባዉን ቃል ሳይመሽ እንደ ጴጥሮስ ሦስቴ የሚክድ ብዙ ቃላ አባይ ሰላለ ነዉ። አገሬን ከወያኔ አጸዳለሁ ብሎ ቃል የሚገባ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዕዳ አለበት
።ዕዳዉ ደግሞ ገንዘብ ወይም ንብረት አይደለም። ቃሉን መጠበቅ ወይም ቃሉን ማክበር ነዉ። ደግሞም አንድ ሰዉ የተናገርዉን ቃል ሰብሮ የእምነት ባለዕዳ ከሚሆን ዕድሜ ልኩን የገንዘብ ባለዕዳ ቢሆን ይሻለዋል። የገንዘብ ዕዳ ቆይቶም ቢሆን ይከፈላል ወይም አበዳሪዉ ሊምረን ይችላል፤ የዕምነት ዕዳ ግን የማይሽር ጠባሳዉ እየቆረቆረን አብሮን ይኖራል እንጂ አይጠፋም። ማንም ሰዉ ለአገሬ ህይወቴን እሰጣለሁ ብሎ ቃል ሲገባ መሃላዉ ከህዝብና ከአገር ጋር ብቻ አይደለም፤ እንዳዉም የሰዉ ልጅ ቃል የሚገባዉ መጀመሪያ ከራሱ ጋር ነዉ
። ለራሱ የገባዉን ቃል የማያከብርና ቃሌ ቃል ነዉ ብሎ የገዛ ራሱን የእምነት ዕዳ ያልከፈለ ሰዉ ለህዝብና ለአገር ቃል መግባት አይችልም። ዛሬ ወያኔን እናጥፋ ብሎ ካራ ጨብጦ አብሮኝ የቆመ ሰዉ ነገ ከወያኔ ጋር ሆኖ ካራዉን እኔዉ ላይ አዙሮ ባየዉ እሱ ቀድሞዉንም ካራ የጨበጠዉ ወያኔን ለማጥፋት ሳይሆን ስጋ ሊቆርጥብት ነዉና ብዙ አይገርመኝም። እንዲህ አይነቱን ለቁም ነገር ሲፈልጉት አልሰማ ብሎ ሆዱ ሲሞላለት ግን ሳይጠሩት አቤት የሚል ስጋ ወዳድ ሆዳም ደግሞ ኢትዮጵያ በየዘመኑ አፍርታለችና ብዙ ሊገርመን አይገባም። ከሰሞኑ ከምድረ ኤርትራ የነፈሰዉ ነፋስ ያስተማረን አንድ ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር እንዲህ አይነቱን ሞላ ጎደለ የሚባል የካራና የስጋ ጨዋታ ነዉ። አዎ! የካራ ጨወታ – ወዲህ ማዶ ስጋ ሊቆርጡበት ወዲያ ማዶም ስጋ ሊቆርጡበት። “የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” . . . ገዢዎቻችን በተለይ የዛሬዎቹ ቃል አባዮች እንደቆሻሻ ዕቃ መሬት ላይ ጣሉት እንጂ ቃል የዕምነት ዕዳ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ዘመን አይሽሬ የአገራችን አባባል ነዉ። አባቶቻችን የተናገሩትን ወይም ቃል ገብተዉ የተማማሉትን ነገር ከሚያጥፉ የወለዱትን ማጣት ይቀላቸዋል። እኛ ልጆቻቸዉ ግን ከዬት የመጣን ጉዶች አንደሆንን አላዉቅም ቃል አባይነታችን እኛን፤ ልጆቻቸንና አገራችንን ሲያጠፋ በአይናችን እያየን ቅር እንኳን አይለንም። “እመጣለሁ ብሎ ሰዉ እንዴት ይዋሻል፤ ማበል እንኳን አንቺን ምድር ያበላሻል” መሬት ላይ ጠብ የማይል ትክክለኛ አባባል ነዉ። አገራችን ኢትዮጵያ ትናንት እንሞትልሻለን ብለዉ ዛሬ በሚገድሏት ቃል አባይ ልጆቿ እየተበላሸች ነዉ። እነዚህ ቃልአባዮች የኢትዮጵያን የምድር ላይና የምድር ዉስጥ ኋብቷን አንጂ የገረጣዉን ፊቷን ማየት አይፈልጉም- አዎ ወያኔ የሚያየዉ ኃብትሽን፤ የሳዑዲዉ ሰዉ ወርቅሽን፤ ባዕድ ከበርቴዉ ለምለም መሬትሽን . . . ወይኔ ኢትዮጵያ ማን ይሆን የሚያየዉ የጠቆረዉ ፊትሽን፤ ማን ይሆን የሚያብሰዉ እምባሽን፤ እኮ ማን ይሆን የሚያቆመዉ መከራሺን . . . ማን ይሆን?. . . ማን ይሆን? የዛሬዋ ኢትዮጵያ አንድ ትዉልድ ዉሸት ብቻ እየሰማ ያደገባት የዉሸት መዲና ሆናለች። ጳጳሱ፤ ቄሱና ፓስተሩ “እኔ መንገድ፤ አዉነትና ህይወትና ነኝ” ያለዉን የሰማዩን አምላካቸዉን ረስተዉ ለምድር ዉሸታሞች አደሩ። ሂዱና ዋሹ ሲባሉ ሄደዉ ዋሹ፤ እዉነትን በዉሸት አስተባብሉ ሲባሉ አስተባበሉ፤ በሀሰት መስክሩ ሲባሉ አፋቸዉን ሞልተዉ በሀሰት መሰከሩ። “ታላቁ መሪ” እየዋሸን ኖሮ እየዋሸን ሞተ። መታወቂያዉ ዉሸት ነዉና ሞቶም አልሞተም ተብሎ ተዋሸለት። ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር ምን ለምዳ ትመጣለች እንዲሉ ሌላ ሁሉ ቢቀር ዉሸትን ይፀየፋል ተብሎ የተነገረለት የዛሬዉ ጠ/ሚኒስቴር ጭራሽ “ታላቁን መሪ” እንደዋቢ እየጠቀሰ ስራዉ ሁሉ ዉሸት፤ ዉሸት፤ ዉሸት ብቻ ሆኖ ቀረ። የኢትዮጵያ ሬድዮ ሲከፈት ዉሸት ይናገራል፤ ሲዘጋ ደግሞ ነገ ስለሚዋሸዉ ዉሸት ያስባል። ጋዜጦች በስህተት አንኳን እዉነት አይጻፍባቸዉም። የኢቲቪ ዜና አንባቢ ተመስገን በየነ ግማሽ ሰዐት የዋሸዉን ዉሸት ለማካካስ ዜናዉን አንብቦ ሲጨርስ ለ15 ደቂቃ ጎንበስ ብሎ ይሰግዳል። ለረጂም ግዜ ተማምነን ጀርባችንን የሰጠነዉ ሰዉ ለጠላት እጁን ሰጥቶ ጦርነት ሲያዉጅብን አንዳንዴ በትግሉ ዉስጥ ማንን አምነን ጀርባችንን እንደምንሰጠዉ ግራ ሊገባን ይችላል። ከሰሞኑ የሰማነዉ ዜና እንዲህ ግራ የሚያጋባ ዜና ነዉ። ሆኖም ሳንተማመን ትግል ብሎ ነገር የለምና የትግል ጓዶቻችንን ማመን ብርታት እንጂ ደካሞች እንደሚሉት ሞኝነት ወይም የዋህነት አይደለም። በጓዶቻችን ላይ ክህደት ፈጽመን ከምናሰቃያቸዉ እኛ ብንሰቃይ ይሻላል፤ ደግሞም ጓዶቻችንን ማመን አቅቶን በጥርጣሬ ተፋጥጠን ባለንበት ከምንረግጥ አንዳንዴ አዉቀንም ቢሆን ብንታለል ብዙ መንገድ መጓዝ እንችላለን። ትግል በተለይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ከሚያስተምረን ትምህርቶች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ሌሎች በኛ ላይ እምነት እንዲኖራቸዉ ከፈለግን እኛ አስቀድመን ልናምናቸዉ አንደሚገባን ነዉ። አለዚያ ሁለታችንም አንተማመንም። አለመተማመን ደግሞ ያጠፋፋናል እንጂ አንድ ቤት ዉስጥ አብሮ አያኖረንም። እንደኔ እንደኔ የወያኔን ስርዐት ደምስሰን ኢትዮጵያን የእኩሎች አገር የምናደርጋት እያንዳንዳችን ለትግል ጓዶቻችን የገባነዉን ቃል ሰብረን ረጂም ህይወት ከመኖር ቃላችንን አክብረን ዛሬዉኑ መሞትን ስንመርጥ ብቻ ነዉ። ወያኔ አንደ እሳት የሚፈራዉና በፍጹም የማያሸንፈዉ አንዲህ አይነቱን ከብረት የጠነከረ ጽኑ አቋማችንን ብቻ ነዉ። ለዚህ ነዉ እንዲህ አይነት ጽናት የሌላቸዉን ደካማ ግለሰቦች ፈልጎ እያማለለ ጽናታችንን የሚፈታተነዉ። ከሰሞኑ ለህዝብ ከመታገል ህዝብን መታገል መርጦ ከለየላቸዉ የህዝብ ጠላቶች ጋር የተቀላቀለዉ ሞላ አስገዶም ለዚህ ዉሳኔ የበቃዉ ህዝባዊዉ ትግል የሚፈልገዉ የአለማ ጽናት የሌለዉ ደካማ ግለሰብ ስለሆነ ብቻ ነዉ። ዉድ ኢትዮጵያዉያን ክህደት ትናንት ነበር፤ ዛሬ አለ፤ ነገም ይኖራል። ስለዚህ ክህደት ሊያስተምረን እንጂ በፍጹም ሊያስበረግገንና አንገታችንን ሊያሰደፋን አይገባም። ክህደትና ከሀዲዎችን እያሰላሰልን የምንኖር ከሆነ የበለጠ እንዲጎዱን ተጨማሪ ዕድል እንሰጣቸዋለን እንጂ ሌላ ምንም የምንፈይደዉ ፋይዳ የለም። ሞላ አስገዶም እሱን የመሰሉ ደካማ ጓደኞቹን ከተቀላቀለ በኋላ መቀሌ፤ አዲስ አበባና አዳማ ዉስጥ ክህደቱን አስመልክቶ እርስ በርሳቸዉ የሚጣረሱ ሦስት ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ሰጥቷል። እርግጠኛ ነኝ ይህ ቁርስ ላይ የተናገረዉን ምሳ ላይ የማያስታዉስ ግለሰብ በተያዘለት የጉብኝት ሰሌዳ መሠረት ዘጠኙን ክልሎች የሚዞር ከሆነ ዘጠኝ የተለያዩና እርስ በርሳቸዉ የሚጣረሱ ምክንያቶችን መደርደሩ አይቀርም። የወያኔ የመረጃና የደህንነት መ/ቤት ተብዬዉም ቢሆን ምን ያህል የዉሸትና የጉራ ቤት ለመሆኑ መረጃ ብሎ የለቀቃቸዉን ዉሸቶችና ቱልቱላዎች መጥቀሱ ይበቃል። ለምሳሌ የመረጃና ስለላ ድርጅቱ ከአንድ አመት በላይ ከሞላ አስገዶም ጋር በሚስጢር ይሰራ እንደነበር ተናግሯል። ይህ እዉነት ከሆነ የደምህት ታጋዮች በዚህ አንድ አመት ግዜ ዉስጥ በወያኔ ታጣቂዎችና ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ለወሰዷቸዉ እርምጃዎች በተለይ እግር ኳስ ጨዋታ በመከታተል ላይ እንዳሉ ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር እንዳለ ለተደመሰሱት የኢትዮጵያ ወታደሮች ተጠያቂዉ ከሞላ አስገዶም ጋር ይሰራ የነበረዉ የወያኔ የመረጃና የስለላ ድርጅት ነዉ ማለት ነዉ። ሞላ አስገዶም ትናንት ከኛ ጋር ሆኖ እኛ ሲል ነበር፤ ዛሬ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጠለቶች ጋር ሆኖ እኛ ይላል። ይህ ሰዉ “እኛ” ሲል የሱ እኛ እነማንን እንደሚያጠቃልል አይታወቅም፤ እሱ እራሱም የሚያዉቀዉ አይመስለኝም። ሞላ አስገዶም ወያኔን እንደተቀላቀለ አፉን ሞልቶ ጥምረቱን የፈጠርነዉ “እኛ” ነን ብሎ ሲናገር በተደጋጋሚ ተደምጧል። ጥምረቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ህዝባዊ ትግሉ የደረሰበት የዕድገት ደረጃ ዉጤት ነዉ እንጂ ሞላ አስገዶም ስለፈለገዉ የሚፈጠር አለዚያ የሚቀር የሞላ አስገዶም የቤት ዉስጥ ዕቃ አይደለም። ደግሞም እንደ ሞላ አስገዶም ፍላጎት ቢሆን ኖሮ የደምህት ጥምረቱ ዉስጥ መግባት ለግዜዉም ቢሆን ሊዘገይ ይችል ነበር። ደምህት ጥምረቱ ዉስጥ ገብቶ አገር አድን የጋራ ንቅናቄዉ የተፈጠረዉ የደምህት ሠራዊትና ከሞላ አስገዶም ዉጭ ሁሉም የደምህት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከሌሎች ኢትዮጳያዉያን ወገኖቻቸዉ ጋር ሆነዉ በጋራ ለመታገል በመወሰናቸዉ ነዉ። የሞላ አስገዶም ፈርጥጦ ወያኔ ጉያ ዉስጥ የመሸጎጡ ዋነኛዉ ምክንያትም የዚህ ዉሳኔ ዉጤት ነዉ እንጂ የወያኔ መረጃና ስለላ ድርጀት ሚስጥራዊ ግንኙነት ዉጤት አይደለም። ሌላዉ እርስ በርሱ የሚጋጭ የወያኔ ዉሸት – በአንድ በኩል ሞላ አስገዶምና የደምህት ሠራዊት ሙሉ ትጥቃቸዉን እንደታጠቁ ጠቅልለዉ ወደ አገራቸዉ ተመለሱ የሚለዉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ቁጥሩ ወደ 700 የሚጠጋ የደምህት ሠራዊት ወደ አገሩ ተመለሰ የሚለዉ የተምታታ ዘገባ ነዉ። እዚህ ላይ የደምህትን ሠራዊት ብዛት መናገሩ አስፈላጊ ባይሆንም ግንዛቤ ማግኘት የፈለገ ሰዉ ግን ተመድ ያወጣቸዉን ሪፖርቶች መመልከቱ የሚበቃ ይመስለኛል። ደግሞም ሞላ አስገዶም አታልሎ መንገድ ካስጀመረዉ ሠራዊት ዉስጥ ገሚሱ ወደ ትግሉ ሜዳ ተመልሷል፤ የተቀረዉ ደግሞ ወደ ትግሉ ሜዳ ካልተመለስኩ እያለ ከሱዳን ባልስልጣኖች ጋር እየተደራደረ ነዉ። በነገራችን ላይ የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ ሞላ አስገዶም አታልሎ ሀምዳይት ከወሰዳቸዉ በኋላ ትግል ወይም ሞት ብለዉ ተመልሰዉ ከትግል ጓዶቻቸዉ ጋር ከተቀላቀሉ ጀግኖች ኢትዮጵያዉያን ጋር አብሮ ቡና ጠጥቷል። ጓዜን ጠቅልዬ ትግሎ ሜዳ ከመግባቴ በፊትም ሆነ ከገባሁ በኋላ የደምህት ስም በተነሳ ቁጥር አብረዉ የሚነሱ ሁለት መላምቶች አሉ። አንደኛዉ መላምት ደምህት የኤርትራ መንግስት ሆን ብሎ የፈጠረዉና ጭራሽ ኤርትራ ዉስጥ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎችን ተክቶ በመንግስታዊ ተቋሞች ጥበቃና ደህንነት ስራዎች ላይ የተሰማራ ድርጅት ነዉ የሚል መላምት ሲሆን ሁለተኛዉ መላምት ደግሞ ሞላ አስገዶም በኤርትራ መንግስት ድጋፍ ሁለተኛዉ መለስ ዜናዊ ሆኖ ህወሃትን ተክቶ አትዮጵያን ይመራል የሚለዉ መላምት ነዉ። ደግነቱ የነዚህ መላምቶች የማዕዝን ራስ የሆነዉ ሞላ አስገዶም ኮብልሎ ወያኔን መቀላቀሉና ከተቀላቀለ በኋላ የሰጣቸዉ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ሁለቱንም መላምቶች እንዳልነበሩ አድርጓቸዋል። እኔን አልገባ ያለኝና በጣም የሚገርመኝ ግን በአንድ በኩል የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች ትብብር እንዲፈጥሩ አይፈልግም ይባላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጥምረቱ የተፈጠረዉ በሻዕቢያ ግፊት ነዉ ይባላል። መቼም ገና በልጅነቴ ካልጃጀሁ በቀር ሻዕቢያና የኤርትራ መንግስት መሃል ልዩነት ያለ አይመስለኝም። ሌላዉ የሰሞኑ አስቂኝ ድራማ ደግሞ ሞላ አስገዶም ጥምረቱን የፈጠርነዉ እኛ ነን ሲል የሱን መኮብለል አስመልክቶ የሚሰጠዉ አስተያያት ደግሞ ሞላ አስገዶም ጨርቁን ጠቅልሎ ወያኔን የተቀላቀለዉ ብርሀኑ ነጋ በኤርትራ መንግስት ግፊት የጥምረቱ ሊ/መንበር መሆኑ አልዋጥ ብሎት ነዉ ይባላል። ሌላዉ አሁን በቅርቡ ወይም ከሞላ አስገዶም መኮብለል በኋላ የተጠነሰሰዉ መላምት ደግሞ ደምህቶች እራሳቸዉ ኤርትራ ዉስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ድርጅቶች በወያኔ ስርዐት ላይ ወታደራዊ እርምጃ መዉሰድ እንዳይችሉ ሆን ተብለዉ በወያኔ የተፈጠሩ እንቅፋቶች ናቸዉ የሚለዉ መላምት ነዉ። በኔ ግምት ይህኛዉ መላምት ከሁሉም መላምቶች የከፋና እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ ጽንፈኛ መላምት ነዉ። እንደዚህ መላምት ፈጣሪዎች አባባል የትግራይ ህዝብ በህወሃት አመራር በደል አይደርስበትም ወይም የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ሆኖ የህወሃትን ግፈኛ ስርዐት አይታገልም ማለት ነዉ። እንዲህ አይነቱ ጭፍንነትና ጠባብነት የሚመነጨዉ ደግሞ ሞላ አስገዶምንና ደምህትን ወይም ህወሃትንና የትግራይን ህዝብ ለያይቶ ማየት ካለመቻል አባዜ ነዉ። በደርግ ስርዐት ዉስጥ ጭቆናዉና በደሉ በዛብኝ ብሎ ጠመንጃ ያነሳዉ ጀግናዉ የትግራይ ህዝብ ህወሃት ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወገኖቹ ተነጥሎ እንዲታይ ለማድርግ የሚሸርብበትን ሤራና የሚያደርስበትን ግፍና መከራ አፉን ዘግቶ የሚቀበልበት ምንም ምክንያት የለም። ስለዚህ ደምህት የትግራይ ህዝብ ብሶትና ምሬት አምጦ የወለደዉ ፀረ ህወሃት ንቅናቄ ነዉ እንጂ ወያኔ የፈጠረዉ ድርጅት አይደለም፤ሊሆንም አይችልም። ሞላ አስገዶምም ቢሆን የራሱ የተጠረቃቀመ ድክመት ከንቅናቄዉ ሊ/መንበርነቱ እንደሚያስነሳዉ ሲያዉቅ የፈረጠጠ ፈርጣጭ እንጂ እሱና ወያኔ እንደሚሉት የአንድ አመት ቀርቶ የአንድ ወርም ተከታታይ ግንኙነት አልነበራቸዉም። ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረከ ብቅ ብለዉ የጠፉትንም ሆነ ዛሬም ድረስ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች ባህልና ድርጅታዊ አሰራር ስንመለከት የድርጅቶች ህልዉና መመዘኛና የማንነታቸዉ መለኪያ ቆምንለት የሚሉት አላማ ሳይሆን የመሪዎቻቸዉ በተለይ የዋናዉ መሪ ተክለሰዉነት ነበር። የድርጅት ወይም የፓርቲ ሊ/መንበር ከድርጅቱ ባለይ ነዉ፤ እሱ ይሁን ያለዉ ይሆናል፤አይሁን ያለዉ አይሆንም። ብዙ ግዜ የድርጅት/ፓርቲ ሊ/መንበር ድርጅቱን የማፍረስ አቅም ጭምር አለዉ። ይህንን ደግሞ በቅርብ ግዜ ታሪካችን በተደጋጋሚ አይተናል። አንድን ድርጅት ወይም ፓርቲ አባላት ሲቀላቀሉ የሚመለከቱት የፓርቲዉን ሊ/መንበር እንጂ የፓርቲዉን የፖለቲካና የኤኮኖሚ ፕሮግራም አይደለም። የፓርቲ ሊ/መንበርም ቢሆን የኔ የሚላቸዉን ሰዎች ነበር እየመረጠ የሚያሰባስበዉ። እንደዚህ አይነቱ የፓርቲ አደረጃጀትና አሰራር አሁን እየተቀየረ የመጣ ቢሆንም ለረጂም ግዜ የፖለቲካ ትግላችን ችግር ሆኖ ቆይቷል። ሞላ አስገዶም በቅርቡ የደምህትን ሠራዊት ከነሙሉ ትጥቁ ይዤ ኢትዮጵያ ገባሁ ብሎ በድፍረት የተናገረዉ ንግግር ይሄዉ የድርጅት ሊ/መንበር ያሰኘዉን ሁሉ ማድረግ ይችላል የሚለዉ የቆየ የፖለቲካ ባህላችን በሽታ ተጠናዉቶት ነዉ። “ዝንጀሮዉን ከጫካ ያዉጡታል እንጂ ጫካዉን ከዝንጀሮዉ ዉስጥ አያወጡትም” የሚል ብህል አለ፤ ትክክለኛ ብህል ነዉ። ሞላ አስገዶም ህወሃት/ወያኔ የኢትዮጵን ህዝብ በአጥር እየለያየ በትናናንሽ ጎጆዎች ዉስጥ ማኖሩ አልዋጥ ብሎት ሁሉንም የሚያቅፍ ሰፊ ቤት ሰርተን ኢትዮጵያን የዲሞክራሲ አገር እናደርጋለን ብሎ ለብዙ አመታት የታገለ ሰዉ ነዉ። ችግሩ ሞላ አስገዶም ነዉ ከነዚያ ትናንሽ የወያኔ ጎጆዎች የወጣዉ እንጂ ትናንሽ ጎጆዎቹ ከሞላ አስገዶም ዉስጥ ስላልወጡ እንደ ማግኔት እየሳቡት ወደነበረበት ቦታ መልሰዉታል። ለሁሉም የሞላ አስገዶም ታሪክ ሲጻፍ – መጣና ሄደ ከሚሉ አምስት ሆሄያት የዘለለ ምንም ቁም ነገር የለዉም። እየመጡ መሄድና እየሄዱ መምጣት ደግሞ ትናንሽ ቤት የሚናፍቃቸዉ ትናንሽ ሰዎች እስካሉ ድረስ ይቀጥላል። ሁለት ሺ ሰባት ሊጠናቀቅ ሦስት ቀን ሲቀረዉ አንድ የብዙ ኢትዮጵያዉያንን ጆሮ የሳበ ዜና ቴሌቪዥኑን፤ ሬድዮኑን፤ ጋዜጣዉንና ድረገጹን ተቆጣጠረዉ። ዜናዉ የወያኔ/ህወሃትን ስርዐት በመሳሪያ ኃይል የሚታገሉ አራት ድርጅቶች አገር አድን የጋራ ንቅናቄ ፈጠሩ የሚል የአዲስ አመት የምስራች ነበር። የኢትዮጵያ ህዝብ ለረጂም ዘመን የናፈቀዉ የምስራች ነበር። ግን ምን ያደርጋል – በጥባጭ እያለ ንጹህ ዉኃ አይጠጣምና ይሀንን የአዲስ አመት የምስራች ሰምተን ሳናጣጥም ነበር የሞላ አስገዶምን ዜና ክህደት የሰማነዉ። አስደንጋጭ ዜና ነበር። በእርግጥም የአራት ድርጅቶች ጥምረት ተፈጠረ የሚል ዜና በተሰማ ማግስት የጥምረቱ ምክትል ሊ/መንበር ሠራዊት እየመራ ሄዶ ወያኔን ተቀላቀለ የሚል ዜና መስማት የሚያስደነግጥና በመጀመሪያዉ ዜና ላይ ቀዝቃዛ ዉኃ የቸለሰ ልብ ሰባሪ ዜና ነዉ። ደግነቱ ሁሉም ነገር ለበጎ ነዉ። የሞላ አስገዶም መክዳት ተራ ዜና ነዉ ማለቴ አይደለም። ግን ሞላ አስገዶምና የወያኔ መረጃ ድርጅት በትብብር ሠራነዉ ያሉት አዲስ ድራማ ተዉኔቱ ሳይጻፍ አየር በአየር የተከወነ ምናቡ ያልተባ ድራማ በመሆኑ ድራማዉ ከያኒዉን ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብና ለአንድነቱና ለነጻነቱ የሚታገሉ ልጆቹን በከፍተኛ ደረጃ የጠቀመ መሆኑን ማሳዉቁ አስፈላጊ ይመስለኛል። ደምህት በዚህ የወያኔ ድራማ ዉስጥ በእሳት ተፈትኖ ወርቅነቱን አረጋግጧል። ሞላ አስገዶም የደምህትን ሠራዊት ለወያኔ አስረከብኩ ብሎ በተናገረ ማግስት የደምህት መሪዎች የሰጡት አርቆ አስተዋይነት የታየበት አመራርና ያሳዩት ቆራጥነት የፖለቲካ ድርጅቶቻችን የደረሱበትን የዕድገት ደረጃ በግልጽ አሳይቷል። ደምህት እራሱም እንደ አንድ የትግል ድርጅት የተደቀነበትን አደጋና ፈተና በጣጥሶ በመዉጣት በትናንሾችና በደካሞች ሴራ በፍጹም የማይናጋ ጠንካራ ድርጅት መሆኑን በተግባር አሳይቷል። የዛሬዉ ደምህት ዉስጡን ከአድርባዮች ያፀዳ ሁለትና ሦስት እርምጃዎች ወደፊት የተራመደ ጠንካራ ድርጅት ነዉ። እርግጠኛ ነኝ ይህ የደምህት መሪዎች ያሳዩት አስተዋይነት፤ ጽናትና ቆራጥነት እኔ የምፈልገዉ ነገር ካልሆነ ድርጅቱን በአፍጢሙ እደፋዋለሁ ብለዉ ለሚያስቡ ዕብሪተኛ መሪዎች ጥሩ ትምህርት ነዉ። ሌላዉ የሞላ አስገዶም ክህደት በግልጽ ያሳየን ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ የሀዝብ መብትና ነጻነት ይከበር በሚሉ የነጻነት ሀይሎችና ህዝብን ረግጠን እንገዛለን በሚሉ ፀረ ህዘብ ሀይሎች ለሁለት መከፈሉን ነዉ። ወደድንም ጣላን ካሁን በኋላ ያለን አማራጭ ሁለት ብቻ ነዉ፤ ወይ ወያኔ ሆኖ ከህዝብ ጋራ መዋጋት ወይም ከህዘብ ጋር ሆኖ ወያኔንና ስርዐቱን መዋጋት። ሞላ አስገዶም ጎራዉን ለይቷል፤ እኛም ጎራችንን እንለይ። መኃል ቆሞ መመልከት አብቅቷል። ጠላቴን አግዝፌ መመልከት አልወድም፤ ትንሽ ነዉ ብዬም ጠላቴን በፍጹም አልንቅም። በቅርቡ የወያኔ የመረጃና ደህንነት መ/ቤትና ሞላ አስገዶም ከአንድ አመት በላይ አብረን ሠራን ያሉትን የጀማሪዎች ስራ ስምለከት ግን ወያኔ/ህወሃት “የምትሰሩትን ብቻ ሳይሆን የምታስቡትን ጭምር የሚያይ አይን አለኝ” እያለ የኢትዮጵያን ህዝብ ከማስፈራራት ዉጭ የረቀቀ የመረጃ ስራ መስራት ቀርቶ አረፍተነገሮችን አገጣጥሞ ለጆሮ የሚጥም ንግግር ማድረግ የሚችል አዋቂ የሌለበት የባዶዎች ድርጅት መሆኑን ነዉ የተረዳሁት። ሞላ አስገዶምም በወዶገባነት ሄዶ የተቀላቀለዉ ይህንኑ አዋቂ የሌለበትን እሱን የመሰለ ድርጅት ነዉ። ይህንን ደግሞ እስከዛሬ በሰጣቸዉ ቃለመጠይቆች በግልጽ አይተናል። ህወሃት/ወያኔን እስከዛሬ በሥልጣን ላይ ያቆዩት ሁለት ነገሮች ቢኖሩ አንዱ ጠመንጃ ሁለተኛዉ የኛ የነጻነት ኃይሎች መበታተን ብቻ ነዉ። ነገ የምንፈልጋት ኢትዮጵያ እንደ መኪና ተገጣጥማ አትጠብቀንም – የዛሬዉ ጥረታችንና ድካማችን ዉጤት ናት። ኢትዮጵያና ህዝቧ ከወያኔ ሲፀዱ የሚነፍሰዉ የነጻነት አየር ሁላችንንም ቢያስደስትም ደስታዉ የሚገለጸዉ በግለሰብ ደረጃ ነዉ። ዛሬ ከጠላት ጋር ተፋልመን የተቀማነዉን ነፃነት ማስመለስና እንደገና እንዳንቀማ ነቅቶ መጠበቅ ግን የሁላችንም የጋራ ሀላፊነት ነዉ። እንግዲህ ወገን ወገባችንን ጠበቅ የምናደርግበት ግዜ አሁን ነዉና ሁላችንም በየተሰለፍንበት መስክ እንበርታ። ጠላታችን ጠንካራ መስሎ የሚታየዉና ያለ የሌለ ጡንቻዉን የሚያሳርፍብን የማይቀረዉን ድል ማሽተት ስንጀምር ነዉ። የድል መአዛችንን የምናሸትበት ግዜ ደግሞ ሩቅ እንዳይመስለን ነገና ከነገ ወዲያ ነዉ። ከወላዋይና እዚህም እዚያም እየዘለለ ከሚያዘናጋን አጉል ጓደኛ አንዱኑ የለየለት ጠላት ይሻላልና የሞላ አስገዶም ክህደት ትግላችንን ሊያጠራዉና መንገዳችንንም ሊያሳጥረዉ ይገባል እንጂ በፍጹም ግራ ሊያጋባን አይገባም። አይዞን. . . ሞኝ ከዘመዱ ከሚያገኝዉ ጥቅም አዋቂ ከጠላቱ የሚያገኘዉ ጥቅም ይበልጣልና ጠላቶቻችን የፈጠሩልንን አጋጣሚዎች ሁሉ በሚገባ እንጠቀምባቸዉ እንጂ ለጠላት አንመቻች። ጠላታችን እየተሳሳተልን ነዉ፤ ጠላት ሲሳሳት ማቋረጥ ነዉር ነዉ። ቸር ይግጠመን!!! አፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር - See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46859#sthash.mBYG3Uqj.dpuf
No comments:
Post a Comment