ኮለኔል ባጫ ሁንዴ በአንቦ አካባቢ በጊንጪ ከተማ ተወለዱ ።በአምቦ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በ1965 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በኢትዮጵያ አየር ሃይል በአውሮፕላን ጥገና አገራቸውን ለማገልገል ተቀጥረው ስልጠናቸውን እንደጨረሱ ከክፍላቸው ያመጡት ውጤት የላቀ በመሆኑ እና የተዋጊ አውሮፕላን በራሪ ለመሆን ባሳዩት ከፍተኛ ፍላጎት ሙያው የሚጠይቀውን ማንኛውንም መስፈርት በማሟላት ወደ በረራ ትምህርት ቤት ገቡ ።
የሚፈለግባቸውን የበረራ ትምህርት እንደጨረሱ ወደ ተዋጊ ስኳድሮን በመመደብ የኤፍ 86 አውሮፕላን ሲበሩ ቆይተው የኢትዮጵያ አየር ሃይል F-5E የሚባል አዲስ አውሮፕላን ሲገዛ ወደ አሜሪካን አገር ተልከው በዚሁ አውሮፕላን ስልጠና በመውሰድ እና በማጠናቀቅ ወደ አገራቸው ተመልሰው በወቅቱ አገራችንን የወረሩትን የሱማሌ ወራሪዎች ጋር ፍልሚያ ውስጥ በመግባት በአየር ላይ ውጊያ ሁለት የሱማሌ ሚግ አውሮፕላኖችን መትተው የጣሉ ሲሆን በዚህም ላሳዩት ከፍተኛ ጀግንነት ከኢትዮጵያ መንግስት የጦር ሜዳ የላቀ ጀግንነት ሜዳይ ተሸላሚ ሆነዋል።
ኮለኔል ባጫ ሁንዴ በአየር ሃይል ሰራዊት ዘንድ እንዲሁም በጓደኞቻቸው በጣም ተወዳጅ ከነበሩት መካከል እና በስራቸውም አሉ ከሚባሉት የተዋጊ አውሮፕላን አብራሪዎች አንዱ እንደነበሩ ይታወቃል።
ኮለኔል ባጫ በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ መንግስት አስተዳደር ባለመደሰት በ1986 ሲሲና የምትባል አውሮፕላን በማብረር ወደ ሱዳን ተሰደው በመጨረሻም ወደ አሜሪካ በመምጣት በሳንፍራንሲስኮ ከተማ ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ ኖረዋል።
ኮለኔል ባጫ የአንድ ሴት እና የሁለት ወንዶች አባት ሲሆኑ ሶስት የልጅ ልጅ ለማየትም በቅተዋል።
የኮለኔል ባጫ የቀብር ስነ ሥርዓት የፊታችን ቅዳሜ ኦክቶበር 3 (Oct 3, 2015) በሚኖሩበት ካሊፎርንያ ግዛት ልጆቻቸውና የቅርብ ጓደኞቻቸው በሚገኙበት ይፈፀማል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ማህበር በዋሽንግተን ዲሲ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እየተመኘ በመኮንኑ እረፍት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልፃል።
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46956#sthash.BNs02zwZ.dpuf
No comments:
Post a Comment