መስከረም ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ መንግስት የአለም ባንክ የቋንቋ አስተርጓሚውን ፓስተር ኦሞት አግዋን ጨምሮ አሽኔ አስቲንና ጀማል ኦማር ሆጀሌ የተባሉ ለጋምቤላ ህዝብ መብት መከበር የሚታገሉ ሰዎች የምግብ ዋስትናን በተመለከተ ለስብሰባ ወደ ናይኖቢ ኬንያ ሲያመሩ ቦሌ አለማቀፍ አየር ማረፊያ ላይ መያዛቸውን በመጥቀስ፣ ግለሰቦቹ የቀረበባቸው የሽብረተኝነት ክስ ውድቅ ሆኖ በአፋጣኝ እንዲፈቱ 6 አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የምግብ ዋስትናን በተመለከተ በአንድ የአገር ውስጥ እና በሁለት አለማቀፍ ድርጅቶች የተዘጋጀው ስብሰባ " የሽብርተኞች ቡድን ስብሰባ" የሚል ስያሜ ሰጥቶ ፣ በስበሰባው ላይ ለመሳተፍ የሚሄዱ 7 ሰዎችን ያሰረ ሲሆን
፣ ከእነሱ መካከል 4ቱ ተፈትተዋል ሲሉ ድርጅቶች በመግለጫው ላይ ጠቅሰዋል። መግለጫውን ያወጡት 6ቱ ድርጅቶች ሂውማን ራይትስ ወች፣ ብሬድ ፎር ኦል፣ ግሬይን፣ አኝዋ ሰርቫይቫል፣ ኦክላንድ ኢንስቲቲዩት እና እንክሉሲቭ ዴቨሎፕመንት ኢንተራንሽናል ናቸው። የብሬድ ፎር ኦል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሚጌስ ባውማን " ኢትዮጵያ ስለምትከተለው የልማትና የምግብ ዋስትና ፈተናዎች በግልጽ ውይይት እንዲካሄድ ማበረታታት እንጅ፣ በታዋቂ አለማቀፍ ተቋማት የተዘጋጁ ስብሰባዎችን ለመካፈል የሚሄዱ ሰዎችን በሽብረተኝነት መወንጀሉ" ጠቀሜታ እንደሌለው ገልጸዋል። ፓስተር ኦሞት በጋምቤላ ክልል የመካነ እየሱስ ቤ/ክርስቲያን ወንጌላዊ ሲሆኑ፣ ከአለም ባንክ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለመመርምር የአለም ባንክ የምርመራ ቡድን ላደረገው ምርምራ በአስተርጓሚነት ሰርተዋል። ፓስተር ኦሞት ከመታሰራቸው አንድ ሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው ሲገልጹ መቆዬታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል። ስብሰባውን ያዘጋጁት ብሬድ ፎር ኦል ወይም በአማርኛ ትርጉሙ " ዳቦ ለሁሉም" የሚባለው ድርጅት ስዊዘርላንድ ውስጥ የሚገኝ የፕሮቴስታንት የልማት ድርጅት ሲሆን፣ ግሬን የተባለው ድርጅት ደግሞ ስፔን ውስጥ የሚገኝ አምራቾችን ለመደገፍ የተቋቋም አነስተና ድርጅት ነው። አኝዋ ሰርቫይቫል ደግሞ በምእራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ማህበረሰቦችን ለመርዳት የተቋቋም በለንድን ተመዝግቦ የሚገኝ ድርጅት ነው። በናይሮቢ የተደረገው ስብሰባ ዋና አላማ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን በመጋበዝ ከአለማቀፍ ድርጅቶች ጋር የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ማድረግ ነበር። መንግስት ፓስተር ኦሞትን የጋምቤላ ነጻ አውጭ ንቅናቄ ተባባሪ መስራችና መሪ አድርጎ የሚመለከተው ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ካላቸው እስከ 20 አመት ሊፈረድባቸው ይችላል። ከእስረኞች መካካል ጀማልና ኦሞት በእስር ቤት ውስጥ መታመማቸው ተገልጿል። የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮ " የሶስቱ ሰዎች መታሰር መንግስት የነጻ አሳቢ ዜጎችን ለማፈን ሲያደርገው የነበረው አንድ የቅርብ ክስተት ነው" ካሉ በሁዋላ፣ አፈና፣ እስር እና የሃሰት የሽብረተኝነት ክሶች ነጻ አስተሳሰቦችን ለማፈን የኢትዮጵያ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ነው" ብለዋል። በመግለጫው እና በመንግስት የሽብርተኝነት ክስ ስማቸው የተጠቀሰው አቶ ኒካው ኦቻላ ለኢሳት እንደተናገሩት እርሳቸው የሚመሩት አኝዋ ሰርቫይቫል ለንደን ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኝና ከሽብርተኝነት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑን ጠቀስው፣ የኢትዮጵያ መንግስት የተምታታበት ይመስለኛል ብለዋል። ፓስተር ኦሞት በጋምቤላ ሰላም እንዲወርድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሰው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኒካው፣ ፓስተር ኦሞትም ሆነ ሌሎች እስረኞች ከጋምቤላ ህዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ ( ጋህነን) ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም ብለዋል። ከጋህነን ጋር በተገነኛ ከ300 በላይ ሰዎች ታስረው እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ኒይካው፣ ጋህነን ከኢህአዴግ ጋር ደርግን ለመጣል አብሮ ሲታገል መቆየቱን ተናግረዋል። አራዳ ፍርድ ቤት የነበሩ ዳኞች ሰዎቹ አላጠፉምና ይፈቱ ቢሉም ፖሊሶቹ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርተው ክሱን ሌላ ፍርድ ቤት መውሰዳቸውን አቶ ኒካው ተናግረዋል። በአሁኑ ሰአት በጋምቤላ መንግስት አለ ብሎ ማናገር እንደማይቻል ዳይሬክተሩ አክለው ተናግረዋል
No comments:
Post a Comment