Tuesday, December 6, 2016

የአውሮፓ ፓርላማ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ዶ/ር መረራ ጉዲና ለእስር የተዳረጉበት ምክንያት ግልፅ እንዲደረግ ጥያቄ አቀረበ ኢሳት (ኅዳር 27 ፥ 2009)


Related imageየአውሮፓ ፓርላማ የሰብዓዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ ዶ/ር መረራ ጉዲና ለእስር የተዳረጉበት ምክንያት ግልፅ እንዲደረግ ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄን አቀረበ።
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴው ሃላፊ የሆኑት ኤሊና ቫሌንሲያኖ በኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራሩ ላይ የሚመሰረት ክስ ካለ መንግስት ጉዳዩን ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ አሳስበዋል። ባለፈው ሳምንት ከአውሮፓ አባላት ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክርን ያካሄዱት ዶ/ር መረራ ጉዲናን ከጉብኝታቸው መልስ አዲስ አበባ በገቡ ጊዜ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
ይሁንና የአውሮፓ ህብረት፣ የአሜሪካ መንግስትና የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የዶ/ር መረራ ጉዲናን ለእስር መዳረግ ስጋትን እንዳሳደረባቸው እየገለፁ ይገኛል።
ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ላይ የአውሮፓ ህብረት የተለያዩ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ውሳኔን አስተላፎ የነበረው የአውሮፓ ፓርላማ ይህንኑ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቡም ታውቋል።
በፓርላማ የሰብዓዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ ሃላፊ የሆኑት ኤሊና ቫሌንሲያኖ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ለተቃውሞ አደባባይ በሚወጡ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ መሻሻል ባለማሳየቱ ውሳኔው በህብረቱ ዘንድ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አክለው አሳስበዋል።
ባለፈው አመት በኦሮምያ ክልል ሲካሄድ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአውሮፓ ፓርላማ አስቸኳይ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወስድ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል።
ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው የፓርላማው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ባለፉት አንድ አመታት በሰብዓዊ መብት ጥሰትና አፈና ዙሪያ ምንም አይነት መሻሻል አለመታየቱን አስመልክቷል።
የኦፌኮ አመራር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተላልፈዋል ተብለው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው ፖሊስ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜን ጠይቆ ፈቃድ እንደተሰጠው ታውቋል።
በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ምርመራ እየተካሄደባቸው የሚገኙት ዶ/ር መረራ በአውሮፓ ቆይታቸው ከሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ጋር በመሆን ለህብረቱ የፓርላማ አባላት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያን አቅርበዋል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከግንቦት 7 ጸሃፊ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር በመገናኘትና በጋራ መግለጫን በመስጠት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል ሲል ለእስር ተዳርገዋል ያለበትን ምክንያት ይገልጻል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ በበኩሉ አመራሩ ምንም የፈጸሙት ወንጀል አለመኖሩን በመግለጽ ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ አሳስቦት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር ሁለት የቅርብ የቤተሰብ አባላትም ለእስር መዳረጋቸውንና ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment