አባይ ሚዲያ
አቶ አለበል አማረ በጲላጦስ ወንበር ይቀመጡ ይሆን ?!
አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ እንዳይሆን…
(መስቀሉ አየለ)
ሰው በስነፍትረት አንድ ብሎ እንደ ማህበረሰብ በህገ ልቦና ሲኖር እንዲሆን የታዘዘው ትንፋሹ እስካለ ድረስ ለቃል ኪዳን ሚስቱ ታማኝ ሆኖ እንዲኖር ነበር። ነገር ግን ግዜው የወንዶች የበላይነት የገነነበት፣ ስርአተ አልበኝንት ልክ ያጣበት፣ የሰው ህይወት ተክለሃይሞኖት አጠገብ አውራ ጎዳና የጣለውን አሮጌ የካርታሜ በርሚል ያህል እንኳን ለአይን የማይቆረቁር ተራ ነገር በሆነበት በዚያ የጨለማ ዘመን፤ ያለዝሙት ምክንያት ሚስቱን የፈታ የሚል ህግ እንቅፋት ይሆንባቸው ነበረና ባሎች ሚስቶቻቸውን ሊፈቱ ሲፈልጉ ማድረግ የሚጠበቅባቸው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ሶስት የሃሰት ምስክር ፈልጎ ዝሙት ስ ትፈጽም አገኘናት ብሎ መክሰስ፤ በቃ፤ የሙሴ ህግ ለድርድር የሚቀርብ አልነበረምና እራሱዋን በማትከላከልበት ሁኔታ ባልገባት ነገር ተጠርንፋ በህግ ስም የሰዎችን ክፉ ምኞት ለመሙላት ሲባል ብቻ በዲንጋይ ተወግራ ትሞታለች። ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ “ባይሆን ስለ በድሉዋ የፍችዋን ወረቀት ስጡዋት” ብሎ ኢፍትሃዊነትን ለማስታርቅ ስለሄደበት የመንገድ እርቀት ክርስቶስ በመዋእለ ስጋዌ ሳለ ገልጦባቸው ነበረና።
የቀድሞው የአጋዚ ክፍለ ጦር አዛዥና በኋላም ጸረ ወያኔ ትግሉን እቀላቀለሁ ብሎ ወደ ኤርትራ ገብቶ የነበረው ኮሎኔል አለበል። በአባይ ቲዩብ በኩል በነገው እለት ቃለ መጠይቅ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ባለፈው ነሃሴ ወር ገደማ በእስራ ኤል ለሚገኘው መሬት ኢትዮ እስራኤል ራዲዮ እንዲሁ ቃለመጠይቅ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን በዙውን ክፍል የሸፈነው ከልጅነት እስከ እውቀት በተለይም ከወያኔ ጋር አንድ ብለው ጀምሮ እስከወጣበት ግዜ ድረስ ያለውን ነው ማለት ይቻላል። ቢያንስ አጋዚን ያህል የስርዓቱ አርመኔያዊ ገጽታ መገለጫ የሆነ፣ ገና “ሀ” ተብሎ ከተቋቋመበት ቀን ጀምሮ ህልቁ መሳፍርት ዜጎቻችንን በሞት ሰረገላ ሲያግዝ የነበረና በናዚው ጀስታፖ አምሳል የተፈጠረ የሞት ስኩዋድ ውስጥ በአመራር ሰጭነት እንደመሰራቱ አንድ ታማኝ ሎሌ ትንሽም ቢሆን የትም ደመ ከልብ ሆነው ስለቀሩት ወገኖቻችን አንድ ነገር እንኳን በጸጸት ይነግረን ይሆናል ብለን ስንጠብቅ እንደ ጲላጦስ እጁን በውሃ ታጥቦ ለማለፍ መሞከሩ ያሳዝናል።
ኤርትራ ውስጥ ስለነበረው ቆይታም ሆነ ባሁኑ ሰአት ስላለው ተሳትፎ ያለው ነገር እለ ማለት አይቻልም። አሁን ቃለ ምልልሱን የሚሰጠው ግን ለአባይ ቲዩብ መሆኑና አባይ ቲዩብ ደግሞ ሙሉ ግዜውን በምን አይነት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ላይ ተጥዶ እንደሚውል ላስተዋለና የወቅቱን የገባያ ግርግር ላየ ሰው ለዚኽ ሰው ቃለ መጠይቅ ሲጋብዙት ምን እንዲናገርላቸው ፈልገው ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ አይቸግርም። ትናንት ያለበደላቸው አማራ ስለሆኑ ብቻ ስለጨፈጨፋቸው ዜጎቻችን ጸጸት ተሰምቶት ንሳሃውን ሊያወርድ እንዲያወርድ ሳይሆን ይልቁንም ከተቻለ ለአማራ ወገኞቹ የተቆረቆረ በመምሰል ሚዲያው “መርሄ ነው” ብሎ በተነሳበት ወርድና ቁመና ልክ የሚሆን ወሬ በመፍጠር የድህረ ገጽ አቡዋራ ማስነሳት ቢቻል የሚል ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ መንገደኛ ስሌት ሊሆን እንደሚችል ከግምት በላይ መሄድ ይቻላል።
በንጹህ ኢትዮጵያዊያን ደም እጁ የተነከረውና የአጋዚ ክፍለ ጦር መስራችና አዛዥ የነበረው ኮሎኔሉ ድህረ ደርግ ወቅት በጎጃም ክፍለሃገር እና በሰሜን ሸዋ በወታደራዊ ክፍል ውስጥ ተመድቦ ባገለገለባቸው ልዩ ልዩ ቦታዎች ላይ ተመድቦ ሲሰራ ምን ያህል የመአህድና የመኢአድ አባላትን እንዳሳፈነና እንዳስገደለ በዚህም ስራው ባሳየው የሎሌነት ብቃት እንዴት አዲስ ወደሚዋቀረው አጋዚ ክፍለ ጦር ውስጥ እርሾ ሆኖ ያገለግል ዘንድ እድሉን እንዳገኘው በዚህ አጋጣሚ እድሉን ይጠቀምበትና እንደኑዛዜም ቢሆን ቢነግረን መልካም ነበር። ካልሆነም እንዲሁ ሞታቸው የውሻ ሞት ሆኖ የትም የቀሩትን የህልቁ መሳፍርት ንጹሃንን ወገኖቻችንን ሙሉ ስም ዝርዝር እና የሆነውን ሁሉ እንዳስፈላጊነቱ የሚለቀቅ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እንዲያውቀው ይሁን።
ከላይ እንደጠቀስኩት መሬት ኢትዮ እስራኤል ራዲዮ ላይ ምንም ነገር ሳይናገር እንዳለፈው ሁሉ ስለ ኤርትራ ቆይታው አደረኩ ብሎ ለመናገር የሚደፍረው ቅንጣት ነገር ይኖራል ተብሎ አይገመትም። አንድም ቀን ከአስመራ ከተማ ሳይወጣ በአንድ የቅርብ ዘመዱ የሚታዘዘውን ጦር በረሃ ወርዶ ሳያይ፣ በቅርብ ሆኖ ስልጠናም ሆነ አመራር ሳይሰጡበት ባጠቃላይ እመራዋለሁ የሚውለን ጦር ሳያውቀው በመጨረሻም ለምክትሉ እንኩዋን ሳያሳውቅ አሁን ወዳለበት ስካንዲኒቪያን አቅንቷልና።ዛሬ ራስን የተቀደሰ መስዋእትና ስለ ሌላው የተሰጠ ቤዛ አድርጎ ለማቅርብ ሲባል ብቻ ከእውነታዋ ያፈገፈች አንዲት ጠብታ ጥላሸት ብትኖር እኔ የሙሴን ያህል ትእግስት አልተሰጠኝምና “ባይሆን የፍችውን ወረቀት ጽፈው ይስጡት” እንደማልል ይልቁንም በዚህ በኩል እኔም ለባሰ ቀን ተብሎ የተቀመጠውን እብድ የሚያክል ዶሴ የማወጣውና በዝርዝር የምሄድበት አንባቢም እውነቱን እንዲረዳው እድሉን የምሰጥ መሆኑን እንዲታወቅ ይሁን። ሁለት ግዜ ለካ አንድ ግዜ ቁረጥ ይላሉ አበው።
No comments:
Post a Comment