Tuesday, December 27, 2016

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዝዋይ እስር ቤት ውስጥ በጽኑ ታሞ ባቱ ሆስፒታል ገባ

የሶስት ዓመት እስራት ተፈርዶበት በዝዋይ እስር ቤት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታህሳስ18 ቀን 2009 ዓ.ም በፀና ታሞ በአንፑላንስ ተጭኖ ዝዋይ በሚገኘው ባቱ አጠቃላይ ሆስፒታል መግባቱ ታውቋል።
በተደጋጋሚ ጊዜያት ከቤተሰቦቹ እና ሕጋዊ ጠበቃው ጋር እንዳይገናኝ ሲደረግ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ የእስር ቤቱ ወታደሮች ወደ ሆስፒታል ይዘውት በሚገቡበት ወቅት በአቅራቢያው የሚገኙትን ሰዎች እንዲርቁ አድርገዋል። በዚህም ምክንያት የተመስገን የሕመም ደረጃ ምን ያህል እና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ እንዳልተቻለ ቤተሰቦቹ ስጋታቸውን ገልፀዋል። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት እስካሁኗ ሰዓት ድረስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በቃሬዛ ተጭኖ ከገባበት ዝዋይ ባቱ ሆስፒታል ያልወጣ ሲሆን የሕመሙን ዓይነት ቤተሰቡ እንዲያውቁት አልተደረገም።

”የዛሬው የፈረቃ መሪ ሻለቃ ንጉሴ ጨምሮ ዝዋይ እስር ቤት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም እስከ ዛሬ በተመሰገን ላይ ለደረሰው እና ለሚደርሰው ነገር ሁሉ መንግስት ሙሉ ሃላፊነቱን ይወስዳል” ሲል የጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ ወንድም የሆነው ታሪኩ ደሳለኝ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከወራት በፊት የአመክሮ ጊዜውን ጨርሶ መፈታት ይገባው የነበረ ቢሆንም የእሱ መጽሐፍ እና ጹሁፎች አሁን ለተፈጠረው ሕዝባዊ እንቢተኝነት መቀስቀስ መንስዔዎች ናቸው በሚል ምክንያት ከሕግ አግባብ ውጪ በሕመም ላይ እያለ በኮማንድ ፖስቱ በእስር እንዲማቅቅ መደረጉ ይታወሳል።

1 comment: