Wednesday, December 21, 2016

ሞሮኮ የሚገኘው የሼክ አል አሙዲ ነዳጅ ማጣሪያ በፍርድ ቤት እንዲፈርስ ታዘዘ

የሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ኩባንያ የሆነው ኮራል ፔትሮሊየም ሆልዲንግስ 67 በመቶ ድርሻ በመያዝ የሚያስተዳድረውና በሞሮኮ ብቸኛው የነዳጅ ማጣሪያ እንደሆነ የሚነገርለት ሳሚር ግሩፕ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይፍረስ የተባለው ባጋጠመው የገንዘብ ቀውስ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡ የሞሮኮ መንግሥት 1.34 ቢሊዮን ዶላር የታክስ ዕዳ እንዳለበት አስታውቋል
http://amharic.abbaymedia.com
በቀን 200 ሺሕ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማጣራት አቅም ያለው ሳሚር ግሩፕ ባጋጠመው የፋይናንስ ቀውስ ሳቢያ፣ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ሥራ ለማቆም ተገዷል ያለው የሮይተርስ ዘገባ ሲሆን የሞሮኮ ፍርድ ቤትም ቀውሱን ተከትሎ ኩባንያው እንዲፈርስ ወስኗል፡፡ ኩባንያውን የማፍረስና በሽያጭ ወደ ሌሎች የማስተላለፍ ሒደት እንዲመሩ የንብረት ጠባቂ ግለሰብ በመሰየም ሽያጩ እንዲከናወን አዟል፡፡

የንብረት ጠባቂ ሆነው በፍርድ ቤት የተሰየሙት መሐመድ አል ከሪሚ ፍርድ ቤት ከዚህ በፊት ሰጥቶ የነበረው የሽያጭ ትዕዛዝ ላይ ማራዘሚያ መጠየቃቸውንና ፍርድ ቤቱም ጥያቄያቸውን መቀበሉን ለዜና አውታሩ ገልጸዋል፡፡
በሦስት ወራት ውስጥም ነዳጅ ማጣሪያውን የሚገዙ አካላት የግዥ ጥያቄ የሚያቀርቡባቸውን ሰነዶች በማስገባት፣ ደህና ዋጋ ለሰጠ ኩባንያ በሽያጭ እንደሚተላለፍ አል ከሪሚ አስታውቀዋል፡፡
ነዳጅ ማጣሪያው እስኪሸጥ ድረስ ለጊዜው ሥራ እንዲጀምር ለማድረግ ቢሞከርም እንዳልተሳካ ታውቋል፡፡ ይህም የሆነው ድፍድፍ ነዳጅ የሚያቀርብለት በመጥፋቱ እንደሆነ ከሞሮኮ የወጡ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡
ኩባንያው እንዲፈርስ ትዕዛዝ ከወጣበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሞሮኮ ፍርድ ቤት ሀብትና ዕዳው እየተጣራ እንደሚገኝ ሲታወቅ፣ ኩባንያውን ከመፍረስ ለመታደግ ከገንዘብ አበዳሪዎች ፋይናንስ ለማግኘት ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ሳይሳኩ መቅረታቸውም ተሰምቷል፡፡ ባንኮችን ጨምሮ በነዳጅ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት ለሳሚር ግሩፕ ገንዘብ እንዲያበድሩ ኮራል ሆልዲንግስ ሲያደርግ የነበረው ጥረትም እንዲሁ መና ቀርቷል፡፡
የሞሮኮ መንግሥት ሳሚር ግሩፕ ያልከፈው የ1.34 ቢሊዮን ዶላር (13 ቢሊዮን የሞሮኮ ድርሃምየታክስ ዕዳ እንዳለበት አስታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ አጠቃላይ ውዝፍ ዕዳ ስላለበት እንዲሸጥ ተወስኖበታል ተብሏል፡፡
ሼክ መሐመድ አል አሙዲ በሳዑዲ ንጉሣውያን በኩል የሞሮኮ ንጉሥን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በተደጋጋሚ በማነጋገር፣ የሞሮኮ መንግሥት ውሳኔውን እንዲለውጥ መጣራቸውን ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቢሊየነሩ ያደረጓቸው ሙከራዎች ባለመሳካታቸው ኩባንያቸው ተሸጦ ዕዳውን እንዲከፍል ሞሮኮ በመወሰኗ ገዥዎች እየተጠበቁ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በሼክ አል አሙዲ ዳይሬክተርነትና የቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመራው ኮራል ፔትሮሊየም ሆልዲንግስ ኩባንያ67.25 በመቶ ድርሻ እንዳለው የሚነገርለት ሳሚር ግሩፕ፣ ከዚህ ቀደም የሞሮኮ ፍርድ ቤት ያስተላለፈበትን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ቢልም ውድቅ እንደተደረገበት ተዘግቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከኩባንያው የሚፈልገው ውዝፍ ታክስና ሌሎች ዕዳዎችን ለማስከፈል የይፍረስ ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት፣ የኩባንያው የባንክ ሒሳቦችም እንዳይንቀሳቀሱ አግዶ እንደነበርም ታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment