Thursday, December 29, 2016

በቁማችን ተሸጠን እያለቅን ነው | ሊነበብ የሚገባው ጥብቅ መረጃ


‘ባህርዳር’ ተብላ የምትጠራው የካርጎ መርከብ
ለኢሃድግ ጽህፈት ቤት ለፓርላማ አባላት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሚመለከታቸው ሁሉ
የዛሬ 7 ዓመት ገደማ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደተለመደው አንድ አገርን ለውጪ ሰው የመሸጥ ወንጀል ፈጽመዋል። ይኸውም የባህረኛ ማሰልጠኛ ተቋም በኢትዮጵያ ባህርዳር እንዲገነባ በሚፈቀድበት ጊዜ ለ30 ዓመታት የዚህ ዓይነት ትምህርት ቤት በአገሪቱ ሌላ ማንም እንዳይገነባና ይህ ኩባንያ ብቻ እንዲሆን አገሪቱን ግዴታ ማስገባታቸው ነው።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው የበታች አካላት ይህንን ቢቃወሙም ማስፈራሪያ እየደረሳቸው የ30 ዓመቱ ጊዜ ወደ 15 ዝቅ እንዲል አስደርገዋል። ይህ ኩባንያ ይህ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ለፖሊስ እንኳን የማይፈቀድ እንደ ውሸት መመርመሪያ መሳሪያ እንዲያስገባ፣ የአገሪቱ ቀረጥ ከፋይ ያስገነባቸውን ትምህርት ቤቶችና ምርጥ ተማሪዎችን በመመልመልና ወደ ውጪ በመላክ ከፍተኛ የሆነ ጥቅም ከማጋባሱም በላይ፣ እነዚህን ልጆች በአብዛኛው በኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት ለማሰልጠን አንድ ሚሊዮን ብር የሚያህል እዳ በማስፈረም በመሰረቱ ባሪያ ሆነው እንዲሰሩ ያስገድዳቸዋል።

ከዚህ ትምህርት ቤት የወጡ ተማሪዎች ነጻነታቸውን ሙሉ በሙሉ ማጣታቸው ብቻ ሳይሆን በሄዱበት ቦታ ለመብታቸውና ለደህንነታቸው የሚቆረቆር ባለመኖር አስገድዶ እስከመደፈር የደረሱና ሰሚ ያጡ አሉ። ተማሪዎቹ በስነልቦና ላሽቀው እንዲወጡ አድርጎ እንዲያሰለጥን የተቀጠረው የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት ወታደር የነበረ ሰው ነው። የዛሬው ሌላ አገሪቱን የመሸጥ ዝግጅት። ይህ አልበቃ ብሎ በዚሁ ዘርፍ ሌላ ወንጀል ዛሬ ሊሰራ ዝግጅቱ አልቋል። ይኸውም የኢትዮጵያ የመርከብ ስራና ሎጂስቲክ ድርጅትን ለቻይና መሸጥ ነው።
ይህ በተለይ ለምን አደገኛ የሆነ ነገር እንደሆነ ከዚህ በታች እንገልጻለን።
የኢትዮጵያ የመርከብና ሎጂስቲክ ድርጅት ምንም እንኳን የተወሰኑ መርከቦች ቢኖሩትም፣ ዋና ገቢው መርከቦች አይደሉም። ገቢውን በሚከተለው አማካኝነት ያገኛል። አንድ እቃ ወደ ኢትዮጵያ በሚገባበት ጊዜ ያንን እቃ ጭኖ የሚያመጣ ድርጅት ፈቃድ ያለው መሆን አለበት።
በኢትዮጵያ ፈቃድ ያለው ብቸኛ ድርጅት የኢትዮጵያ የመርከብ ስራና ሎጂስቲክ ድርጅት ብቻ ነው። ይህ በህግ የተቀመጠ ነገር ነው። ብቸኛ ድርጅት በመሆኑም ያለውድድር የፈለገውን ገንዘብ መጠየቅ ይችላል። ግን ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ የመርከብ ድርጅት በቂ መርከቦች ስለሌሉት አንድ እቃ ለምሳሌ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ሲጫን ሌላ የመርከብ ድርጅት ያንን እቃ ለመጫን የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት ፈቃድ መጠየቅ አለበት። ያንን ፈቃድ ለመስጣት ድርጅቱ ከጫኙ የመርከብ ድርጅት ኮሚሽን ይቀበላል።
ይህን ኮሚሽን ደግሞ እቃውን የጫነው ድርጅት ወደ ባለ እቃው፣ ባለ እቃው ደግሞ ያንን ሂሳብ ወደ ተጠቃሚው የኢትዮጵያ ህዝብ ያስተላልፋል። ያ ማለት እያንዳንዱ ወደ አገር ውስጥ ከሚገባ እቃ የኢትዮጵያ የመርከብ ድርጅቱ ምንም አገልግሎት ሳይሰጥ የኢትዮጵያን ህዝብ እየቀረጠ ይኖራል። በዚህም ምክንያት ድርጅቱ ከአመት ዓመት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ትርፋማ እየተባለ ይነገራል። የድርጅቱ ሰራተኞች ደሞዝ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀርቶ በአውሮፓም የማይታለም ነው። እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር 100 000 ብርና ከዛ በላይ የሚከፈላቸው ሰራተኞች አሉ። የሚያሳዝነው ነገር ይህ ድርጅት አሁን ተላልፎ ለቻይና ለመሸጥ ዝግጅቱ አልቋል። ያ ማለት የቻይና ኩባንያ በብቸኝነት የኢትዮጵያን ህዝብ እየቀረጠ እንዲኖር ሙሉ ፈቃድ ይሰጠዋል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በንዲህ ዓይነት ሁኔታ መብቱ እየተሸጠ ነው። ይህንን ለማድረግ እንደተለመደው ቻይና ከፍተኛ የሆነ ጉቦ ለተወሰኑ ባለስልጣኖች እንደከፈለች ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ በቁማችን ከነልጅ ልጆቻችን ተሸጠን ከማለቅ የብኩላችንን ጩኸት ጩሁ ለማለት ተስፋ በመቁረጥ የጻፍነው ነው።

No comments:

Post a Comment