Tuesday, December 13, 2016

የሰሜን ጎንደር ዞን የጸረ ሽምቅ ዋና አዛዥ ኮማንደር ዋኘው አዘዘ፣ በነጻነት ሃይሎች እና በገዢው ፓርቲ ታማኝ ወታደሮች መካከል የሚደረገውን ውጊያ ተከትሎ ፣ በገዢው ፓርቲ በኩል ለደረሰው ሽንፈት ተጠያቂ ናቸው በሚል ከታሰሩ በሁዋላ ፣ በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ አመራሮች እየተገመገሙ ሲሆን፣ አመራሮች ለሁለት ተከፍለዋል።


ታኅሣሥስ ፬ (አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :
አንደኛው ወገን የኮማንደሩን መታሰር አጥበቆ እየተቃወመ ሲሆን፣ የህወሃት ድጋፍ አላቸው የሚባሉት አመራሮች ደግሞ ለሽንፈታቸው ኮማንደሩን ተጠያቂ በማድረግ መታሰራቸውን ደግፈዋል። ግምገማው የሚቀጥል በመሆኑ፣ የመጨረሻውን ውጤት እስካሁን ለማወቅ አልተቻለም። ምክትል አዛዡ የት እንደገቡ አለመታወቁን የሚገልጹት ምንጮች፣ የተወሰኑ ወገኖች አዛዡ ዜናውን እንደሰሙ ወታደሮችን ይዘው ጠፍተዋል ሲሉ፣ ሌሎች ወገኖች ደግሞ በጃኖራው ውጊያ ተገድለዋል ይላሉ። በዞኑ ከሚንቀሳቀሱት ከፍተኛ የደህንነት ሰዎች መካከል ጎሼ በመባል የሚጠራው ደህንነት ተይዞ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩንም ለማወቅ ተችሎአል። በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ የወረዳ አስተዳዳሪዎች መካከል የጠገዴ ወረዳ አስተዳደር ካሳሁን መኮንን፣ የምእራብ አርማጭሆ አስተዳዳሪ አቶ መሰንበት፣ የወገራ እና የመተማ አስተዳዳሪዎችም ተይዘው ታስረዋል። በሌላ በኩል አዲሱ የጎንደር ማረሚያ ቤት ሃላፊ ሆነው የተሾሙት ግለሰብ ስልጣኑን ለመረከብ ፈቀደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። የባህርዳር ማረሚያ ቤት ሃላፊም ከስልጣናቸው ተነስተዋል። በአማራ ክልል ከሚታየው የነጻነት ትግል መጠናከር ጋር በተያያዘ ፣ ህዝባዊ ትግሉን ይደግፋሉ ወይም ስርዓቱን ውስጥ ሆነው ይቃወማሉ የተባሉ የተለያዩ የብአዴን አባላት እርምጃ እየተወሰደባቸው ሲሆን፣ እርምጃው በማረሚያ ቤት ሃላፊዎች እና በፖሊሶች ላይ ማነጣጠሩን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። የባህርዳር ማረሚያ ቤት ሃላፊ ኮማንደር ውቤ ወንዴ የሰሞኑ ቅነሳ የጎበኛቸው ሲሆን፣ በምትካቸው የዳንግላ ከተማ ማረሚያ ቤት ሃላፊ ቦታውን እንዲይዙት ተደርጓል። በቅርቡ ከስልጣናቸው ተነስተው ለእስር የተዳረጉትን የሰሜን ጎንደር ዋና ማረሚያ ቤት ሃላፊ ኢንስፔክተር ልጃለም መሰረትን ይተካሉ ተብሎ የተሾሙት አቶ አየለኝ ቦታውን አልፈልግም በማለት ስልጣናቸውን መልሰዋል። አቶ አየለኝ በተሾሙ በሳምንት ውስጥ ስራውን አልፈልግም ማለታቸው ፣ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ከሚገኙት ከኮሌኔል ደመቀ ዘውዴ ጋር በተያያዘ ከህዝብ ጋር ለላመጋጨት በመፈልግ ነው። ኢንስፔክተር ልጃለም ኮሌኔል ደመቀ ተላልፈው እንዳይሰጡ እንዲሁም በእስር ቤቱ ጥቃት እንዳይደረስባቸው ሲከላከሉ ቆይተዋል። ኢንስፔክተር ልጃለም እስካሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን ጉዳያቸውን የሚይላቸው ሰውም አላገኙም። ኢንስፔክተሩን በእስር ቤት ለማቆየት የተፈለገው ኮ/ል ደመቀን ከጎንደር ከተማ አውጥቶ ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ ነው የሚሉ አስተያየቶች አሉ። ከሲቪል ተመርጠው የማረሚያ ቤቱ ሃላፊ ሆነው እንዲሰሩ የተሾሙት አቶ አየለኝ ቦታውን አልፈልግም ማለታቸውን ተከትሎ፣ የዳባት ማረሚያ ቤት ሃላፊ ቦታውን እንዲይዙት ተደርጓል። ሹም ሽሩና እስሩ እንደቀጠለ ባለቤት ሰአት ፣ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ባህርዳር ከተማ በሚገኘው ፓፒረስ ሆቴል እንዲሰበሰቡ ተደርጓል። ስብሰባው የተጀመረው ዛሬ ማክሰኞ ሲሆን፣ ለተከታታይ ቀናት ይቆያል ተብሎ ይጠበቃል።

No comments:

Post a Comment