- ”አቶ ሞላ አስገዶም ሱዳን ውስጥ ወደ አልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል።አብረውት የነበሩት ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ከሰላ ውስጥ ናቸው” ሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ
- ”ሞላ ከታጣቂዎቹ ጋር ኢትዮጵያ ገብቷል የሱዳን መንግስትን እናመሰግናለን” ፋና ራድዮ ።
የትግራይ ሕዝብ ንቅናቄ ድርጅት (ትህዴን) ሊቀመንበር አቶ ሞላ አስገዶም ከነበሩበት ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ማምለጣቸውን አርብ ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ተዘግቧል።ይህንኑ ዜና መስከረም 2/2008 ዓም የኢህአዴግ/ህወሃት ልሳንነቱ የሚነገርለት ራድዮ ፋና ”ራሱን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ በማለት የሚጠራው እና በኤርትራ ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረው የጦር ክፋይ ትናንት ወደ ሀገሩ ገባ።” በማለት ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳን ታዋቂ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ”ሱዳን ትሪቡን” የአቶ ሞላን ማምለጥ እና ኢትዮጵያን፣ሱዳንን እና ኤርትራን በምታዋስነው ሃምዳይት ከተማ አካባቢ ከኤርትራ ወታደሮች ጋር ግጭት እንደነበር እና የሱዳን ወታደሮች ሽፋን ሰጥተው ታጣቂዎቹ ትጥቃቸውን ለሱዳን ወታደሮች ማስረከባቸውን እና ወደ ሱዳን ከሰላ ግዛት በምትገኘው ዋድ-አል-ሂሉ ከተማ መወሰዳቸውን እና መሪዎቻቸው ወደ አልታወቀ የሱዳን ከተሞች መወሰዳቸውን ጋዜጣው አክሎ ያብራራል።
የአቶ ሞላ መጥፋት በኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ኤርትራ ላይ የሚፈጥረው አዲስ የፖለቲካ ትኩሳት
የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ሞላ አስገዶም ሁለት የፖለቲካ ትኩሳቶችን እንደ አዲስ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ።እነርሱም በሱዳን እና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻከር እና በትግራይ ተወላጆች እና በኤርትራውያን መካከል አዲስ የበቀል ስሜት ሊፈጥር የመቻሉ ድንገት ነው።
በሱዳን እና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻከር
በሱዳን እና በኤርትራ መካከል የነበሩ ይቆዩ ግንኙነቶች አንድ ጊዜ ሲሰምር ሌላ ጊዜ ሲደበዝዝ እና እንደ ኳታር ያሉ ሀገሮችን ሸምጋይነት እየጠየቁ ቀጥለዋል።ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ግን የአቶ ኢሳያስ እጅ ደቡብ ሱዳን ውስጥ መገኘት እና ለደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ከህወሃት ተቃራኒ መቆም ሁሉ ሱዳን ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲዋዥቅ አድርጎታል።
ይህ በእንዲህ እያለ ነው እንግዲህ ከኤርትራ አምልጠው ሱዳን ከሰላ ግዛት ገብተው እና በሱዳን ወታደሮች ተደግፈው እንደ ፋና አገላለፅ ኢትዮጵያ ገቡ የተባሉት የአቶ ሞላ ጉዳይ የሳምንቱ መጨረሻ ወሬ የሆነው።ይህ ማለት ሱዳን ቀድሞውንም ከሀወሃት ጋር ተነጋግራ ነበር ማለት ነው? ያልተነጋገረች ቢሆንስ ከኤርትራ እየተፈለገ መሆኑን ያወቀች ግለሰብን ኤርትራ ውስጥ ምን አይነት የፀጥታ ችግር እንደፈጠረ ሳታውቅ ለኢትዮጵያ አሳልፋ ትሰጣለች ማለት ነው?
በእዚህም በኤርትራ ላይ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚስጥር የደረሰችው ስምምነት አለ ማለት ነው? እነኝህ እና ሌሎች ጥያቄዎች በሙሉ በሱዳን እና በኤርትራ ማካከል የነበሩ ግንኙነቶችን የሚያጎድፉ ናቸው።በተለይ ሱዳን ላደረገችው አስተዋፅኦ ምስጋና አቀረበ የተባለው የህወሃት መንግስት በኤርትራ እና ሱዳን መካከል አዲስ ቅራኔ የሚፈጥር ነው።
ይህ ብቻ አይደለም በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ አዳዲስ አሰላልፍ የምትፈልገው አሜሪካ ከሱዳን ጋር የሚኖሩ ግጭቶች ለኤርትራ ከአሜሪካን ጋር ግንኙነት ለማደስ ጥረት እያደረገች ነው እየተባለ ሰሞኑን የሚነገረው ዜና አዲስ ኃይል ይጨምራል።ሱዳን እራሷን ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ ወገን ባለመሆን ገለልተኛነትን ለማራመድ ስለሚቸግራት አጣብቂኝ ውስጥ የመግባት እድሏ ትልቅ ነው።በእዚህ ሁሉ መካከል ግን ኤርትራ ውስጥ የመሸጉት የህወሃት ተቃዋሚ ኃይሎች አመቺ የመጠናከርያ ዕድል እንደተከፈተላቸው ለማወቅ ይቻላል።ይሄውም አቶ ኢሳያስ ሙሉ ኃይላቸውን በጸረ-ሱዳን እና ህወሃት መንገዳቸው ከኢትዮጵያ የነፃነት ኃይሎች ጋር በጠነከረ መንገድ እንዲቆሙ የሚያደርጋቸው ነው።
በትግራይ ተወላጆች እና በኤርትራውያን መካከል አዲስ የበቀል ስሜት ሊፈጥር የመቻሉ ድንገት
የአቶ ሞላን በሱዳን በኩል አድርጎ መሸሽ በተመለከተ ከህወሃት መንደር እና ከኤርትራ ተወላጆች በኩል የሚሰሙት በሁለቱ መካከል ያሉ እልሆች እና የበለጠ መካረር ተከስቷል።ህወሃት በመንደሩ ለአንድ ዓመት ያህል የሰራሁት ”ኦፕሬሽን” ነው የሚል እና ”አቶ ኢሳያስ ስር ሆነን አቶ ኢሳያስን ጉድ ሰራናቸው” የሚል ከበሮ ሲያሰማ በኤርትራ ተወላጆች በኩል ደግሞ በተለይ ጉዳዩን አስመልክተው ሃሳባቸውን በማህበራዊ ሚድያ የሚገልፁትን ስንመለከት በትግራይ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንደነበራቸው እና ቀድሞውንም ትግራዮችን ማስጠጋት አልነበረብንም የሚል መልክት ሲተላለፍ ለመመልከት ይቻላል።
በአንድ ማህበራዊ ድረ-ገፅ ላይ በተለይ አንዲት ኤርትራዊት እንደፃፈችው ”የአስመራን መንገዶች ያቆሸሸው ሞላ ከእነ ሰራዊቱ መልቀቅ ነበረበት እነርሱ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ በክብር ሊታዩ አይገባም ሌላው ኢትዮጵያዊ የሰለጠነ ነው፣ ወዘተ” የሚሉ ፅሁፎችን አስነብባለች።ይህ ሁሉ የሚያሳየን በ1990 ዓም ” የአይናችሁ ቀለም አላማረኝም ብለን ኤርትራውያንን የማባረር መብት አለን” ብለው ቃል በቃል የተናገሩት አቶ መለስ እና ንግግራቸውን ተከትሎ ከ70 ሺህ በላይ የሚሆኑ ንፁሃን ትውልደ ኤርትራውያን በግፍ ከተባረሩበት ድርጊት ጋር ተያይዞ እና አሁን አቶ ሞላ ምናልባትም (ገና ጉዳዩ በዝርዝር ስላልታወቀ) በትግራይነት ስሜት ብቻ ያስጠለሏቸውን ከድተው የመሄዱ ሂደት ቅራኔዎቹን ያባብሳሉ እንጂ ምንም አይነት የማብረድ ሁኔታን አያሳዩም።
በመጨረሻ ግን የአቶ ሞላ መሸሽም ሆነ ክህደት የሚያሳየው መጪው ጊዜ በኤርትራ የመሸጉትን የነፃነት ኃይሎች ጥንካሬን የሚያመጣ እንጂ ምንም አይነት ጉልህ ተፅኖ የለውም ማለት ይቻላል።ለእዚህም ምክንያቶቹ የትህዴንን ሰራዊት ጨምሮ አርበኞች ግንቦት 7፣የአፋር ንቅናቄ እና የአማራ ንቅናቄ በአንድነት ጥምረት መፍጠራቸው እና አቶ ሞላ ይብሱን የበለጠ ጉዳት በነፃነት ኃይሎች ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉበት ዕድል በአጭሩ መሰናከሉ የሚሉትን መጥቀሱ ይበቃል።ህወሃት መቼም ቢሆን በጊዜያዊ እይታ ላይ ብቻ መመርኮዙ እና ቀጥሎ የሚመጣውን የመመልከት ችግር ስለሚያጠቃው ከሰሞኑ ቀድሞ አሸባሪ ሲለው የነበረውን ”ሀገር ወዳድ” እያለ በማሞካሸት እና ሻብያ ያሰበውን አዲስ ሴራ አገኘሁ የሚሉ ፕሮግራሞችን በቲቪ ደጋግሞ በማሳየት የህዝብን የነፃነት ጥያቄ ለማድበስበስ ይሞክር ይሆናል።ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእሩብ ክ/ዝመን በላይ ይታለላል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።ላለፉት ሃያ አራት አመታት የነበሩ የህወሃት ተመሳሳይ የፕሮፓጋንዳ ዜማዎች አሁን ላይ ይሰራሉ ማለት ዘበት ነው።የሚሆነው ግን አቶ ኢሳያስም የበለጠ የኢትዮጵያን የነፃነት ኃይሎች የመደገፍ ሥራ በበለጠ እንዲገፉበት የኢትዮጵያ የነፃነት ሃሎችም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ የበለጠ ለነፃነት ትግሉ እንዲነሱ ከማድረግ ያለፈ አንዳች ፋይዳ አይኖርም።
ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
መስከረም 3/2008 (ሴፕቴምበር 14/2015)
- See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/10353#sthash.bcH1j8qA.dpuf
No comments:
Post a Comment