የዓመቱ ምርጥ ሰው በሚል አንባቢዎቿን በማሳተፍ ምርጫ ስታደርግ ይህ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው:: እስካሁን መምህር የኔሰው ገብሬ; ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ; ታጋይ አንዱአለም አራጌና አብርሃ ደስታ በተከተታይ ዓመታት የአመቱ ምርጥ ሰው ሽልማቶችን አግኝተዋል::
ዘንድሮ ለአንድ ወር ያህል ዘ-ሐበሻ የሕዝብ ድምጽን በስልክ; በቫይበር; በፌስቡክ; በኢሜይል እና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ስትቀበል ነበር:: በሺህዎች የሚቆጠሩ የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች የ2007 የዓመቱ ምርጥ ሰው ይሁንልኝ ሲሉ ድምፃቸውን የሰጧቸው ሰዎች በርካቶች ነበሩ:: የዘ-ሐበሻ ኤዲቶሪያል ቦርድ ሁሉም የሕዝብ ድምጽ ቆጠራ ካደረገ በኋላ የሚከተሉት 10 ሰዎች ከፍተኛውን ድምጽ አግኝተዋል::
1ኛ. አህመዲን ጀበል
2ኛ. አንዳርጋቸው ጽጌ
3ኛ. ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
4ኛ. አቶ ነአምን ዘለቀ
5ኛ. አቡነ መቃሪዮስ
6ኛ. ገንዘቤ ዲባባ
7ኛ. ቴዲ አፍሮ
8ኛ. ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋ
9ኛ. ወይንሸት ሞላ
10ኛ. ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ናቸው::
ከ10ሩ እጩዎች ውስጥ ከፍተኛውን ድምጽ ያገኙትን በየዘርፉ ከፋፍለን አቅርበናቸዋል:: በዚህም መሠረት የዘ-ሐበሻ የዓመቱ ምርጥ ሰው የሚከተሉት ናቸው::
የዓመቱ ምርጥ ሰው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
በዘ-ሐበሻ አንባቢዎች ዘንድ ከፍተኛውን ድምጽ ያገኙትና የአመቱ ምርጥ ሰው የተሰኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ናቸው:: “ካሁን በኋላ ሰዎችን ሰብስቤ ማውራት ላቆም ነው” ባሉ በሁለተኛው ቀን ለነፃነታችን እየወደቅን እንታገላለን ብለው ጥሩ ኑሯቸውን ትተው በርሃ ወርደዋል::
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በ1958 ዓ.ም ደብረዘይት አካባቢ የተወለዱ ሲሆን ምንም እንኳ የተወለዱት ከሃብታም ቤተሰብ ቢሆንም አስተዳደጋቸው ግን ራሳቸውን ችለው እንዲያድጉ እየተማሩ ነው:: ይህንን ፕሮፌሰር ብርሃኑ በሃገር ቤት ለሚታተም ጋዜጣ በ1997 ዓ.ም ሲናገሩ “አባቴ ነጋ ቦንገርን ልጅ እያለሁ ሲኒማ ራስ ጥሩ የህንድ ፊልም ወጥቶ ለማየት ሳንቲም ስጠኝ ስለው ራስህ ሰርተህ ስታገኝ ትገባለህ ይለኝ ነበር” (ቃል በቃል የተወሰደ አይደለም) ይላሉ:: አባታቸው አቶ ነጋ ቦንገር ሲያሳድጓቸው በማሞላቀቅ ሳይሆን ራሳቸውን መቻል እንዳለባቸው በማስተማር ነበር:: ይህም ለፕሮፌሰሩ ስኬት ጠቅሟቸዋል::
ፕሮፌሰሩ ወደ ሳሪስ አካባቢ ግሎባል የሚባል ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ከፍተው የነበረ ቢሆንም በሽብርተኛነት በኢትዮጵያ መንግስት ከተከሰሱ በኋላ ይህ ሆቴል ተወርሷል::
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ወደ ትግሉ ዓለም የገቡት ገና የ17 ዓመት ወጣት በነበሩበት ወቅት ነው:: ያን ጊዜ ከኢህ አፓ ጋር በሚሰሩበት ወቅት ብዙ ምስጢሮች ባይነገራቸውም መኪና ይነዱ ስለነበር የኢሕአፓ አመራሮችን ከቦታ ቦታ በመውሰድ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር አብረዋቸው ይታገሉ የነበሩ ሰዎች ለዘ-ሐበሻ ይናገራሉ:: እንዲሁም ፕሮፌሰር ብርሃኑ በወቅቱ በኢህአፓ አመራሮች እርምጃ ሊወሰድባቸው ሲል በሱዳን በኩል አምልጠው እንደጠፉ ከታሪካቸው ያሰባሰብነው መረጃ ያመለክታል::
በሱዳን በኩል አድርገው አሜሪካ ከገቡም በኋላ ትምህርታቸው ላይ በማተኮር በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ሲሆን ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ኢትዮጵያ ጠቅልለው በመግባት ሃገራቸውን ማገልገል ጀምረዋል:: ፕሮፌሰር በቅድሚያ ኢሕ አዴግን ለመለወጥ አዳዲስ ሃሳቦችን ቢያቀርቡም ኢህ አዴግ ግን የሚለወጥ ድርጅት ሊሆን አልቻለም:: በዚህም ተስፋ ሳይቆርጡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበርን በመመስረት ብዙ አስተዋጽኦ አበርክተዋል::
ከምርጫ 2007 በፊት ፕሮፌሰር ብርሃኑ እና ፕሮፌሰር መስፍን በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመሰብሰብ ስለ ነፃነትና መብት ምንነት በሰፊው በሕዝባዊ ስብሰባ ይሰብኩ ነበር:: በርካታ ተከታዮችን እያፈሩ መምጣታቸው ያስፈራው መንግስት ሁለቱንም ታዋቂ ፖለቲከኞች ሕገመንግስቱን በኃይል ለመናድ በሚል አስሮ ሲያንገላታቸው ቆይቷል::
ምርጫ 1997 እየቀረበ ሲመጣ በየወሩ በሂልተን ሆቴል ኢትዮጵያ በ2020 በሚል ምሁራን እየተሰባሰቡ ኢትዮጵያ በ2020 ዓ.ም ምን መሆን እንዳለባት እንዲመካከሩ ያደርጉ የነበሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በነበሩበት ወቅት ደመወዛቸውን ለችግረኛ ተማሪዎች ያከፋፍሉ እንደነበር ይነገራል::
ፕሮፌሰሩ ቀስተዳመና የተሰኘ ፓርቲ አቋቁመው ከኢድሊ ጋር በመተባበር ታላላቆቹን መኢአድና ኢዴፓ-መድህንን አንድ በማድረግ ቅንጅት ፓርቲ እንዲፈጠርና በምርጫ 97 ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዲፈጠር ጥረው ነበር:: በዚህም የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው በሕዝብ ተመርጠው የነበረ ቢሆንም መንግስት በሃይል ያመጣሁትን ስልጣን በስኪብርቶ አለቅም በሚል የፖለቲካውን ምህዳር ዘግቶታል::
በዚህ ምርጫ ሰብሰብም ፕሮፌሰር ብርሃኑ እስር ቤት ተወርውረው ነበር:: ከ እስር ቤት ከወጡ በኋላም ሰላማዊ ትግል ብቻውን ለውጥ አያመጣም በሚል ወደ ሁለገብ ትግል በመሸጋገር ግንቦት 7ን መሰረቱ:: ግንቦት ሰባት በአሁኑ ሰዓት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየተዋሃደ ትግሉ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲሸጋገር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሰርተዋል:: ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ2007 የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች የአመቱ ምርጥ ሰውን ክብር ስላገኙ እንኳን ደስ ያለዎ::
የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኛ – ገንዘቤ ዲባባ
የ23 ዓመቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የዘ-ሐበሻ የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኛ ሆናለች:: ገንዘቤ በ2007 ዓ.ም አመርቂ የሆነ ውጤትን አስመዝግባለች:: ባለፉት 8 ዓመታት የአትሌትነት ቆይታዋም በርካታ ድሎችን አጣጥማለች:: ገንዘቤን ዘንድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ በርካታ ትልቅ ስፖርተኞች መካከል የሚያደርጋት በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት የዓለም ክብረ ወሰኖችን መስበሯ ነው::
ባለፈው ጥር ላይ በስዊድን ስቶክሆልም ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ያለተሰበረውን የ3 ሺህ ሜትር ሩጫ ሪከርድ ሰብራለች:: እንዲሁም ይህን ድል ካጣጣመች ከ4 ቀን በፊትም እንዲሁ በ1500 ሜትርን ሪከርድ ሰብራለች:: አትሌት ገንዘቤ ዲባባ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው በፓሪስ የአምስት ሺህ የዳይመንድ ሊግ ውድድር በአንደኝነት ያጠናቀቀችውም በዚሁ በተሰናባችሁ 2007 ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር:: ሰኔ 27፣2007 ምሽት በተደረገው 8ኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ገንዘቤ ርቀቱን በ14 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ ከ41 ማይክሮ ሰኮንድ በመግባት ነበር ያጠናቀቀችው፡፡ ገንዘቤ የእህቷን ጥሩነሽን ክብረወሰን ትሰብራለች ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካላት ቀርቷል። የጥሩነሽ ክብረ ወሰን ለመስበር 4 ሰከንድ ብቻ ነበር የቀራት።
አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ሞናኮ ውስጥ በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ 1500 ሜትር አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ያስመዘገበችውም በዚሁ ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር::
ገንዘቤ በዚሁ በተሰናባችሁ 2007 ዓ.ም ቤጂንግ ላይ በተደረገው የዓለም ሻምፒዮና ላይ አንድ ወርቅ እና አንድ ነሃስ ሜዳሊያ ለሃገሯ ያስገኘች ጠንካራ አትሌት ናት:: የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኛ በሚል መርጠዋታል:: እንኳን ደስ ያለሽ::
የአመቱ ምርጥ አርቲስት – ቴዲ አፍሮ
ቴዲ አፍሮ “ሚስማር በመቱት ቁጥር ይጠብቃል” እንደሚባለው ሆኗል:: በመንግስት የሚደርስበት ጫና ይበልጥ ተወዳጅ እንዲሆን እያደረገው ነው:: በዚሁ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ላይ 70 ደረጃ የሚለውን ነጠላ ዜማ ከለቀቀ ወዲህ የሕዝብ ጆሮን አግኝቶ ነበር:: ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ውጭ ሃገር ለኮንሰርት ዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት ድንገት ፖሊሶች አስረውት ነበር:: ምክንያታቸውም ከዚህ ቀደም ቴዲ አፍሮ- ከዓመታት በፊት የጎዳና ተዳዳሪ ገጭቶ ገድሏል የተባለበት ቢኤምደብሊው የቤት አውቶሞቢል ቀረጥ ሳይከፈልበት የገባ ነው በሚል በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መርማሪ ቡድን በቁጥጥር ሥር ዋለ:: በ30 ሺህ ብር ዋስም ተለቀቀ:: የሚገርመው ይህ ክስ ከብዙ ዓመታት በፊት መመስረቱ ብቻ ሳይሆን መኪናው በአሁኑ ወቅት በአርቲስቱ እጅ አለመኖሩም ጭምር ነው::
ቴዲ አፍሮ በዚህ ዓመት ‘አልሄድ አለ’ እና ‘ኮርኩማ’ አፍሪካ የተሰኙ መል ዕክት ያላቸውን ተወዳጅ ዘፈኖቹን አበርክቶልናል:: ሁለቱም ዘፈኖቹ እጅግ ተወዳጅ ሆነውለታል::
በዚህ ዓመት በቴዲ አፍሮ ላይ ከፍተኛ ጫና የተደረገበት ሲሆን ከዚህም ውስጥ የአውሮፓው ኮንሰርቱ እንዲስተጓጎል የተደረገበት ነው:: ከሃገር ሊወጣ ሲል ፓስፖርቱን ከሕግ ውጭ በደህንነቶች የተቀማው ቴዲ በአውሮፓ ማቅረብ የነበረበትን ኮንሰርት በዚህ ሳቢያ በመሰረዙ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል:: በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሳይባል ደህነነቶች ‘ልክ እናስገባሃለን’ በሚል ፓስፖርቱን የተቀማው ቴዲ እየደረሰበት ያለውን ጫና ዘፈኑ ገልጾታል እየተባለ ነው:: “አልሄድ አለ” የሚለው ነጠላ ዜማውም ለራሱ የሰራው ነው እየተባለ ይነገራል::
ቴዲ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በአዲስ አበባ ላፍቶ ሞል ሊያቀርበው የነበረው ኮንሰርቱ በፖሊስ ምክንያት እንዲሰረዝ ተደርጓል:: ለስርዓቱ ቅርብ የሆኑት ማዲንጎ አፈወርቅ እና አስቴር አወቀ ኮንሰርት እንዲያቀርቡ ሲፈቀድ ቴዲ በመከለከሉ የተቆጡት ኢትዮጵያውያን ኮንሰርቱን በፌስ ቡክ ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል::
ቴዲ አፍሮ በዘ-ሐበሻ አንባቢዎች የአመቱ ምርጥ ሰው ሽልማትን አግኝቷል:: እንኳን ደስ ያለህ::
የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ – ሃብታሙ አሰፋ
የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋ ሆኗል:: የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር ከፍተኛ አመራር የነበረውና በሃገር ቤትም እንደነ መብረቅ/መብሩክ; ሩሕ; ሪፖርተር እና ሌሎችም ሚድያዎች ውስጥ ሲሰራ የነበረው ጋዜጠኛ ሃብታሙ በስደት ካይሮ ከቆየ በኋላ ወደ አሜሪካ ላስቬጋስ ከተማ ኑሮውን ካደረገ በኋላ ሕብር የተሰኘች ራድዮ መስርቶ ሙያውን ቀጥሎበታል::
ሃብታሙ አሰፋ ካለምንም የሕዝብ እርዳታ; በራሱ ጥረት በየሳምንቱ የሚያዘጋጃት ሕብር ራድዮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ ሆና በአሁኑ ወቅት እንደ አማራጭ የመረጃ ምንጭነት ተቀምጣለች:: ከኪሱ እያወጣ በየሳምንቱ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት ከሃገር ቤትም ሆነ ከውጭ ሃገር ቃለምልልሶችን በማቅረብ ለኢትዮጵያ ህዝብ መረጃዎችን በማድረስ አኩሪ ሥራ ሰርቷል::
ሕብር ራድዮ በ2007 ዓ.ም እድገት ካሳዩ ሚዲያዎች መካከል አንዷ ስትሆን በድረገጽ; በሳውንድ ክላውንድ; በዩቲዩብ; በጎግል እና በአፕል አፖች እንዲደመጡ ጋዜጠኛ ሃብታሙ ትልቁን ሥራ ሰርቷል::
ከራድዮው ሥራ በተጨማሪም በተለይ ለተሰደዱና ለተጎዱ ጋዜጠኞች ሞራል በመስጠት; በማስተባበር ከጎናቸው በመቆም ያደረገው አስተዋጽኦ ይጠቀስለታል::
ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋና ሕብር ራድዮ ሕዝቡ በቁሳቁስ ሊያግዛቸው ከቻለ እስካሁን ከሰሩት የበለጠ ሥራዎችን መሥራት እንደሚችሉ በየሳምንቱ እሁድ የሚያቀርቡት ፕሮግራሞች ይነግሩናል::
የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች የ2007 የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋ – እንኳን ደስ ያለህ::
የዓመቱ ምርጥ የሃይማኖት መሪ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል
ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በ1972 አ.ል በጂማ ከተማ ተወለደ፡፡ ኡስታዛችን ለቤተሰቦቹ የአራተኛ ልጅ ሲሆን ከህፃንነቱ ጀምሮ በሰዎች ዘንድ ፍፁም ዝምተኛና በፀባዩ ተወዳጅ ነበር፡፡ ኡስታዝ አህመዲን ከሰባ ወንድምና እህቶቹ ለወላጆቹ የተለየ ፈቅር ያለው ሲሆን በተለይ ለእናቱ ያለው ፍቅርና ታዛዥነት ከሌሎቹ ለየት ያደርገዋል፡፡
ኡስታዝ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ 1ኛ ደረጃ ትምህርቱን ቄራ መለስተኛ ት/ቤት ይማራል፡፡ ኡስታዝ ከትምህርት ይልቅ የ mechanic ሙያን ይወድ ስለነበር ወደ እዚያው ያደላል፡፡ በዚህም የአስረኛ ክፍል ማትሪክስ ውጤት በመድገሙ አባቱ ከሙያ ትምህርቱ እንዲቆም በማድረግ ሙሉ ትኩረቱን ወደ መደበኛው ት/ት እንዲያደርግ ይመክሩታል፡፡ እናም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ጂማ high school እስከ 12ኛ ድረስ በመማር በከፍተኛ ውጤት አጠናቀቀ፡፡ ከፍተኛ ትምህርቱን በአዲስ አበባ 4 ኪሎ campus በ chemistry የትምህር ክፍል የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘ ሲሆን በመቀጠልም በ Arabic and litrecher ማስተርስ ዲግሪውን ይዟል፡፡
ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በ campus ውስጥ ለ6 አመታት የቆየ ሲሆን በነዚህ አመታት ውስጥ ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን የሙስሊም ተማሪ ጀመዓ አሚር በመሆን አገልግሏል፡፡ እንዲሁም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ ታዋቂና ተወዳጅ ያደረገውን “ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች” የሚለውን መፅሃፍ በግቢ ቆይታው አዘጋጅቷል፡፡ ኡስታዛችን በ6 ኪሎ campus በ history ማስተርሱን ሰርቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ‹በሙስሊሞች ጉዳይ መፅሄት› እና በተለያዩ ድርጅቶች ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም ብዙ መፅሃፎችን ለህትመት አብቅቷል፡፡ በራሱ ካሳተማቸው ውስጥ ‹የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የጭቆናና የትግል ታሪክ፤ የሴቶች መብት በመፅኃፍ ቅዱስና በቁርአን እንዲሁም 303 በክርስትና ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎች› የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም ኡስታዝ አህመዲን ጀበል አሁን ላለው ኡማ እና ለቀጣዩ ትውልድ ብዙ መፃህፍቶችን በመተርጎም ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
ኡስታዝ አህመዲን ጀበል የመጀመሪያ የዲን ቂርአቱን በጂማ ፍትህ መስጂድ በተለያዩ ኢማሞች ቀርቷል፡፡ እንዲሁም አዲስ አበባ እያለ በኡስታዝ ሸኽ ሀሰን ሀሚዲን እና ኡስታዝ ሀሚድ ሙሳ የተለያዩ የዲን ትምህርቶችን የቀሰመ ሲሆን በራሱም የተለያዩ ኪታቦችን በማገላበጥ እውቀቱን አዳብሯል፡፡
በአጠቃላይ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ከህፃንነቱ አንስቶ አሁን እስካለው የእድሜ ደረጃ ድረስ በባህሪው እጅግ ተወዳጅና የተከበረ ግለሰብ ነው፡፡ ለሰዎች ያለው አክብሮት፣ ለተቸገሩ ያለው አዘኔታ፣ ለታላቆቹ ያለው ታዛዥነትና ለታናናሾቹ ያለው አክብሮት በስነ-ምግባሩ የላቀ ያደርጉታል፡፡ ሲናገር በእርጋታ፣ ሲያስረዳ የማይቆጣ፣ ክርክርና ጥላቻን ከቀልቡ ያራቀ ድንቅ ግለሰብ ነው፡፡
ይህ ድንቅ የኢስላም ልጅ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ከአስራ ሰባቱ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች አንዱ ሲሆን ለሙስሊሙ ኡማ በትምህርት መልክ ሲሰጥ የነበረውን ዛሬ ላይ በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡ ኡስታዝ አህመዲን አሁን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኝ ሲሆን በረመዳን ወር ላይ ከፍተኛ የሆነ ስቃይንና ፊትናን ቀምሷል፡፡ ኡስታዝ ዛሬ ለሁላችንም የሚሆን አርአያ መምህራችን ነው፡፡ ፈተና በመጣ ሰአት ከራሱ የበለጠ ለሙስሊሙ ኡማ የሚጨነቅ፣ ከነፍሱ ይበልጥ ለዲኑ የሚጨነቅና ከህይወቱ በላይ ኢስላምን የሚወድ ድንቅ መምህር፡፡ ይህንንም ዛሬ በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በአንድ ወቅት እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር….
“ታሪክ ሰሪ እንጂ ታሪክ አንባቢ መሆን የለብንም…!”
አዎ! ዛሬ እርሱ ታሪክ ሰሪ ሁኗል፡፡ በኢስላም ላይ ያንዣበበውን አደጋ በመጋፈጥ፤ ለልጆቻችን ኢስላምን እንጂ አናወርስም በማለት የመጀመሪያው ድንቅ ሰው ነው፡፡ ማንም ያልሆነውን ስም ቢለጥፉበትም (አሸባሪ፣ አክራሪ፣ መንግስት ለመገልበጥ የሚሮጥ፣…..ሌላም ሌላም) እያሉ ቢጠሩትም ይህን አለመሆኑን ግን ራሳቸው ጠሪዎቹ ያውቁታል፡፡ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ሰላምን ተምሮ ሰላምን ያስተማረ፣ ሰላምን አውቆ ስለ ሰላም ያሳወቀ፣ ሰላምን በማሻተማር ላይ ህይዉን የመራ ድንቅ የኢስላም ልጅ ነው፡፡ በሰላም አደፍራሾች በተደበዱ ጊዜም፣ ኢስላም ላይ ዘመቻ በተከፈተበት ጊዜም፣ ጠላቶች በሃይል ኢስላምን ካልለቀክ እያሉ በሚያሰቃዩበት በዚህ በጭንቅ ጊዜም ሰላምን እንጂ ሌላን ያልሰበኩ ባለ ድንቅ ስብእና::
አህመዲን ጀበል እንኳን ደስ ያለህ::
- See more at: http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46599#sthash.yBNtvINK.dpuf
No comments:
Post a Comment