በአዲሱ አከላለል ወደ ትግራይ በተካለለው የቀድሞ የሰሜን ጎንደር አካል በነበረችው በምዕራባዊ ዞን ቃፍታ ሑመራ በረከት ከተማ ትላንት ጳጉሜ 6 ቀን 2007 በአዲሱ ኣመት ዋዜማ የከባድ መሳሪአ ድብደባ እንደነበር ነዋሪዎች ገለጹ።
የአካባቢው ነዋሪዎች በመቀሌ ለሚገኘው የአረና የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አምዶም ገብረስላሴ በስልክ እንደገለጹለት ማን እንደተኮሰ ያላወቁት የከባድ መሳሪያ ድብደባ የነበረ ሲሆን በድብደባው የደረሰ ጉዳት ይኑር አይኑር አለመታወቁን ጠቅሷል።
በቅርቡ የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያውን አገዛዝ በጦርነት ተንኳሽነት የከሰሰ ሲሆን ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ሊያመሩ ይችላሉ የሚል ግምታቸውን የሚሰቱም አሉ።
በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኤርትራ የሚገኙ የታጠቁ ከስርዓቱ ተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል አርበኞች ግንቦት ሰባት የከፈቱትን የደፈጠ ጥቃት ተከትሎ ሁለቱ አገራት በግልጽ ጭምር አንዱ አንዱን በጦርነት ጸብ ጫሪነት መክሰስ መጀመራቸው ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አርበኞች ግንቦት 7ን ጨምሮ በኤርትራ የሚገኙ ዋና ዋና አራት ጸረ ወያኔ ታጣቂ ድርጅቶች የጋራ ንቅናቄ መስርተው ስያሜያቸውን <<የኢትዮጵያ አገር አድን በዴሞክራሲ የጋራ ንቅናቄ>> የሚል አዲስ ድርጅት መመስረታቸውንና ለአዲሱ የጋራ ንቅናቄ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሊቀመንበር፣ ታጋይ ሞላ አስገዶም ም/ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ሰሞኑን መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን እኚሁ በኤርትራ የሚገኘውን የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲአዊ ንቅናቄ (ትህዴን) የሚመሩት ግለሰብ ከድተው ከወያኔ ጋር መግባታቸው ተዘግባል።
የህወሓት አገዛዝ አፈ ቀላጤ የሆኑ አንዳንድ ድህረ ገጾች የአቶ ሞላን ከተወሰኑ የግንባሩ ታጣቂዎ ጋር ከድቶ መግባት አስቀድሞ የተሰራበት ስራ እንደነበር ገለጹ። በወያኔ ሰፈር እንደ ሞራል ማነቃቂያ የተፈለገው የአቶ ሞላ መክዳትን አንዳንዶች በኢትዮጵያ የትግል ታሪክ ተደጋጋሚና ተለመደ ይልቁንም የትግሉ እየተጠናከረ መሄድ ማሳያ ሲሉ አጣጥለውታል። ድርጊቱ የትግሉን መጠናከር ያሳያል የሚሉም በርክተዋል። የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲአዊ ንቅናቄ ከአርነቦች ግንቦት ሰባት፣ከአፋር ሕዝብ ንቅናቄና ከአማራ ሕዝብ ነጻ አውጭ ጋር ያደረገውን ውህደት ድርጅታቸውን በመወከል ፊርማቸውን ያኖሩት ሊቀመንበሩ ወደ ወያኔ ለመሄድ ያታደፋቸው ጫና በሳቸው ላይ ያልተጠበቀ መረጃ ተገኝቶ ማንነቴ ይጋለጣል ከሚል ፍራቻ ይሁን በሌላ ለጊዜው ምን እንደሆነ አልታወቀም። ድርጅታቸው ሊቀመንበሩ ቢከዱም የሰራዊቱ ሞራል እና ጥንካሬ አስተማማኝ መሆኑን አንዳንድ ውስጥ አዋቂዎች ለህብር ገልጸዋል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው።
በቅርቡ ከኤርትራ ከድተው ወደ ወያኔ የገቡትን ታጋይ ሞላ አስገዶምና አብረዋቸው የከዱ ጥቂት የሰራዊቱ አባላትን ቃለ መጠይቅ በማድረግ በኤርትራ ያሉትን የነጻነት ታጋዮችና በቅርቡ ትግሉን ለመምራት የሄዱ ከፍተኛ አመራሮችን የማጥላላት ፕሮፖጋንዳ ይሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል።
የህብር ሬዲዮን ዘገባ ህብር ሬዲዮን ከድህረ ገጻችን በተጨማሪ በስልክ ለማዳመጥ 712 -432-8451 መደወል ብቻ በቂ ነው። በእንግሊዝ ለምትኖሩበ01405770140 በስልክ ማዳመጥ ይቻላል። ዘወትር በድህረ ገጻችን ወይም ከgoogel store Hiber radio አፕሊኬሽንን ዳውን ሎድ በማድረግና ከዘሐበሻም ማዳመጥ ይቻላል።
No comments:
Post a Comment