Sunday, December 4, 2016

ራሱን በማወቅና ንስሃ በመግባት ከአጋሰስነት ወደ ሰውነት የተቀየረው ጎበዝ(በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

“መጀመርያ ራስህ እወቅ” ሲል አስተምሯል ሶቅራጥስ፡፡ በመጀመርያ ራስን የማወቅን ጥበብ አውቆም ሆነ ሳያውቅ አገር ቤት ሲጫን ኖሮ ከዚያም ፍራንክፈርት ጀርመን ለጭነት ተልኮ የነበረው አጋሰሱ ግርማ መንገሻ ራሱን አውቆ ሳያመነታ ለንስሃ የበቃ የመጀመርያው ጎበዝ ሆኗል፡፡ ንስሃ ሐጥያትን ያጥባል፤ አቋቋምንም ያስተካክላል፡፡ አጋሰሱ ግርማ በንስሃ ምላጭ ጌቶቹ ይይዙት የነበረውን ጋማውን ተላጭቶ፣ በንስሃ ማጪድ ጅራቱንና ጭራውን አጭዶ፤ በንስሃ አባሎ ቅርቀብ ይጫንበት የነበረውን ገጣባውን አድኖና በንስሃ ካራ የአፉን ልጓም በጥሶ ሰው ሆኗል፡፡ አጋሰሱ ግርማ ዛሬ አቶ ግርማ መንገሻ ሆኖ ሚስቱን፣ ልጁንና ወላጆቹን አኩርቷል፡፡ ባጋሰስነቱ ያደማትን አገሩንና ያሰቃየውን ሕዝቡን ለመካስም ቃል ገብቷል፡፡
አቶ ግርማ መንገሻ ዙሪያ ጥምጥም ሳይሄድ ራስን ማወቅን አስቀድሞ ንስሃን አስከትሏል፡፡ በዚህ ራሱን የማወቅና የንስሃ መግባት ባህሪውም አቶ ግርማ በቅርቀብ ጭነት የተገጣጠበውን ጀርባቸውን በሚያማምሩ ሸሚዞችና ሱፎች ከሚሸፍኑት፤ ሆዳቸውን በሚጣልላቸው ፉርሽካና አተላ ከሚቆዝሩት፣ ልሳናቸውን በተዋቡ ከራቫቶች ለጉመው ከሚጎተቱት ቱባ ቱባ አጋሰሶች የተለየ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ካቶ ግርማ በተቃራኒው ስኳር የላሰው ታምራት ላይኔ፣ በነፍጠኛ ወቢ የተፋው ሀሰን አሊ፣ በጭንቅላት መቺነቱ የደነፋው ጁነዲን ሳዶና ሌሎችም ጉዶች አጋሰሰ እንደሆኑ መኖርን መርጠዋል፡፡ እነዚህ አጋሰሶች ራሳቸውን ሳያውቁ እንደ አዋቂ ሌሎችን ሊያሳውቁ በመቃጣት፣ ንስሃ ሳይገቡ እንደ ቅዱሳን ሊሰብኩ በመዳዳት አሁንም ገጣባቸው ያልደረቀ፣ ምንግጭላቸው በሕዝብ ደም የተበከለ ፣ ሸኮናቸው የሕዝብን ሬሳ የረገጠ መጋዣዎች ሆነው ቀርተዋል፡፡ መጋዣዎች ሆነው በመቅረታቸውም ሚስቶቻቸውን ያጋሰሶች ሚስቶች፣ ልጆቻቸውን ያጋሰሶች ልጆች፤ ወላጆቻቸውንም ያጋሰሶች ወላጆች እያሰኙ ማሸማቀቁን ቀጥለዋል፡፡ እንደ አቶ ግርማ ራሳቸውን በማወቅና ንስሃ በመግባት ወደ ሰውነት ከመቀየር ይልቅ ለአጋሰስነት አገልግሎታቸው የተጣለላቸውን ፉርሽካ በጊዜ ወደ ምዕራቡ ዓለም አሻግረው እየፈረከሱ ሲውጡ ኖረው መሞትን መርጠዋል፡፡አጋሰስ እንደሆነ መኖር ያልፈለገው አቶ ግርማ መንገሻ ግን በዚህ ቃለ መጠይቅ http://ethsat.com/2016/12/esat-tikuret-girma-mengesha-december-1-2016/ ራሱን ማወቁን አረጋግጦ ንስሃ ገብቷል፡፡
“እኛ በተለይ የትግራይ ተወላጅ ያልሆን በሙሉ …ከሚኒስቴር እስከታች ወረዳ ወይም ቀበሌ ሹም ሆነ እሚሰራ የትግራይ ተወላጅ ያልሆነ በሙሉ አጋሰስ ነው!! እኛ አጋሰስ ነን!” ሲል እውነቷን ተናገረና አጋሰስ ምን እንደሆነ ሲጠየቅም “አጋሰስ ማለት ለጭነት የተፈጠረ እንሰሳ!…የማይናገር እንሰሳ፣ እህል ውሀ በማያሰኝ ዱላ ሲዠለጥ አመመኝ የማይል እንሰሳ፣ ወደዚህ ዙር ሲባል የሚዞር፣ ወደ ፊት ሂድ ሲባል የሚሄድ፣ የተጫነውን ተሸክሞ እስከሚደፋ የሚለፋ እንሰሳ” ሲል ከአለቃ ተክለወልድ በረቀቀና  በተዋበ መንገድ አጋሰስን አብራርቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አንዳድ አጋሰሶች ከአጋሰስ ዠላጭ ጌቶች የበለጠ ለአገሪቱና ለሕዝቡ አደገኛ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡
በመጀመርያ ራሱን የተረዳና የት እንዳለ ያወቀ  በመቀጠል ወዴት መሄድ እንዳለበት ያውቃል፡፡ በዚህም መሰረት ራሱን የተረዳውና የቆመበትን ቦታ ያወቀው አቶ ግርማ ከሌሎች አጋሰሶች በተለየ መንገድ ወለም ዘለም ሳይል በቀጥታ ወደ ይቅርታ ቤት ተጉዟል፡፡ ከይቅርታ ደጃፍ እንደ ደረሰም ራሳቸው ንስሃ ለሚያስፈልጋቸው ካህናት ሳይሆን በአጋሰስነት ባገለገለው አገዛዝ ለተረሸነው፣ ለተጠበሰው፣ ከርቸሌ ለታጎረው፣ በችጋርና በበሽታ ለሚሰቃየውና ተሰዶ ገረድ ወይም ባርያ ለሆነው ሕዝብ ሳያመነታ ይቅርታ ጠይቆ ከአጋሰስነት ወደ ሰውነት ተሸጋግሯል፡፡
በይቅርታ ከአጋሰስነት ወደ ሰውነት የተሸጋገረው አቶ ግርማ “እኔ ለዚህ መንግስት ሳገለግል ይህ መንግስት እያደረገ ያለውን ሁሉ እተባበር፣ ተኩሼ ባልገድል ወይም ግደሉ ብዬ ትእዛዝ ባላስተላልፍም ይኸ መንግስት በሚያደርገው ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋሪ መንገድ ተሳታፊ ነበርኩ …” ካለ በኋላ “እኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከልብ፣ በጣም ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብሎ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ “ከልቡ አይደለም!” ብሎ እሚከራከር ልብ አንባቢ ሊኖር ይችላል፡፡ ለእኔ ግን አቶ ግርማ በቅርቀብ ጭነት ከመገጠብ ራሱን ነፃ አውጥቶ ንስሃ የገባ የመጀመርያው አጋሰስ ሆኖ ታይቶኛል፡፡ ያቶ ግርማ ንስሃ የገንዘብና የስልጣን መለመኛ ሻንጣውን አንግቦ ወደ ነፈሰ ገዳዮች አዳራሽ እንደሚተመው የዛሬ ካህን ሳይሆን የቅኔ ጥማቱን ለማርካት አኮፋዳውን አንጠልጥሎ ወደ ዋሸራ ይነጉድ እንደነበረው የድሮ ካህን ይበል ያሰኛል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሆይ! “ከራሱ ያወቀ ቡዳ ነው!” ይባላል፡፡ “ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ” ተብሎም ይተረታል፡፡ የድሮው አጋሰስ የዛሬው አቶ ግርማ መንገሻ ራሱን ጨምሮ ከዚህ አገዛዝ ጋር የሰራ ሁሉ አጋሰስ እንደሆነ በግልፅ ቋንቋ አስረድቶናል፡፡ ግልጥ ባለ አማርኛ ግፈኞችን ባጋሰስነት ማገልገሉን አሳውቆ በሕዝብ ፊት ንስሃ ገብቷል፡፡ ራሱን አውቆ፣ ኃጥያቱን አምኖ ንስሃ የገባ ሲቀድስ ተሰጥኦ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ያቶ ግርማን ፈለግ በመከተል ከጭነትና ከመገጠብ ነፃ ወጥተው ንስሃ ያልገቡትን መጋዣዎች አጋሰሶች ብለን ተፈጥሯቸው በሰጣቸው “ማእረግ” ብንጠራቸው ምን ይመስላችኋል? ተፈጥሯቸው የሰጣቸውን ማእረግ ትተን በሚያሽቃብጥ ትህትና ወይም በድኩማን ዲፕሎማሲ ተሸብበን እነዚህን መጋዣዎች ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ ሚኒስቴር፣ ፕሬዘዳንት፣ ኮሚሽነር፣ ዶክተር፣ ፕሮፌሰር፣ አቶ፣ ኦቦ፣ አቦይ፣ ቅብጥሶ፣ ቅብጥሶ በሚባሉ የቅጥፈት ማእረጎች ከመጥራት አጋሰስ እገሌ እያልን ብጠራቸው ምን ይመስላችኋል?
ተመሳሳይ ጽሑፎች
  1. ሥም አውጡልኝ http://www.abugidainfo.com/amharic/wp-content/uploads/2010/05/sim_awutu.pdf
  2. ከስብከት ንስሃ ይቅደም http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/18736
  3. ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ሆይ፤ ከናዚ ሐኪሞች የደም ታሪክ ከመዘፈቅ ታቀቡhttp://www.satenaw.com/amharic/archives/17276
ህዳር ሁለት ሺ ዘጠኝ ዓ.ም.

No comments:

Post a Comment