ህወሃት/ኢህአዴግ በሃገሪቱ ዜጎች ላይ በሚያካሂደው ግድያና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ምክንያት የፓርቲውን ምርቶች አለመጠቀምና በሃብቶቹም ላለመገልገል የወሰነው የአማራ ክልል ነዋሪ ህዝብ፣ ይህን አቋሙን አጠናክሮ በመቀጠሉ በፓርቲው የግል ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሰ ነው።
በአማራ ክልል ዋና ዋና የንግድ መነኻሪያ ከተሞች ህብረተሰቡ የህወሃት/ኢህአዴግ ኩባንያዎች ምርቶች የሆኑትን ዳሽን ቢራ፣ ራያ ቢራ፣ መሰቦ ሲሚንቶና ሰላም ባስን ባለመጠቀም አቋሙን አጠናክሮ ቀጥሏል። በሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ጫና በማድረግ ስራውን በበላይነትና በብቸኝነት ለመቆጣጠር ሲሯሯጥ የነበረው የህወሃቱ “ሰላም ባስ”፣ ህዝቡ በድርጅቱ ላይ በወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች እንዲሁም ህብረተሰቡ በአውቶቡሱ ባለመጠቀሙ ምክንያት በኢኮኖሚው ላይ ተጽእኖ እያደረሰበት መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ለኢሳት ገልጸዋል። ሰላም ባስ ከአዲስ አበባ በመነሳት ወደ አማራ ክልል በየቀኑ ሲያደርጋቸው የነበሩትን ከሰባት በላይ ጉዞዎች በመቀነስ ወደ ሶስት ጉዞዎች ቢያወርድም በተለይ ከጎንደር፣ ከባህር ዳርና ደብረ ማርቆስ ከተሞች ምንም አይነት ተጓዥ ሳያገኝ ባዶውን እንደሚመላለስ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል። ከጎንደር ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ጉዞ ሲሸፍኑ የነበሩ አራት አውቶብሶች ቀርተው በአንድ አውቶቡስ ለመሸፈን ጥረት እያደረገ ያለው ሰላም ባስ፤ ሰሞኑን ከሶስቱ ከተሞች አስር ተጓዦችን ብቻ ይዞ ለመንቀሳቀስ መገደዱን የዓይን እማኞች ተናግረዋል። “የወያኔን ንብረት በመጠቀምና የገንዘብ አቅሙን በማጎልበት ዜጎቻችንን በማሰቃየትና በመግደል ላይ ላለው ስርዓት የጥይት መግዣ አናደርግም” በማለት በከፍተኛ ቆራጥነት ምርቶቹን ላለመጠቀምና በንብረቶቹም ላለመገልገል የተማማለው ህዝብ፣ አሁንም አቋሙን አጠናክሮ በመቀጠል አንድነቱን ማሳየት እንዳለበት ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ጥሪ አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment