[የኮንዶሚኒየም ቤት ሰብሮ የገባ የክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ዘመድ ደወለላቸው]
  • ሰላም ጋሼ፡፡
  • ምን ፈለግክ ደግሞ?
  • ኧረ ጉድ ፈልቷል ጋሼ፡፡
  • የምን ጉድ ነው?
  • ብጥብጥ ተፈጥሯል ስልህ፡፡
  • አንተ ብጥብጡ ውስጥ አለህበት እንዴ?
  • የትኛው ብጥብጥ?
  • ይኼ በየከተማው የሚካሄደው ውስጥ ነዋ፡፡
  • ኧረ ሌላ ብጥብጥ ተፈጥሯል፡፡
  • የምን ብጥብጥ ነው?
  • እዚህ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ነዋ፡፡
  • ምንድን ነው ሰዎች ተጣልተው ነው?
  • ኧረ ሊያስለቅቁኝ ነው ጋሼ?
  • ምኑን ነው የሚያስለቅቁህ?
  • የኮንዶሚኒየም ቤቱን ነዋ፡፡
  • ለምን ሲባል?
  • ሰብረህ ገብተሃል ብለውኝ ነዋ፡፡
  • ቁልፉን አልሰጥ ሲሉ አይደል እንዴ ሰብረህ የገባኸው?
  • አዎ ጋሼ ያው ሕገወጥ ነህ እያሉኝ ነው፡፡
  • ማን ነው ሕገወጥ ነህ የሚልህ?
  • ያው የእናንተ ሰዎች ናቸዋ፡፡
  • እኔ አይደል እንዴ ቤቱን ያሰጠሁህ?
  • ለዛ ነው እኮ የደወልኩት ጋሼ፡፡
  • በቃ ለእኔ ተወው፡፡
  • ምን ታደርጋለህ?
  • ልካቸውን አስገባቸዋለሁ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ዘመድ ደወለ]
  • እንዴት ዋልክ ጋሼ?
  • ሰላም ነህ፡፡
  • ሰማህ አይደል ጋሼ?
  • ምኑን?
  • የኮንዶሚኒየም ቤቶቹን ወሬ፡፡
  • አዎን ሰምቻለሁ፡፡
  • ጋሼ እኔ እኮ አምስት ልጆች ነው ያሉኝ፡፡
  • እኔ እኮ የማይገባኝ ነገር አለ፡፡
  • ምን ጋሼ?
  • ከገጠር እኮ ያስወጣውህ የቤተሰብ ምጣኔ እንዲገባህ ብዬ ነበር፡፡
  • እሱማ በደንብ እየገባኝ ነው ጋሼ፡፡
  • ይኸው አምስት ልጅ ፈልፍለህልኝ ምኑን ገባህ? እኔ የምለው ማታ ማታ ከሚስትህ ጋር ከመተኛት ውጪ ሌላ ሥራ የለህም?
  • ምን ላድርግ ጋሼ?
  • ቴሌቪዥን አትመለከትም፡፡
  • ዲሽ እኮ የለኝም ጋሼ?
  • የአገር ውስጥ ጣቢያ አትመለከትም ታዲያ?
  • ውሸት እንዳልማር ብዬ ነው እኮ፡፡
  • ወሬውንማ ታውቅበታለህ፡፡
  • ይኸው አሁን የደወልኩት የልጆቼ መኝታ ቤት ይሆን ዘንድ ከጐኔ የነበረውን ኮንዶሚኒየም ጠቅልዬ ይዤው ነበር፡፡
  • እና ምን ሆነ አሁን?
  • ሕገወጥ ነህ ብለው ሊያስለቅቁኝ ነው፡፡
  • እኔ የምለው ሕዝቡን ጐዳና ተዳዳሪ ሊያደርጉት ቆርጠው ተነስተዋል እንዴ?
  • እኔ እኮ ግራ ገብቶኝ ነው የደወልኩት፡፡
  • እኛ ድህነት ጠላታችን ነው እንላለን፣ እነሱ በጐን ድህነትን ሊያስፋፉ ተነስተዋል፡፡
  • የሚገርም እኮ ነው ጋሼ፡፡
  • ፀረ ልማት ሁሉ ተዋቸው፡፡
[ሌላ ሦስት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ያሉት የክቡር ሚኒስትሩ ዘመድ ደወለ]
  • ጋሼ እንዴት ውለሃል?
  • እንዴት ነህ?
  • ጋሼ ትልቅ እቁብ እንደምጥል ታውቃለህ አይደል?
  • አዎን አውቃለሁ፡፡
  • እና እቁቤን ማቋረጥ አለብኝ?
  • ለምን ታቋርጣለህ?
  • የቀረኝ እኮ ጥቂት ወራት ናቸው፤ ዕጣው ራሱ አልደረሰኝም፡፡
  • እኮ ለምን ታቋርጣለህ?
  • ይኸው ሁለቱ ቤቶችህ ይወረሳሉ እያሉኝ ነው፡፡
  • ለምን ተብሎ?
  • ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ብለውኝ ነዋ፡፡
  • ማን ነው አንተን ኪራይ ሰብሳቢ ያደረገህ?
  • ሦስት ኮንዶሚኒየም ቤቶች ታከራያለህ ብለውኝ ነዋ፡፡
  • እኔ የምለው ማን ነው ኪራይ ሰብሳቢነት ወንጀል ነው ያለው?
  • እኔም እኮ ለዛ ብዬ ነው አንተ ጋ የደወልኩት፡፡
  • ሰው ሠርቶ አይለወጥ ነው የሚሉት?
  • የሚያሳዝን ዘመን ላይ ነው እኮ ያለነው ጋሼ፡፡
  • ምቀኛ ሁሉ፡፡
  • ምን ላድርግ ታዲያ ጋሼ?
  • ለእኔ ተወው፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ አክስት ደወሉ]
  • እንዴት ነህ ወንድም ጥላ?
  • እንዴት ነሽ አክስቴ?
  • ወንድም ጥላ የምልህ ዝም ብዬ እንዳልሆነ ታውቃለህ አይደል?
  • ለምንድን ነው የምትይኝ አክስቴ?
  • መጠለያ ቤት እኮ ያሰጠኸኝ አንተ ነህ ብዬ ነው፡፡
  • ልክ ነሽ አክስቴ፡፡
  • አሁን ግን መጦሪያዬን ሊወስዱብኝ ነው፡፡
  • እንዴት አክስቴ?
  • ያው ትልቁን ቤት እያከራየሁ እንደምተዳደር ታውቃለህ?
  • ለዛ አይደል እንዴ ኮንዶሚኒየም ቤት ያሰጠሁሽ?
  • ይኸው ቤት አለሽ ብለው ሊቀሙኝ እኮ ነው?
  • እስቲ የሚነካሽን አያለሁ፡፡
  • ጐሽ ወንድም ጥላ፡፡
  • ጥላውን ነው የምገፈው ስልሽ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ጋ ደወሉ]
  • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን እያደረጋችሁ ነው?
  • ምን አደረግን ክቡር ሚኒስትር?
  • ከተማውን የማተራመስ አጀንዳ ይዛችሁ ነው እንዴ የተነሳችሁት?
  • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ከፀረ ልማት ኃይሎች ጋር ሳትገጥሙ አልቀራችሁም?
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ይኸው በትንሽ ደቂቃ ውስጥ አራት ሰዎች ናቸው የደወሉልኝ፡፡
  • ምን ብለው?
  • ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ነው የነገሩኝ፡፡
  • ቢያብራሩት ክቡር ሚኒስትር?
  • ሰዎችን ከቤታቸው ማፈናቀል እኮ ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡
  • ሰዎቹ እኮ ናቸው ሕገወጦች፡፡
  • ሕጋዊ ማድረግ ነዋ፡፡
  • ማንን?
  • ሕገወጦቹን!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ በጣም ውድ የሆነ ሬስቶራንት ምሳቸውን በልተው ከሹፌራቸው ጋ እየሄዱ ነው]
  • እዚህ ሬስቶራንት ግን ሁለተኛ አልመጣም፡፡
  • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
  • በቃ የከተማው ሀብታም መናኸሪያ ሆነ፡፡
  • ያው ልማቱ ያፈራቸው ናቸው፡፡
  • በዛ ላይ ሰርቪሱም ወረደ፡፡
  • ታዲያ እኛ ጋ ለምን አይመጡም?
  • የት?
  • ክበብ ነዋ፡፡
  • ከሰፊው ሕዝብ ጋር ምሳ ልበላ?
  • እንዴ ክቡር ሚኒስትር ከሕዝቡ ጋር እኮ መመሳሰል አለብዎት?
  • እኔ እኮ ምሳሌ የሌለኝ ሰው ነኝ፡፡
  • በሙስና ነው?
  • ምን አልክ አንተ?
  • እኔ እኮ የማይገባኝ ክቡር ሚኒስትር፣ ዛሬ የበሉበት ሬስቶራንት የአንድ ምግብ ዋጋ የእኔን የስድስት ወር ደመወዝ ነው አሉ፡፡
  • ገብተህ ትበላለህ እንዴ?
  • ሲያወሩ ሰምቼ ነው፡፡
  • እሱንም ማወቅህ ጥሩ ነው፡፡
  • ሌላም ቀናት የሚበሉባቸው ሬስቶራንቶች በጣም ውድ ናቸው፡፡
  • እና ሳልበላ ልኑር?
  • ሚኒስትር ስለሆኑ ገንዘቡን ከየት ነው የሚያመጡት ብዬ ነው፡፡
  • ችግርህ እኮ ይኼ ነው፡፡
  • ምንድን ነው ችግሬ?
  • እኔ እኮ በአንድ ዘርፍ ብቻ የተወሰንኩ ሰው አይደለሁም፡፡
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ከሚኒስትርነት ሌላ በርካታ ሥራዎች አሉኝ፡፡
  • ምን ዓይነት?
  • አስመጪና ላኪ፡፡
  • እሺ፡፡
  • ሕንፃ አከራይ፡፡
  • ሌላስ?
  • ኢንቨስተርም ነኝ፡፡
  • አሁን ገባኝ፡፡
  • ምኑ?
  • ልዩነታችን፡፡
  • ምንድን ነው ልዩነታችን?
  • እርስዎ ዕቃ አስመጪ፣ እኔ ቢራ ጠጪ፡፡
  • እ…
  • እርስዎ ሕንፃ አከራይ፣ እኔ ቤት ተከራይ፡፡
  • እ…
  • እርስዎ ኢንቨስተር፣ እኔ ድራይቨር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ግምገማ ላይ እየተገመገሙ ነው]
  • ክቡር ሚኒስትር በመጀመሪያ የሚገመገሙት እርስዎ ነዎት፡፡
  • ምን ተገኝቶብኝ?
  • ይኼ ሁሉ ማስረጃ እርስዎ ላይ የቀረበ ነው፡፡
  • እኔ የማይገባኝ እኮ አንድ ነገር ነው፡፡
  • ምንድን ነው የማይገባዎት?
  • እዚህ ውስጥ ማን ንፁህ ኖሮ ነው እኔ የምገመግመው?
  • ምን ማስረጃ አለዎት?
  • እኔ እንዲያውም እናንተ ላይ ያለኝን ማስረጃ ፕሪንት ለማድረግ የወረቀት ማስመጫ ኤልሲ አጥቼ ነው የተውኩት፡፡
  • የወረቀት ቢዝነስ ውስጥም ገብተውልኛል?
  • የፈለግኩት ቢዝነስ ውስጥ ብገባ ምን አገባችሁ?
  • ያስጠይቅዎታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ተገቢውን ግብር እስከከፈልኩ ድረስ ማንም ሊጠይቀኝ አይችልም፡፡
  • ይገመገማሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የግምገማውን ውጤት እኮ አውቀዋለሁ፡፡
  • ምንድን ነው ውጤቱ?
  • ግፋ ቢል ቦታ ብትቀይሩኝ ነው፡፡
  • እ…
  • ይህ ደግሞ ሌላ ቢዝነስ ውስጥ እንድገባ በር ይከፍትልኛል፡፡
  • አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት?
  • ከስህተትዎ ሊማሩ ስላልቻሉ አሁን ዕርምጃ ይወሰድብዎታል፡፡
  • ምን ዓይነት ዕርምጃ?
  • ሕጋዊ ዕርምጃ?
[ክቡር ሚኒስትሩ እጅግ ተበሳጭተው በጊዜ ቤታቸው ገብተዋል፡፡ ሚስታቸው ቤት ሲገቡ ክቡር ሚኒስትሩን አገኟቸው]
  • ምነው ቤቱን ፋርማሲ አስመሰልከው?
  • አንቺ ትንሽ ሲስቁልሽ ቀልድሽ ለከት የለውም፡፡
  • ይኼ ሁሉ መድኃኒት ጠረጴዛ ላይ የደረደርከው ምን ሆነህ ነው?
  • ስኳሬና ደሜ ጨምሯል፡፡
  • ገቢህም ጨምሯል፡፡
  • ራስ ምታት ሊገድለኝ ነው፡፡
  • ምነው?
  • ወገቤንም እየወጋኝ ነው፡፡
  • እኮ ምን ተፈጠረ?
  • ሲያንገበግቡኝ ነበር፡፡
  • እነማን?
  • ስገመገም ነው የዋልኩት፡፡
  • ለምንድን ነው የተገመገምከው?
  • ተጠርጥሬ፡፡
  • በምን?
  • በሙስና፡፡
  • በል አሁን ደግሞ በሌላ ነገር እንዳትጠረጠር፡፡
  • በምን?
  • በዶፒንግ!