የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚንስትር ሲራጅ ፈጌሳ ለሶስት ቀናት በሱዳን ካርቱም ቆይተው ትናንት ወደአዲስ አበባ ማምራታቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡የሚንስትሩ የካርቱም ቆይታ በአገር ውስጥ ሚዲያዎች ትንፍሽ ባይባልበትም ሱዳኖች የሲራጅ የካርቱም ቆይታ በቅርቡ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ ከሚጠበቀው የሁለቱ አገራት የድንበር ማካለል ጋር የተያያዘ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡
ሲራጅ በካርቱም ከሱዳኑ የመከላከያ ሚንስትር አዋድ ኢብን በመገናኘት የሚካለለውን ድንበር የሚጠብቁና ድንበሩን የሚያስከብሩ ወታደሮችን በየወሰኖቻቸው ስለሚያሰፍሩበት ሁኔታ መነጋገራቸውን ኢብን ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መረዳት ተችሏል፡፡
ከሁለቱ አገራት በጥምር የሚዘጋጅ የመከላከያ ኃይል ድንበሮቹን ለመጠበቅና ሰላምና ወንድማማችነትን በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን ሲራጅ እንደነገሯቸው የሱዳኑ ሚንስትር ተናግረዋል፡፡
ሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር ለማካለል ኮሚቴ በማቋቋም የሁለትዩሽ ውይይት ለማድረግ ሰሞኑን ለ13ኛ ጊዜ በካርቱም ተገናኝተዋል፡፡ስብሰባዎቹ በአብዛኛው በሱዳን ከመካሄዳቸውም በላይ ለኢትዩጵያዊያን ይፋ ሳይደረጉ መቆየታቸው ለብዙዎች አስገራሚ ሆኗል፡፡ሲራጅ ከሱዳኑ አቻቸው ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም አገራቸው የድንበር ኮሚቴዎቹ የሚደርሱባቸውን ስምምነቶች መሬት ላይ ለማውረድ ቁርጠኛና ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ሚንስትሮች የየአገሮቻቸው የፖለቲካ መሪዎች በድንበር ማካለሉ ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይናገሩ እንጂ ድንበሩ ይካለላል ተብሎ በሚጠበቁ ቦታዎች በህዝቡ መካከል በከፍተኛ ሁኔታ የይገባኛል ጥያቄ እየቀረበባቸው እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ ደም አፍሳሽ ግጭቶች እየተመዘገቡባቸው ይገኛሉ፡፡
ሱዳን የእኔ ነው የምትለው አል ፋሽጋ 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን በውስጡም 600.000 አክረስ ለም መሬት ይገኝበታል፡፡አትባራ፣ሰቲትና ባስላም የተባሉ ወንዞችም በአካባቢው ያልፋሉ፡፡
የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር በአማራ ክልል የሚገኝ ሲሆን ሱዳን በ1900 እንግሊዝና ጣልያኖች አሰመሩት የምትለው የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ህጋዊ ተደርገው እንዲቀጥሉ የምትፈልግ ሲሆን በስልጣን ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ መሪዎችም ምንም አይነት መከራከሪያ ሲያቀርቡ አይደመጡም፡፡
ምንጭ ሱዳን ትሪቡን
No comments:
Post a Comment