ኦሮሚያ ውስጥ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ እምቢተኝነት በአሁኑ ሰዓት በጋምቤላ፣ በደቡብ እና በአማራ ክልሎች እየተስፋፋ ይገኛል። ይህንን ሂደት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በተለያዩ ቦታዎችና ማኅበረሰቦች ውስጥ በተለያዩ ሰበቦች እየተካሄዱ ያሉ ሕዝባዊ እምቢተኝነቶች መገናኘትና መቀናጀት አለባቸው። እንዲቀናጁ ደግሞ የሚያቀናጁ ሰዎች ሊኖሩ ይገባል።
ሕዝባዊ እምቢተኝነት አንዴ ከተቀሰቀሰ እንደ ወረርሽን በፍጥነት ሊሰራጭ ይችላል። ይህ እንዲሆን ግን ሶስት ዓይነት ሰዎች ያስፈልጋሉ (1) የኔታዎች (Mavens) - በሕዝብ አካልና ስነልቦና ውስጥ ያለውን የተደበቀውን በደልና ብሶት ስሜት በሚሰጥ መልክ የሚያቀርቡት፤ ሥርዓቱ ሊለወጥ የሚችል መሆኑ የሚያሳዩ እና ከለውጡ በኋላ የተሻለ ሥርዓት ሊመጣ የሚችል መሆኑን የሚገልጹ በማኅበረሰቡ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች፤ (2) ቀስቃሾች (Salesmen) - የየኔታዎችን መልክት ፍሬ ነገሩ ብቻ ለተራው ሰው በሚገባውና በሚወደው መንገድ (ለምሳሌ በዘፈን፣ በግጥም፣ በቀረርቶ፣ በስዕል፣ በቀልድ፣ ... ወዘተ) የሚያቀርቡ፤ እና (3) አገናኞች (Connectors) - በተለያዩ ርዕሰጉዳዮች ለአመጽ የተነሳሱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያገናኙ።
አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ የአገናኞች ሚና ጎልቶ ወጥቷል።
የአሮሚያውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ከወልቃይት፣ ከቅማንት፣ ከጉጂ፣ ከሱርማ፣ ከጋምቤላው ... ወዘተ ጋር ማገናኘት የሚችሉ ታጋዮች መኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን። እነዚህ ሰዎች የተለያዩ ማኅበረሰቦችን የሚያገናኙ፤ በሁለት ወይም ከሁለት በላይ በሆኑ ማኅበረሰቦች ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው፤ የሁለቱን ማኅበረሰቦች ባህሎች፣ ልማዶች፣ ስሜቶች የሚረዱ መሆን ይኖርባቸዋል። እራሳቸው አባል ከሆኑበት ማኅበረሰብ አልፈው በሌላው ማኅበረሰብ የቀረበው ጉዳይ የሚረዱ እና በጉዳዮች (issues) መካከል የጋራ መግባቢያ ማግኘትና ማጉላት የሚችሉ ሰዎች ያስፈልጉናል።
ስለሆነም የወቅቱ ተግባራዊ ትግል (ወተት) ትኩረት በተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች እየተቀሰቀሱ ያሉ ሕዝባዊ እምቢተኝነቶችን ማገናኘት እንዲሆን ሀሳብ አቀርባለሁ።
No comments:
Post a Comment