Thursday, July 21, 2016

በኦሮሚያ እና በጎንደር የተቀጣጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምሁራን ጠየቁ ኢሳት (ሃምሌ 13 ፥ 2008)


በኦሮሚያ እና በጎንደር የተቀጣጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ እና ተቀናጅቶ እንዲቀጥል ሁለት ታዋቂ ምሁራን ገለጡ።
ከኢትዮጵያ ሳተላይት ሬዲዮና ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጋር ቆይታ ያደረጉት ሁለት ምሁራን ለወራት የዘለቀው የኦሮሞ ህዝብ እንቅስቃሴና የጎንደር ህዝብ መብቱን ለማስመለስ የሚያደርገውን ትግል ተቀናጅቶ ከቀጠለ የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነቱ የሚያደርገው ጉዞ ሩቅ እንደማይሆነ አስታውቀዋል።

በቺካጎ ኤሊኖይ ግዛት ሃርፐር ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው ህወሃት ሰሜናዊው ምስራቅ የወሎ ክፍልና ሰሚናዊ ምስራቅ የጎንደር ክፍልን ወደ ትግራይ ለመጠቅለል ታሪካዊ መነሻ ኖሮአቸው ሳይሆን ሁለት መሰረታዊ ችግሮችን ለመሻገር በማሰብ እንደሆነ ይገልጻሉ። እነዚህ ሁለት ችግሮች ትግራይ የኢኮኖሚ በተለይም የግብርና ምርት እጥረት በመኖሩ እና ከጎረቤት ሃገራት ጋር ድንበር የማይጋሩ በመሆኑ ይህን ለመፍታት እንደሆነ ገልጸዋል።
በትግሉ ወቅት ወልቃይትን በአካል እንደሚያውቁት የገለጹት ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ወልቃይት በትግራይ ለአንድም ቀን ተዳድራ እንደማታውቅ አስታውሰዋል። ሆኖም ግን የትግራይ ተወላጆች የተከዜን ወንዝ ተሻግረው ለግብርና ስራ ይመጡ እንደነበር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የህግ ምሁሩና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባት /አዴግ/ ከፍተኛ አመራት የሆኑት ዶ/ር በያን አሶባ በወልቃይት ላይ ህወሃት የፈጸመውን የህዝብ ስብጥር መቀየሩ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደሆነ አስታውቀዋል። “የወልቃይት ህዝብ ማንነት መወሰን የሚችለው ህወሃት ሳይሆን ራሱ የወልቃይት ህዝብ ነው” በማለት አስገንዝበዋል። “የወልቃይት ህዝብ ትግል መላው የኦሮሞ ህዝብ ይደግፈዋል፣ ድርጅቴ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባት አጋርነቱን ባወጣው መግለጫ አመላክቷል” በማለት የተናገሩት የህግ ምሁሩ ዶ/ር በያን አሶባ በአለም አቀፍ ህግም ተቀባይነት ያለው እንደሆነ አሳስበዋል።
ሁለቱ ምሁራን በመግለጫቸው ህወሃት በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ቁመና የሌለው በመሆኑ በጋራ ትግል ግብዓተ-መሬቱ መፈጸም እንዳለበት፣ ለዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ መተባበር እንዳለበት አስገንዝበዋል። በኦሮሚያ እና ጎንደር የተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ሃገር አቀፍ ንቅናቄ እንዲቀየር በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶችና መላው የኢትዮጵያውያን እንዲቀናጁ ጥሪ አቅርበዋል።

No comments:

Post a Comment