❖❖ኢትዮጵያዊው አቡነ ጴጥረሮስ በየት ተቀበሩ?❖❖
አቡነ ዼጥሮስ በአረመኔው ፋሺስት ጦር ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ/ም ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ ላይ በግፍ በመገደል ሰማዕትነትን የተቀበሉ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነትን ከተቀበሉ ጊዜ አንስቶ ታሪካቸው በጥቂቱም ቢሆን ሲነግር የኖረ ቢሆንም፤ መታሰቢያም ይሆናቸው ዘንድ በአጼ ኃይለሥላሴ አሳሳቢነት በ1938 ዓ/ም ሰማዕትነትን በተቀበሉበት አካባቢ ሐውልት ቢቆምላቸውም፤ ቅድስት ቤተክርስቲያንም ስለተጋድሏቸው የቅድስናን ማዕረግ ብትሰጥም እስከ ዛሬ ግን አስክሬናቸው በየት እንዳረፈ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ አስፈላጊውም ምርምር ሲደረግ አልታየም፡፡ አሁን ግን ነገሩን ጉዳዬ ብሎ የሚይዝና የሚያጣራ ቢገኝ የዚያን ዘመን የአስር አመት ልጅ የነበሩ የዘንድሮ አረጋዊ የሆኑ አንድ አባት የዛሬ ሰማኒያ ዓመት አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ እርሳቸው በቤታቸው ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው የተፈጠረውን ታሪክ የጴጥሮስ ዋዜማ የተባለውን ታሪካዊ ልብወለድ መጽሐፍ ለደረሱት ለደራሲ ፀሐይ መላኩ እንዲህ ሲሉ ነገረዋቸዋል "ከወላጆቼ ጋር እኖርበት የነበረው ቦታ ከጎኑ አንድ ጉብታ ነበረው፤ በዚህም ጉብታ ላይ ጣሊያኖች ይኖሩበት ነበር፤ ከዚያም በጣሊያን ጦርነት ጊዜ የሆነ ቀን ላይ አባቴ በጣም አመሸ ሰዓቱም ገፍቶ እኩለ ለሊት አለፈ፤ እናቴም ምን ሆኖ ይሆን ብላ በጣም ተጨንቃ ታለቅሳለች፤ እኛም እንቅልፍ ሳንተኛ እሳት እየሞቅን አባታችንን እንጠብቃለን፤ ከዚያም ሊነጋጋ ሲል አባቴ በጣም ደንግጦና አዝኖ እየተንቀጠቀጠ ወደ ቤት ገባ እናቴም <ምን ሆነክ ነው ስትል ጠየቀችው> አባቴም <ታላቅ ሰው እዚህ መጥተው አረፉ፤ ጣሊያን እዚህ መጥቶ ቀበራቸው አቡኑ ናቸው፤ እኔንም ጉድጓድ ቆፍር ብለው እዚያው ነው ያደርኩት> ሲል መልሰላት በዚህ ጊዜ ሁላችንም ተደናግጠን መብረቅ የሚወርድብን መስሎን ነበር፡፡" እንግዲህ እኚህ አባት በተናገሩት መሠረት ይህ ታሪክ የተፈፀመው በአዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ ለቡ አካባቢ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ጎን በጉብታ ላይ ሆኗ በሚታየው ጥንታዊ የግንባታ ቅርጽ ያለው በአሁኑ ሰዓት በረጅም ግንብ ታጥሮ በሚገኘው ቤት ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ደራሲ ፀሐይ መላኩ ይህን መረጃ ይዘው ለሚመለከተቻው አካላት ሁሉ ቢያሳውቁም ጉዳዩን ግን ነገሬ ብሎ ፍለጋ የጀመረ አካል እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ይህ ቤት በቅድሚያ የተሰራው በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ሲሆን የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ከንቲባም የሚኖሩበት ቤት ነበር ከዚያም ጣሊያኖች ሀገራችን ሲገቡ በዚያ መኖር እንደጀመሩ ይነገራል ይህንንም መረጃ አጠናክሮ ቤቱ የሚገኝበት ክፍለ ከተማ የቱሪዝም ጽ/ቤት ጥንታዊ ቅርስ ነው ብሎ ቢመዘግብውም ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር ተያይዞ ግን በቦታው ላይ ስለሚነገረው ታሪክ በወሬ በወሬ ክፍለ ከተማው የሚሰማው ነገር እንዳለ ሆኖም ግን የተጠናከረ ጥናት እንዳላደረገ ለማወቅ ችለናል፡፡ የሆነው ሆኖ ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር በተገናኘ በዚህ ቤት እና በዙሪያው ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተገቢውን ጥናትና ምርምር ሊያረጉ ይገባል ይህንን የመቀስቀስ ኃላፊነት ደግሞ የሁላችን ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በክርስትና እምነት ውስጥ ላለን ከቅዱስ ሰውነታቸው በረከትንና ፈውስን ማግኘት እንፈልጋለንና አጽማቸው ይፈለግ ልንል ይገባል፤ ከሃይማኖት ውጪም ያሉ አቡነ ጴጥሮስ የጀግንነት፣ የጽናትና የሀገር ፍቅር ተምሳሌት ናቸውና አጽማቸው ተፈልጎ በክብር እንዲያርፍ ሊጠይቁ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ምንም እንኳን ክፍለ ከተማው ቦታውን ቅርስ ነው ቢልም እንደ ቅርስ እንክብካቤ ከማድረግ ይልቅ ግን ከ1997 ጀምሮ ቤቱን ለአምስት አባወራዎች አከፋፍሎ እያስኖረበት ይገኛልና የአቡነ ጴጥሮስ የተባለው ታሪክ ተፈፀመበትም አልተፈፀመበትም የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ከንቲባ መኖሪያ እስከሆነ ድረስ ግን አስፈላጊው ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል እላለሁ፡፡
ምንጭ፦ የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን ዝግጅት
- ደራሲ ፀሐይ መላኩ
No comments:
Post a Comment