Wednesday, July 20, 2016

ጋዜጠኛ ሳምራዊት ስንታየሁ ተሰደደች – የመንግስት ጋዜጠኞች ስርዓቱን ጥለው መኮብለሉን ተያይዘውታል


(ዘ-ሐበሻ) በታች በኦሮሚያ በኩል በላይ በጎንደር በሕዝብ አመጽ የተወጠረው የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መንግስት የሚያስዳድረው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ (የኢትዮጵያ ራድዮና ቴሌቭዥን) በዜና እና በወቅታዊ ዝግጅት ክፍል በምክትል ዋና አዘጋጅነት ስትሰራ የነበረችው ጋዜጠኛ ሳምራዊት ስንታየሁ ሃገሯን ጥላ ተሰደደች።ለአቶ በረከት ስምዖን የሚዲያ ሞኒተሪንግ ኢንፎርሜሽን ኤክስፐርት በመሆን ያገለገለችው ጋዜጠኛ ሳምራዊት በተለይ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሙያዋ ስነምግባር የሚያዛትን የሕዝቡን ብሶትና ወቅታዊ ጉዳዮችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሀብ የሃገሪቱን መልካም ገጽታ ስለሚያጠፋ በማንኛውም መንገድ ለሕዝብ በሚዲያ መነገር የለበትም በሚል እንዳትዘግብ በሚደርስባት ጫና እና አፈና የተነሳ ስራዋን ለቃ ለመውጣት እንደተገደደች የዘ-ሐበሻ ምንጮች አስታውቀዋል።

እንደምንጮች ገለጻ ከሆነ በማንኛውም መንግስታዊ ሚድያ እንዳይዘገብ የተከለከለው በኢትዮጵያ የተከሰተው ረሃብ፤ በኦሮሚያና በጎንደር ሕዝባዊው ቁጣ አይሎ ከወጣ በኋላ የመንግስት ጋዜጠኞች እውነተኛውን የሕዝቡን ብሶትና እየደረሰ ያለውን እውነታ እንዳይዘግቡ ተከልክለዋል። በተለይም የሕዝቡን ተቃውሞ በነፃነት እንዘግብ ብለው የተነሱ ጋዜጠኞች እንደሚገመገሙና ወደ እስር እንደሚወረወሩ የሚመጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህ ሕዝባዊ ቁጣ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በርከት ያሉ የመንግስት ሚድያ ጋዜጠኞች ሃገራቸውን እየጣሉ እየተሰደዱ ስለመሆኑ ዘ-ሐበሻ መዘግብው አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ራድዮ ቴሌቭዥን በዜና እና ወቅታዊ ዝግጅት ክፍል በምክትል ዋና አዘጋጅነት ስታገለግል የቆችው ጋዜጠኛ ሳምራዊት ተቀማጭነቱ በ እንግሊዝ የሆነ መንግስታዊ ያለሆነ ድርጅት ውስጥም በኮምዩኒኬሽን አስተባባሪነት ታገለግል እንደነበር ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
ይህ በ እንዲህ እንዳለ በጎንደር የተከሰተውን የሕዝብ አመጽ ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስታዊ ጋዜጠኞች በከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደሚገኙ ታወቀ። ጋዜጠኞች ስለሕዝባዊው ተቃውሞ እንዳትዘግቡ የሚል ት ዕዛዝ የወረደላቸው ሲሆን መንግስት ከሚያወጣው መግለጫ ውጭ ምንም ዓይነት ዘገባ እንዳይሰሩ ታዘዋል። አንዳንድ ጋዜጠኞች ይህ ሁሉ የሕዝብ አመጽ ተከስቶ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ማለት አንችልም፤ የሙያ ስነምግባራችንም አይፈቅድልንም በሚል እያግሩረመረሙ እንደሚገኙ ተሰምቷል።

No comments:

Post a Comment