Wednesday, July 20, 2016

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢትዮጵያውያን ከአፋኝ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት እንዲተባበሩ ጥሪ አቀረበ ኢሳት ((ሃምሌ 12 ፥ 2008)


የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኦዴግ/ ከጎንደር ህዝብ ጎን እንደሚሰለፉ አስታወቁ። የጎንደር ህዝባዊ እንቅስቃሴ መሪዎች ትግላቸውን ከኦሮሞ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ጋር እንዲያቀናጁና ሌሎች ኢትዮጵያውያን  ከአፋኝ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።
በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (አዴግ) ሰኞ ሃምሌ 11 ፥ 2008 ባወጣው መግለጫ ህዝብ ለነጻነት፣ ለዲሞክራሲና ለመብት ትግል የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዕመቃ እንደማያቆመው፣ በኦሮሚያ የቀጠለውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ አስታውቀዋል።

የጎንደር ህዝብ እንደ ኦሮሞ ወንድምና እህቶቹ የህወሃትን አግላይነት ለመታገል ተንቀሳቅሰዋል በማለት የቀጠለውን የኦዴግ መግለጫ የነጻነት ትግል ከድል በመለስ ምንም ሃይል እንደማይገታው አስገንዝቧል። የኦሮሚያና የጎንደር ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች የህወሃትን ፍጻሜ እንዲያመጡና የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻ እንዲወጣ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ህዝባዊ እንቅስቃሴውን እንዲቀላቀሉ ኦዴግ ጥሪውን አቅርቧል።
በመላው ኦሮሚያ ለ8 ወራት በቀጠለውና አሁንም የጎንደር ህዝብ የጀመረውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ፣ በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች እንዲቀጣጠል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ለፖለቲካ ሃይሎችና ለሲቪክ ድርጅቶችም ጥሪ አቅርቧል። የህወሃት 25 አመታት አገዛዝ እያበቃለት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የአፈናና የግድያ ስርዓት ቢቀጥል፣ ሃገሪቱ ወደ ቀውስ ታመራለች ሲልም ስጋቱን ገልጿል። ተቃዋሚዎችን መድፈቅ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን ማስቀጠል፣ ኢፍትሃዊ የሆነው የሃብትና የመሬት ቅርምት፣ እንዲሁም ተቋማዊ የሆነው ዘረፋና የሃገሪቱ ተቋማት እየተዳከሙ መሄድ በቶሎ ካልተገታ ኢትዮጵያን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይከታታል ሲልም አሳስቧል።
የኦሮሞ ዴሞክራዊያዊ ግንባር (አዴግ) በመጨረሻም ለጎንደር ህዝብ ያለውን ሙሉ ድጋፍ በማረጋገጥ የንቅናቄው መሪዎች ትግላችንን በጋራ እናስተባብር ሲል ጥሪ አቅርቧል። ሌሎች ኢትዮጵያውያንም የኦሮሚያንና የጎንደርን ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርቧል። ከህወሃት አገዛዝ የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻ እናውጣ በማለትም መልዕክቱን አስተላልፏል።

No comments:

Post a Comment