Friday, July 22, 2016

የሕዝብን ጥያቄ በሃይል ማንበርከክ ክቶዉንም አይቻልም (ከጠለምት ተወላጆች ዓለም ኣቀፍ ትብብር የተሰጠ መግለጫ)

ሰሞኑን ፀረ ሕዝቡ የወያኔ ገዢ ቡድን በወልቃይት፥ ጠገዴና በጠለምት የማንነት ጥያቄ ኣስተባባሪ ኮሚቴ የኣመራር ኣባላትን ጨለማን ተገን በማድረግ በድብቅ ኣፍኖ ወደትግራይ ለመውሰድ ጎንደር ከተማ ኣድፍጦ የቆየው ኣፋኝ ነብሰ ገዳይ ቡድን እነዚህን ብርቅየ የሕዝብ ልጆች የወሰደዉ ኢስብኣዊና አረመኒያዊ ተግባር ኣጥብቀን እንቃወማለን።
መሳሪያ ሳይዝ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በደሉንና ብሶቱን ላቀረበ ሕዝብ የሚሰጥ ምላሽ ኣፈና፥ እስራትና ግድያ ሊሆን አይገባዉም ነበር። ይሁን እንጂ ገና ከጅምሩ ሕዝብን ለስቃይ ሃገርን ለጥፋት ለማብቃት ሽንጡን ገትሮ ከሚታገለው ኣረመኒያዊ የወያኔ ቡድን ይህ እንደሚጠበቅ ላፍታ እንኩዋን ኣንዘነጋዉም።
የሃያ ዓምስት ዓመታት የመከራና የሰቆቃ ስቃይ ተወልዶ ባደገበት ፥ ልጅ ወልዶ ባስተማረበትና ለሃገሩ ኣርሶ በጠቀመበት  ምድሩ፥ እንደሰዉ መኖር ተነፍጎ በግፍ ላይ ግፍ በየቀኑ ኣረመኔ በሆኑ የስርዓቱ ኣሽከሮች እየተፈፀመበት፥ ግፍና በደሉ ሲበዛበት ሕግና ስርዓትን ተከትሎ ኣቤት በማለቱ፥ የሚደርስበት፥ ስቃይ መሸከም በቅቶት በቆራጥንትና በኣንድ ልብ ይህን የሃገርና የሕዝብ ጠላት የሆነን ሥርዓት ለመታገል ዛሬ ኣደባባይ መውጣት የደረሰበት ወቅትና ለነፃነቱ ወደሗላ ላይመለስ ለትግል ዝግጁ ሆኖ ይገኛል።

ይህ ብሶትና በደል ገፋፍቶት የተነሳ ሕዝባዊ ቁጣ በበሰለና በሰከነ መንገድ የሕዝብን ጥያቄ መልስ ካልተሰጠ በቀር በሃይልና በመሣሪያ ጋጋታ ጥያቄዉን ለማፈን መሞከር ሊያመጣ የሚችለዉን መዘዝ ከወዲሁ ልናስጠነቅቅ እንወዳለን። በሃይል ታፍኖ በመሣሪያ ብዛት ተቀብሮ ፀጥ ለጥ ያለ የሕዝብ ቁጣ በየትኛዉም ዓለም ኣልታየም። ጊዜ ይወስድ እንደሆን እንጂ ሁሉም የሕዝብን ቁጣ በየደረጃቸው ይቀምሱታልና።
ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
ይህ የሃገርና የሕዝብ ጠላት የሆነን ኣገዛዝ ለኣንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድ ኣንዱ ኣከባቢ ሲነሳ ሌላው ዝም እያለ ሳይሆን ሁላችንም በኣንድነት በሁሉም የሃገራችን ኣቅጣጫ በጋራ መንቀሳቀስ ካልቻልን የግፉና የመከራዉን ፅዋ በየተራ እየተቀበልን  እንኖራለን። በኣንድ ኣከባቢ የሚነሳን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በሌላው ኣክከባቢ ያለዉ ሕዝብ  ሊደግፈዉና እሱም ኣብሮ ሊነሳ ይገባዋል። በመሆኑም ዛሬ ይህን ኣስከፊ ሥርዓት ፊት ለፊት  እየታጋፈጠ ካለዉ የወልቃይት፥ የጠገዴ፥ የጠለምትና የጎንደር ሕዝብ በኣጠቃላይ ከኣማራው፥ ከኦሮሞውና ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር በመሰለፍ ሃገራችን ከከፍተኛ ኣደጋ ለማዳን ነገን ሳንል ዛሬ በጋራ እንድንነሳ በኣክብሮት እንጠይቃለን።
ቆራጡና ጀግናው የጎንደር ክ/ሃገር ሕዝብ ሆይ! ለበርካታ ዓመታት የተፈፀመብህን ግፍና ስቃይ ሞልቶ ተሸክሞ መኖር በቃኝ ብለህ ለማንነትህና ለመብትህ የምታደርገው የጀግና ሕዝባዊ ትግል እኛ በዉጭ ሃገር የምንገኝ ልጆችህ የምንደግፈዉና ከጎንህ የምንቆም መሆናችንን በኩራት ለመግለፅ እንወዳለን። ዛሬ የምትከፍለው የደም ዋጋ ለወገንህና ለምትወዳት እናት ሃገርህ ኢትዮጵያ በመሆኑ እንደ ቀደምቱ ዛሬም ገድልህ ህያው ሆኖ ይኖራል።
ላለፉት ሃያ ኣምስት ዓመታት የፈፀማችሁት ግፍና ሰቆቃ ኣልበቃ ብሎኣችሁ ይሄውና ዛሬም በኦሮሞ፥ በጋምቤላ፥ በኮንሶና ሰሞኑን ለማንነቱና ለመብቱ የሚታገለዉን የጎንደር ሕዝብ በሃይል ለመደፍጠጥ የምትጥሩ የስርዓቱ መሪዎችና ጀሌዎች ሰሞኑ በጎንደር በተነሳው ሕዝባዊ ዓመፅ እንደተመለከታችሁት ዛሬዉኑ የምትፈፅሙት ግፍና በደል ካላቆማችሁ የሚደርስባችሁን የሕዝብ ቅጣት የሚሸከም ትክሻ እንደማይኖራችሁ ልናስገነዝባችሁ እንወዳለን።
በመጨረሻም በተናጥል የምናደርገዉን ሕዝባዊ ኣመፅ በጋራ ኣድርገን ሃገራችንን ከመበታተን ሕዝባችንን ከመከራና ከግፍ ለማዳን ከወልቃይት፥ ጠገዴና ጠለምት፥ በጠቅላላው ከጎንደር፥ ከኣማራ፥ ከኦሮሞ፥ ከጋምቤላ፥ ከኮንሶና ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር በጋራ ሆነን ኢትዮጵያን እንድናድን ሃገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። ሰሞኑን በቆራጥነትና በጀግንነት ይህን ሃገር በቀል ከሃዲ ሥርዓትን ለማስወገድ እየታገለ ካለዉ የጎንደር ክ/ሃገር ሕዝብ ጎን ሁላችንም እንድንቆም እናሳስባለን።
ሕዝባዊ ቁጣን ብሃይል ማፈን ኣይቻልም!
ኢትዮጵያ በልጆቻ ተጠብቃ ለዘላለም ትኖራለች !!
የጀግናው የጎንደር ክ/ሃገር ሕዝብ ትግል እናደንቃለን ከጎኑም እንቆማለን!!!

No comments:

Post a Comment